ዛሬ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን እጅግ ታሪካዊ ቀን ነው።
እንኳን ደስ ያለን።
ሕልማችን ዕውን እየሆነ ነው። በርካታ ኢትዮጵያውያንና መሪዎቻችን ዓባይን ለማልማት ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም ዕቅዳቸው በተለያዩ መሰናክሎች ተስጓጉሏል።
ነገር ግን "እኛ አሁን ባይሳካልንም መጪው ትውልድ ይገነባዋል" የሚል ታላቅ እምነት ነበራቸው። ይህ ትውልድ ያንን አደራ ጠብቋል። ኃላፊነቱንም እየተወጣ ነው።
የሚጠራጠር ካለ ዛሬ ምላሹን አግኝቷል። ተፈጥሮም እንኳን ምስክርነቷን ሰጥታለች። የሃገራችን ሃብት ከዜጎቿ አቅም፤ አንድነትና እና ቁርጠኝነት ጋር እስከተቀናጀ ድረስ ምንም የማይቻለን ነገር የለም።
ከተባበርን፤ ለአንድ ዓላማ ከቆምን ምንም የሚያግደን ነገር የለም።
ኢትዮጵያ ለራሴ ብቻ ብላ አታውቅም። ሁልጊዜም እንደምንለው የዓባይን ውኃ መጠቀማችን በአካባቢው እህትማማች ሀገራት መካከል ድንበር ተሻጋሪ ትብብሮች እንዲጠናከሩ የተለየ ዕድል ይሰጣል እንጂ የመጠራጠርና የውድድር ምንጭ ጨርሶ ሊሆን አይገባም።
አሁን ግድባችን ወደ ኋላ ሊመለስ እንደማይችል በተግባር ተረጋግጧል። ይህ እርምጃ አካባቢያችንን የሰላምና የመረጋጋት ምንጭ ለማድረግ ለሚተጉ ኃይሎች ሁሉ ታላቅ ድል ነው።
ብስራቱም ለመላው የተፋሰሱ አገራት ሀገራት ሕዝቦችም ጭምር ነው።
ኢትዮጵያ የተ.መ.ድ መሥራች አገር ነች። ከ75 ዓመታት በፊት ቻርተሩ ላይ ፊርማዋን ያሳረፈች አገር ነች። ድርጅቱ ከተቋቋመበት መርህ አፈንግጣ አታውቅም።
ለአፍሪካ አንድነት፣ የጋራ ሰላምና ዕድገት ያላት ዘመናትን እንዲሁም መንግሥታትን የተሻገረ የማያወላውል አቋምና ተጨባጭ ተግባር ምስክር አያሻውም። የምናድገው አብረን ነው።
ቀጣዩ ወሳኙ ምዕራፍ የሆነው የኃይል ማመንጨት ፍላጎታችን ያለ ጥርጥር ዕውን ሊሆን እንደሚችል ዛሬ አሳይቶናል። ዓይኖቻችን ከዚህ የመጨረሻ መደረሻ ሊነቀል አይገባም።
ግድባችንን ማጠናቀቅ ማለት ለዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን ውል ማበጀት ማለት ነው። ይህ ደግሞ ሁላችንንም ይመለከተናል። በርካታ የቤት ሥራዎች እንዳሉን አንዘንጋ።
ከፍታን እንመልከት። ከፍ ብለን እንመኝ። ወደ ከፍታው የሚወስደን ላይ እናተኩር። አንድ ላይ በሆንንና በተባበርን ቁጥር ከአማችን በላይ የሚሆን የለም።