የካርታ ፕሮፓጋንዳ ፋይዳና ዕዳ

ካርታ ትክክለኛ መረጃን አቅልሎና አሳምሮ እንደሚያሳይ ሁሉ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታም ይውላል። የካርታ ፕሮፓጋንዳ ትርጓሜም ካርታን በመጠቀም ሆን ብሎ የካርታ አንባቢውን ምልከታ ወደ ሚፈለገው አቅጣጫ ማስኬድ ነው።

Dr Daniel Kassahun

Dr Daniel kassahun (L) and World map by Camaldolese monk Fra Mauro, 1449. Detail: Ethiopia. Source: D.Kassahun and Getty

በደርግ ዘመን ወደ መጨረሻው አካባቢ ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሽምቅ የአርነት ውጊያን ባጧጧፈበት ወቅት ፕሮፓጋንዳን በዕጅጉ ተጠቅሟል። በውጤቱም ግዙፍ ሠራዊትና የመሣሪያ አቅም የነበረውን የኢትዮጵያን ጦር ከሽሬ እንዳ ሥላሴ በቀር በቀላል ውጊያ በማሸነፍ በርካታ ሥፍራዎችን ባጭር ጊዜ ለመቆጣጠር አስችሎታል።

የደርግን ጃሚንግ ተቋቁሞ በዘወትር ዜናው ይህን ያህል ሺህ የአምባገነኑን፣ የደርግ-ኢሠፓውን ሠራዊት ማረኩኝ፣ ገደልኩኝ፣ መሣሪያ ወረስኩኝ፣ ቁልፍ ወታደራዊ ቦታን አስለቀቅሁኝ፣ በድንጋይ ኮሎኔል ማረኩኝ እያለ ሽብር ይነዛ ነበር። ለቀጣዩ የአዲስ ዓመት፣ የገና፣ ወይንም የፋሲካ እገሌ የተባለውን ከተማ ተቆጣጥሬ በዓሉን አከብራለሁ የሚል ትንቢትንም ያዘወትር ነበር።

በወቅቱ የሟቹና ተማራኪው ወታደር ድምር ቁጥር ከአገሪቱ አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር ልቆ መገኘት ሕዝቡም ሆነ ጋዜጠኞች “ይሄ ሁሉ ቁጥር ወደፊት ከሚወለደው ዜጋ በብድር የተገኘ ነው እንዴ” የሚያስብል ስላቅም ፈጥሮ ነበር። በዜናዎቹ ጠባይ በሽብር ይናጡ የነበሩት በጦርነቱ አቅራቢያ የሚገኙ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ኗሪዎች ብቻ አልነበሩም። ግንባር ላይ የነበሩ ጦር ክፍሎች ገና የተኩስ ልውውጥ ሲጀመር ነበር ከባድ መሣሪያዎቻቸውን ጭምር እየጣሉላቸው ያፈገፍጉ የነበረው።

የተከለከለን ነገር መሻት የሰው ባሕሪ ነውና “የወንበዴን ራዲዮ አታዳምጡ” ብሎ ሲከለከል ይልቁኑ የሽብር ወሬው በሹክሹክታ መረብ በሰፊው እንዲንሸራሸር አደረገው። ሕወሓት/ኢሕአዴግም የአናሎግ ሚዲያ ፕሮፓጋንዳ ብቃቱን በደርግ ሚዲያ ላይ የበላይነቱን በማስመስቀር ከአራት ኪሎ የሥልጣን ኮርቻ ማማ ላይ ተፈናጠጠ።

በሰፈሩት ቁና? 

ጊዜ ጠብቆ ከሁለት ዐሥርት ዓመታት በላይ በፍጹም የበላይነት የሥልጣን መንበር ላይ ከቆየ በኋላ ስሉስ ዞሮ የኢሕአዴግ ሚዲያም ከአጥቂነት ወደ ተካላካይነት ተዘዋወረ። በሰፈሩት ቁናመሰፈር አይቀርምና ሕዝባዊ አመፅ ተቀስቅሶ ማዕበሉ ከትግራይ ክልል በቀር ከጫፍ ጫፍ ተቀጣጠለ።

በጸረ-ሽብር ዐዋጁ ተቃዋሚዎች “ሽብርተኛ” ተባሉ፣ አስር ቤቶች ተጣበቡ፣ የሕትመትም ሆነ የዲጂታል ሚዲያዎች ላይ እገዳ ተጣለ፣ 264 ድረ ገጾች ተዘጉ፣ የኢሣት ቲቪ 28 ጊዜ ጃሚንግ ተደረገበት፣ አንዳንድ የተቃዋሚ መሪዎች በሌሉበት የሞት ፍርድ ተፈረደባቸው፣ በርካታ ጋዜጠኞችና ተቃዋሚዎች ለእስርም ሆነ ለስደት ተዳረጉ።

በመጨረሻም የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ በ2010 ዓም ሲያውጅ ውጥረቱን አከረረው። ሲፈርድበት ኢሕአዴግ ከተቃሚዎችና አክቲቪስቶች የገጠመው የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ቀድሞ እጅግ በተጠበበት የራዲዮ ሞገድ ሳይሆን በማኅበራዊ ሚዲያ ሜዳ ላይ ነበር። የማኅበራዊ ሚዲያ የፀደዩን አብዮት በማፋፋም ለበርካታ የአረብ አገራት አምባገነን መሪዎች መንኮታኮት አስተዋፅኦ እንዳደረገው ሁሉ የኢሕአዴግ መንግሥትንም ሽባ አድርጎ ለለውጥ ዳርጎታል።

በተቃውሞው ወቅት እንኳንስ በከተማ ወደ አጎራባች የገጠር አካባቢዎችም የስልክና የኢንተርኔት ሥርጭት አየተስፋፋ ነበር። የማኅበራዊ ሚዲያ ማናቸውም ግለሰብ ከየትኛውም ሥፍራ ሆኖ ተጠያቂነትና ቅድመ ምርመራ ሳያግደው መረጃን በፍጥነት ለማስተላለፍ፣ ሕዝቡን ለተቃውሞ ለማስተባበርም ሆነ ለአመፅ ለማነሳሳት አስቻለ። ሆኖም ማኅበራዊ ሚዲያው ከትክክለኛ መረጃ ጋር ቀላቅሎ የተጋነነ ሁነትን፣ ያልተረጋገጠ መረጃን፣ ግርድፍ ግምትን ያንሸራሽር ነበረ።

ባመዛኙ በጽሑፍ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ተንቀሳቃሽ ምስሎችን፣ ፎቶግራፎችንና፣ ካርታዎቸን አጣምሮ ማቅረቡ የመረጃዎችን ቅቡልነትና ተአማኒነት አጎልብቶ ማኅበራዊ ሚዲያን በፕሮፓጋንዳው ፍልሚያ የላቀ የበላይነት አላበሰው።

ማየት ማመን?

አንድ ምስል የአንድ ሺህ ቃላት ዋጋ አለው ይባላል። ናፖሊዮን ቦናፓርት ሲናገርም “ከረዥም ወሬ ይልቅ ግሩም ሆኖ የተዘጋጀ አንድ የምስል ንድፍ ይሻላል” ይላል። የካርታ ዋጋ ከአንድ ሺህ ቃላት ቢበልጥ እንጂ አያንስም። ካርታ ደጋግመን እንድናየው ይጋብዘናል፣ አንሰለቸውም። ቀድሞ ለባለሞያዎች ብቻ ያገለግል የነበረ ካርታ አሁን ከመደበኛ ሕይወታችን ጋር እጅና ጓንት ሆኗል።

በዜና፣ በምርጫ፣ በንግድ፣ በማስታወቂያ፣ በቅስቀሳ፣ በዕቅድ፣ ወዘተ ሁሉ ካርታ አለ። የአንዳንድ አገራት የፖለቲካ ካርታ ወረቀት ላይ በእርሳስ የሚሰመረው በዲፕሎማቶች ወይንም በጦር ጄኔራሎች ነው። ይህም “ብዕር ከሰይፍ ይልቃል” የሚሰኘውን አባባል የለበጣ ያደርገዋል ይላል ሞንሞኒየር የተባለ የካርታ ሊቅ። 

የሰው ልጅ ለምስል መረጃ የቀረበ ነው። Man is a virtual animal እንዲሉ። የካርታ መልዕክትን የምንረዳው በማየት ነው። ማየት ማመን ነው ይባል የለ? የእንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ነገር ሲገባቸው “I see” (አየሁ፣ ገባኝ) እንደሚሉት። እንደ ጥናቶች ከሆነ የሰው አንጎል ከጽሑፍ መረጃ ይልቅ ምስልን ሲመረምር 60 ሺህ እጥፍ ጊዜ ይፈጥናል። የካርታ ጠቢባን “ምስልን በመጠቀም ነጭ ውሸትን እንኳ አስውቦ ማቅረብ ይቻላል” ይላሉ። ስለዚህም ካርታ ለበጎ ምግባር ሲውል ፋይዳው ትልቅ ነው።

ካርታም ይዋሻል?

ካርታ ትክክለኛ መረጃን አቅልሎና አሳምሮ እንደሚያሳይ ሁሉ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታም ይውላል። የካርታ ፕሮፓጋንዳ ትርጓሜም ካርታን በመጠቀም ሆን ብሎ የካርታ አንባቢውን ምልከታ ወደ ሚፈለገው አቅጣጫ ማስኬድ ነው። እንደውም “እንዴት በካርታ መዋሸት ይቻላል” በሚል ርዕስ የታተመ መጽሐፍም አለ። ዘዴውም የወሰን መስመሮችን በማቅጠን፣ በማጉበጥ ወይንም በማወፈር፣ ቀለሞችን በማድመቅ ወይንም በማደብዘዝ፣ ሥፋትን በማተለቅ ወይንም በማሳነስ፣ ወዘተ ነው።

እንዲሁም የቦታ ሥምን መቀየር፣ ኮርዲኔቶችና ልኬትን ማዛባት፣ ወዘተ። ለምሳሌ ራሺያኖች ሚስጥር ለመጠበቅ ሲሉ በካርታዎቻቸው ላይ ልኬት እንዳይኖር ያደርጉ ነበር። በሞስኮ ከተማ ካርታ ላይ የኬጂቢና ሌሎች ስትራቴጂካዊ ሕንጻዎች መጠናቸው እጅግ አንሶ እንዲሰፍር ያደርጉ ነበር። በተለይም ለውጪ ዜጋ የራሺያ ከተሞች ካርታን ተመርኩዞ ትክክለኛ መረጃን ማግኘት ፈታኝ ነበር። 

ከአገራት የድንበር ግጭት ጀርባ ሁሌም የካርታ አሻራ አለ። በፖስታ ቴምብር ላይ በሚሠፍር ሚጢጢ ካርታ ሳቢያ እንኳ አገራት ወደ ግጭት የሚገቡበት አጋጣሚ አለ። ፓኪስታን የካሽሚርን ግዛት (በሕንድ ውስጥ ያለችውን) እንደራሷ አካል አድርጋ በቱሪስት ካርታዋ ላይ ስታመላክት፣ አርጀንቲና የፎክላንድን ደሴትን (በእንግሊዝ ተያዘችውን) በቴምብር ላይ ስታሰፍር፣ ቻይና በፓስፖርቷ ላይ ባስቀመጠችው ካርታዋ ላይ አወዛጋቢ የጎረቤት አገራት መሬቶችን አክላ ስታሰራጭ፣ ወዘተ የዲፕሎማሲ ቀውሶች ተከስተዋል።

ካርታ በሕዝበ ውሳኔ ላይ ተጸዕኖ ሲያሳድርም በቅርቡ አይተናል። ከአምስት ዓመት በፊት እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት እንገንጠል ወይንስ አንገንጠል በሚለው የሕዝበ ውሳኔ ወቅት ካርታ ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ሆኖ በሁለቱም ጎራ አገልግሏል። ሆኖም ግን እንገንጠል የሚለው ቡድን የተጠቀመው የካርታ ፕሮፓጋንዳ የበለጠ ውጤታማ ነበር።

ባቀረቡት ካርታ እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ብትቆይ ከሶሪያ፣ ኢራቅ እና ቱርክ ሊመጡ በሚችሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህገወጥ ስደተኞች እንደሚጥለቀለቁ የሚያሳይ ቀለማቸው ቀይ የሆኑ (አደጋን አመላካች ቀለም ነው) ቀስቶች ወደ እንግሊዝ አቅጣጫ ስላነጣጠሩባቸው የህዝቡን የስጋት በማናር ወደ መገንጠል እንዲያዘነብሉ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።

ካርታ ለድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕሮፓጋንዳም ይውላል። ለምሳሌ እስራኤል በበርካታ የአረብ አገራት የተከበበች ናት። በአንድ በኩል እነ አሜሪካ የደህንነት ሥጋቷን በመገንዘብ የጦር መሣሪያ እንዲረዷት ለማስቻል፣ በሌላ በኩል እስራኤል ራሷ በፓለስታይን መሬቶች ላይ የምታደርገውን ሕገወጥ ሠፈራ እንዳይቃወሟት ካርታን በመሣሪያነት ትጠቀማለች።

የአገሯን ካርታ ለብቻው ነጥሎ ከማሳየት ይልቅ መላውን የመካከለኛ ምስራቅ አገራትን ካርታ በማሳየት፣ እስራኤል ምንኛ መጠናቸው ግዙፍ በሆኑ አገራት የተከበበች ተሰባሪ (fragile) አገር ሆና እንድትታይ ለማስቻል ትጥራለች። ተሳክቶላታልም።

ልክ የመጽሐፍ ቅዱሱ ግዙፉ ጎልያድ ወጣቱ ዳዊትን ሊጨፈልቅ እንደዳሰፈሰፈ ዓይነት የሚመስል የካርታ ድባብን በመፍጠርና የዳዊትን አሸናፊነት የሚያስገኝላትን የብዙ አገራት ድጋፍና አጋርነት በቀላሉ ትሸምታለች።

ካርታን ለኃያልነት ማስመስከሪያ መሣሪያነት የተጠቀሙ አገራት በርካታ ቢሆኑም እንደ ጀርመኑ ናዚ ካርታን ያለማቋረጥ እያቀያየረ፣ በጥበብና ያለይሉኝታ የተጠቀመበት አገር የለም ይባላል። የጀርመን ጂኦፖለቲካ ጠበብቶች ሕዝባቸው ለካርታ መረጃ የሚሰጠውን አመኔታ ሲረዱ ቀጣይ ዕቅዶቻቸውን በካርታ አማካይነት ነበር እየቀሸሩ የሚያቀርቡት።

በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የሶቪየት ሕብረት ከምዕራባውያን አገራት በላቀ ሁኔታ ግዙፍና አስጊ ሆና ትታይ ዘንድ ጥራለች። ለምሳሌ በ1946 በታይምስ መጽሔት ላይ የሶቪየት ሕብረት ካርታ ታትሞ ነበር። የተጠቀሙት ደማቅ ቀይ ቀለም ሲሆን ኮሚኒዝም እንደ ሠደድ እሣት በመላው ዓለም እየተቦገቦገ የሚዳረስ እንዲያስመስል ታቅዶ ነበር።

ማፕቲቪዝም

ሰዎች ከጽሑፍ ስሕተት ይልቅ በካርታ ሳቢያ ለሚከሰት ስህተት ታጋሽና ይቅር ባይ ናቸው። ካርታ በባለሙያና በኃላፊነት የሚዘጋጅ ታማኝ የመረጃ ምንጭ ነው ብለው ያምናሉና። ይህ የዋህ ዕምነት ደግሞ ሆን ብለው ካርታን በፕሮፓጋንዳ መሣሪያነት መጠቀም ለሚሹ አመቺ በር ከፍቶላቸዋል። አሁን አሁን ቴክኖሎጂው የካርታ ሥራን እያቀለለው መጥቷል። በማናቸውም የካርታ መደብ (basemaps) ላይ አዲስ መረጃን (ትክክል ይሁን አይሁን) አክሎ በቀላሉ ማቅረብ ተችሏል።

ያለ ተጨማሪ ሥልጠና ካርታን በድረ ገጾችና ሶሻል ሚዲያ በቀላሉ ማሰራጨትም ቀላል ነው። በውጤቱም በርካታ ማፕቲቪስቶች (የካርታ አክቲቪስቶች) ተፈጥረዋል። እንደምናየው ማኅበራዊ ሚዲያው ካርታን ሲጠቀም የግጭት ወይንም የሁነት መገኛ መረጃን በትክክል ለማመላከት ብቻ አይደለም። አንዳንዴም የድንበር ይዞታን አፋልሶ ያቀርባል። አወዛጋቢ ካርታዎች ሊያስከትሉ የሚችሉት ጉዳት ከፍተኛ ሲሆን ያደጉ አገራት ጭምር የተፈተኑበት ነው።

ድንበርን ያፋለሰ ካርታ የማኅበረሰብን የልብ ትርታ በቀላሉ ስለሚነካ መዘዙ ቀላል አይሆንም። ለዚህም ይመስላል በህንድ አገር ካርታን ሆን ብሎ ለሚያዛባ ግለሰብ እስከ 15 ሚሊዮን ሩፒና ሰባት ዓመት ድረስ የሚያሳስር ቅጣት የተደነገገው። በአሜሪካም ሆን ብሎ ካርታ አሳስቶ ያቀረበ ግለሰብን እስከ 90 ቀናት በእስራት እንደሚያስቀጣ ሕጉ ይደነግጋል።

በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አመፁ ወቅት (በተለይም ከ2006 ዓም እስከ 2010 ዓም) ማኅበራዊ ሚዲያው በብቃት ከተጠቀማቸው የመረጃ ዘርፎች መሃል አንዱ ካርታ ነበር። በወቅቱ አያሌ ካርታዎች በሚዲያው ተንሸራሽረው የነበረ ቢሆንም የስድስት ካርታዎች ባሕሪያትን ብቻ እንመልከት። 

ሀ. ሚስጥራዊው “የታላቋ ትግራይ” ካርታ።

ሕወሓት 1968 ዓም ስለ ትግራይ ሪፐብሊክ ማኒፈስቶ ሲያዘጋጅ የክልሉ ወሰን በወቅቱ ከነበረው የጠቅላይ ግዛቱ መጠንና ቅርጽ የተራራቀ ነበር። አንድም በበጌምድርና ወሎ የሚገኙ አንዳንድ ሥፍራዎችን በማከል የምዕራብ ወሰኑን እስከ ሱዳን ድንበር ሲያደርሰው፣ ሁለትም በምሥራቅ ወሰኑ አፋርን አቋርጦ ከቀይ ባሕር ወደብ አሰብ ድረስ ያመጣዋል (ምስል 1)።

ኢሕአዴግ ሥልጣኑን ከተረከበ በኋላ በ1986 ዓም የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ክልሎች ካርታ ላይ የትግራይን ምዕራብና ደቡብ ወሰን የሪፐብሊኩን ዕቅድ ሲተገብረው የቀይ ባሕር ወደብን ዕቅድ ግን አልተተገበረም ነበር።

እንደውም ብዙ አይነገር እንጂ በስተምሥራቅ በኩል ቀድሞ ከነበረው የጠቅላይ ግዛቱ ይዞታ ተቀንሶ ለአፋር ክልል ተላልፎ ተሰጥቷል። ምናልባትም ኤርትራ ሉዓላዊ አገር መሆኗ የአሰቡን ወደብ ባለቤትነት ዕቅድን በማምከኑ ይመስላል። ቀሪው አካባቢም ለሠፈራ፣ ለኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታም ሆነ ለድንበር ተሻጋሪ እንቅስቃሴ አያመችም። የምዕራቡን አቅጣጫ ዕቅድ ማስፈጸም ግን በርካታ ጠቀሜታ ነበረው፤ ሕዝብን ማስፈር የሚያስችል ለም መሬት መሆኑና ወደ ሱዳን የሚያገናኝ ኮሪዶር መሆኑ።

ሆነም ቀረ በማኒፈስቶው ወቅት የተሰራው ሚስጥራዊው የታላቋ ትግራይ ካርታ ለተቃዋሚዎች አመቺ በትር ሆኖ ለ27 ዓመታት አገልግሏል። ማኅበራዊ ሚዲያው ለፕሮፓጋንዳ የተጠቀመው ሚስጥራዊውን የማኒፌስቶውን ካርታ ብቻ አልነበረም። እንዲያውም የተለያየ አይነት የተጋነኑ የ “ታላቋ ትግራይ” ካርታዎችን (ምስል 2) በማምረትና በማሰራጨት ነበር የሕዝቡን ቁጣና ቁጭት ያባባሱት።

በምስል 1 ላይ እንደሚታየው የፕሮፓጋንዳው ካርታ መጠን የማኒፌስቶውን የስፋት መጠን በእጥፍ አሳድጎት ነበር።
ምስል 1፡ የትግራይ ካርታ በለውጥ ሂደት።
ምስል 1፡ የትግራይ ካርታ በለውጥ ሂደት። Source: D.Kassahun
ለ. በሚስጥር ለሱዳን “የተሠጠው”መሬት ካርታ።

ኢትዮጵያ ከሱዳን 744 ኪ.ሜ.፣ ከደቡብ ሱዳን 883 ኪ.ሜ.፣ በድምሩ 1623 ኪ.ሜ. ድንበር ትጋራለች። አወዛጋቢው አል ፋሻቃ ሥፋቱ ወደ 260 ካሬ ኪ.ሜ. (ምስል 2) ሆኖ “የዳቦ ቅርጫት” መሰኘቱ የመሬቱን ለምነት አመላካች ነው። እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1902 ሱዳንን በቅኝ ግዛት ከምታስተዳድረው እንግሊዝ ጋር የተጀመረው የድንበር ማካለል ዛሬም አልተጠናቀቀም።

በአገር ደረጃ የድንበር ግጭት ባይከሰትም በድንበርተኛ ገበሬዎች መሃል ግን በተለያየ ጊዜ ግጭቶች ተከስተዋል። በ1999 ዓም በአቶ መለስ ዜናዊና በኦማር አል በሽር ስምምነት የሁለቱ ሐገራት ሕዝቦች በጋራ አካባቢውን የሚያለሙበት ምስጢራዊ ቀመር ነድፈው በቀጣይ ድንበር ማካለሉን እንደሚገፉበት ተስማሙ ተባለ። ጉዳዩ በሚስጥር በመያዙ ለተለያዩ መላምቶችና ተቃውሞ በር ከፈተ።

የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ተቋቋመ። ዓላማውም “የወያኔ/አሕአዴግ መንግሥት ለሱዳን የሰጠውን ለም የአገራችን ድንበር መሬት በተመለከተ የሚፈጽመውን ድብቅ ሤራ እየተከታተለ በማጋለጥ የኢትዮጵያ ሕዝብና የዓለም ኅብረተሰብ እንዲያውቀው” እንደሆነ ተገለጸ። 

ተቃዋሚዎችና አክቲቪስቶች ለሱዳን በሚስጥር ተሰጠ በሚባለው የመሬት መጠን ላይ ልዩነቶች ነበሩ። ሥፋቱ 1,600 ካሬ ኪ.ሜ. ነው የሚሉ አሉ። ምናልባትም የጋራ ድንበሩን ርዝመት ልክ እንደ ሥፋት መጠን ቆጥረውት ሊሆን ይችላል። ፕሮፌሰር አል ማርያም መጠኑን ወደ 250 ካሬ ኪ.ሜ. ዝቅ ቢያደርገውም በተሳሳተ ሥሌት 600,000 ኤከርስ ነው ብሏል። ሆኖም ግን 250 ካሬ ኪ.ሜ. ወደ ኤከርስ ሲቀየር ከ62 ሺህ በታች እንደሚሆን እሙን ነው።

ለፕሮፓጋንዳው ዘመቻ የተዘጋጀው የተጋነነ ካርታ (ምስል 3) የሚያስተላልፈው መልዕክት በመላው የኢትዮ-ሱዳን የድንበር መስመር ከመተማ እስከ ቱርካና ሐይቅ ዳርቻ ድረስ የእኩልዮሽ ሽግሽግ “ሥጦታው” የተካሄደ አስመስሎት ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት የሚስጥሩን ሥምምነት ገልጦ ለሕዝብ ከማስረዳት ይልቅ ክሱን በድፍን ሊያስተባብል መሞከሩ የጉዳዩን አወዛጋቢነት አባባሰው እንጂ አላረገበውም። 

 

ምስል 2፡ ኦፊሴላዊው የኢትዮ-ሱዳን አወዛጋቢ ሥፍራ ካርታ

ምስል 3፡ የፕሮፓጋንዳው የኢትዮ-ሱዳን ሚስጥራዊ ሥጦታ ካርታ


 

Pic 2
Source: D.Kassahun
 ሐ. የዋልድባ ገዳም “የታረሰበት” ካርታ።

በስኳር ምርትና ከአፍሪካ አገራት የቀዳሚውን ሥፍራ እንድንይዝ ያስችለናል በሚል ራዕይ በኢትዮጵያ ሊገነቡ ከታቀዱት 11 የስኳር ፕሮጄክቶች አንዱ የወልቃይት ልማት ነው። አድራሻው በዋልድባ ገዳም አካባቢ ሆኖ በ2004 ዓ.ም ሲጀመር የዛሬማና የቃሌማ ወንዞች ላይ የመስኖ ግድብ በመገንባት የሸንኮራ እርሻ አልምቶ የስኳር ፋብሪካን ለመትከል የታለመ ነው።

ፕሮጄክቱ እስከ 50 ሺህ ሰራተኛ ከገዳሙ ቅርብ ርቀት ላይ ያሠፍራልና በመላው ዓለም ባሉ ኢትዮጵያውያን ቁጣ ቀስቅሶ “የዋልድባ ገዳምን እናድን” በሚል ተቃውሞ ተካሄደ።

ከተመሠረተ ከ1,600 ዓመታት በላይ ባስቆጠረው ገዳም በውስጡ ከ3,000 በላይ መናንያን እንደሚኖሩበት፣ ስቋር፣ አበረንታት፣ አባ ነፃ፣ ደሻል፣ ቤተ ሚናስ፣ የሚባሉ ገዳማት ያሉበት እንደሆነ፣ ከሃያ ሽህ በላይ ገበሬዎች የመፈናቀል ዕጣ እንደሚደርሳቸውና በገዳሙ የተቀበሩ የቅዱሳን አጽም ተቆፍሮ እየተጣለ እንደሆነ የሚገልጽ ቅሬታ በማኅበራዊ ሚዲያው ተሰራጨ።

የመንግሥት ባለሥልጣናት “ኃይማኖትን ለፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ መሣሪያ አድርጎ የመጠቀም አባዜ ነው” ቢሉም ተቃውሞውን ቋያ ማብረድ አልቻሉም። “በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ መንግሥት ከገዳሙ ሆነው የፕሮጄክቱን ተቃውሞ የመሩ ናቸው ብሎ ጥቂት ቀሳውስትን አስሮና አፈናቅሎ ነበር።

የወልቃይት ስኳር ልማት ተቃውሞ ዘመቻ በካርታዊ ፕሮፓጋንዳ ሲታገዝ የተወሰነ ግነትም ነበረው። በተለያዩ የካርታ ድረ ገጾች (Google Map, Google Earth, Wikimapia) ላይ የሠፈረው የዋልድባ ገዳም ኮርዲኔት (13042’N, 37045’E) የተሣሣተ ነበረ። ገዳሙ ያረፈበት ሥፍራ 13062’N 37057’E ነበር። የተሣሣተው ኮርዲኔት የወልቃይት ፕሮጀክት ያረፈበትን ሥፍራ እጅግ ለገዳሙ ስለሚያቀርበው ዜጎችን የበለጠ ሥጋት ላይ የሚጥል ነበር።

ፕሮጄክቱ የሚገነባው ከገዳሙ 23 ኪ.ሜ. ርቆ ሲሆን በተሣሣተው ካርታ ርቀቱ 5.6 ኪ.ሜ. ብቻ ነበር። ይህንን የተሣሣተ ኮርዲኔት ካርታ በርካታ ሚዲያዎች (ቪኦኤ የአማርኛው ፕሮግራምን ጨምሮ) በሰፊው አንሸራሸሩት። የመንግሥት ሚዲያና የአይጋ ፎረም ድረ ገጽ ደግሞ ፕሮጀክቱ ከዋልድባ ገዳም ይዞታ ውጪ ስለሆነ የመነኮሳቱ መንፈሳዊ ተግባርን እንደማይነካ ለማሳመን ብዙ ጥረው ነበር።

ዘሩ ጨርቆስ የተባለ ግለሰብ ትክክለኛውን የካርታ ኮርዲኔት ለማሳየት እንዲያስችለው የተለያዩ ቪዲዮዎችን፣ የመንግሥት መረጃን፣ እና የጉግል ካርታን በድረ ገጹ ተጠቅሟል። በተለይም ስለዋልድባ በቪዲዮ የተዘመሩ የኦርቶዶክስ መዝሙሮች ከሥፍራው ስለተቀረጹ ከበስተጀርባው (background) የሚገኙ የምድር ገጾችና የደን ሽፋኖች በማስረጃነት ቢጠቀምም ብዙም ትኩረት አላገኘም ነበር። ይልቁንስ ሕዝባዊ ተቃውሞው ተፋፋመ።

መ. የራስ ዳሸን ተራራና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት “የተሰረቁበት” ካርታ። 

ሌላው ሕዝቡን ለተቃውሞ ያነሳሳው በተማሪዎች የመማሪያ መጻሕፍት ላይ የሰፈረ ሐሰተኛ የሥነ ምድራዊ መረጃ ነው። በስድስተኛ ክፍል የእንግሊዝኛ መማሪያ መጽሐፍ (ገጽ 148) ላይ የሰፈረው ወደ አማርኛው ሲተረጎም “ራስ ዳሸን በስሜን ተራራዎች የሚገኝ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራራ ነው። የሰሜን ተራራዎች በክልል አንድ (ትግራይ) ውስጥ ይገኛል።…..” ይላል።

በተጓዳኝም በቱሪዝም ኮሚሽን አማካይነት በእንግሊዝኛ ቋንቋ በተዘጋጀ ቪዲዮ (Infomercial) ላይ “የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት በትግራይ ይገኛሉ” ሲል ለመላው ዓለም ይፋ አደረገ። ሁለቱም መረጃዎች ስህተት እንደነበሩ በቀላሉ ማየት ይቻላል (ምስል 4)።

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት “መሰረቅ” ዜና እንደተሰማ ከራስ ዳሸን ተራራ ቅሌት ጋር ተዳምሮ ቁጣው በማኅበራዊ ሚዲያ መረብ በአገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተዳረሰ። ከባህር ወለል 4,550 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝውና ደረጃውም ከኢትዮጵያ አንደኛ ከአፍሪካ ዘጠነኛ የሆነው ራስ ዳሸን ተራራ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት በተመዘገበው የሰሜን ብሔራዊ ፓርክ የአማራ ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው።

“ከሰሜን ጎንደር ተሰርቆ ለ25 ዓመታት ሙሉ ትግራይ ክልል ገብቶ ነበር” ተባለ። “አንድ ትውልድ በሥነ-ምድር ሳይንስ በውሸት ታሪክ እንዲታነጽ አደረገ”፣ “በታዳጊ ተማሪዎች ጭንቅላት ላይ ሆን ተብሎ መረጃን ለማዛባት ታቅዶ የተካሄደ ደባ ነው”፣ ወዘተ ተብሎ ክስና ትንተና ቀረበ።

ፍስሃ ተገኝ የተባለ የስፖርት ጋዜጠኛ በትዊተር "አይጫንም እንጂ ወንዝ በመኪና፣ መቀሌ ነበሩ አባይና ጣና" ሲል ጻፈ። አበበ ገላው በፌስ ቡክ ሕወሓት መላው አገሪቱን በበላይነት ተቆጣጥሮ ሳለ የትግራይን “ታላቅነት” አጋኖ ለማቅረብ መሞከሩ እንቆቅልሽና የናዚ ፓርቲን ልምድ በኢትዮጵያ ለመድገም አስቦ ነው ሲል ከሰሰ።
pic 3
ምስል 4፡ የራስ ዳሸን ተራራና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ትክክለኛ አድራሻ። Source: D.Kassahun
ሠ. የአማራ ክልል መሬት በቤንሻንጉል ክልል “የተነጠቀበት” ካርታ።

በአስረኛ ክፍል የሲቪክና ሥነ ዜጋ መማሪያ መጽሐፍ ገጽ 24 ላይ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአማራን ክልል ከሱዳን ድንበር መነጠሉ (ምስል 5) ሲታወቅ ሌላ በማኅበራዊ ሚዲያ የቁጣ ወጀብ ተቀሰቀሰ። መንግሥት “በየዋህነት የተፈጠረ ሥህተት በመሆኑ” ይቅርታ እንዲደረግለት ጠየቀ። ይህ የተሣሣተ ካርታ በተለያየ የቴሌቪዥን ሥርጭት ላይ እንደማጀቢያ (background) ማገልገሉ ሆን ተብሎ የተከናወነ እንደሆነ ብዙዎች ተናገሩ።

ሲያብራሩም፡ ሕወሓቶች ለቅማንት ሕዝብ ይገባዋል ብለው በራሳቸው ውሳኔ ከአማራ ክልል መሬት ላይ ቆረሱ፣ ከቤንሻንጉል ክልል ጋር ደመሩት፤ የአማራ ክልል ከሱዳን ጋር የጋራ ድንበር እንዳይኖረው አደረጉ፣ ይህንን አዲስ የቤንሻንጉል ክልል ከትግራይ ክልል ጋር እንዲዋሀድ ዓለሙ፤ የመገንጠል አጀንዳን አስፈጽመው የትግራይን ክልል እስከ ጋምቤላ ጠርዝ ድረስ እንዲዘልቅ በሚስጥር አሰሉ፤ በውጤቱም ለም የሱዳን መሬቶችንና ሕዳሴውን ግድብ ለመውሰድ ቀመሩ ተብሎ ክስ ቀረበ፤ የሕዝብ ቁጣንም አጋጋለ።

ለዚህ ጽሑፍ ዝግጅት ካርታው ላይ በተደረገ ምርመራ አዲሱ የቤንሻንጉል ካርታ ቁመቱ ረዝሞ፣ ወርዱ ጠቦ፣ የቆዳ ሽፋኑ ደግሞ በ11,500 ካሬ ኪ.ሜ. ቀንሶ ተገኝቷል። በካርታው ላይ ለስትራቴጂ ጠቀሜታ ሲባል ብዙ የቀመር ጨዋታ እንደተካሄደበት ያሳብቃል። ይሆን እንጂ ብዙዎች ልብ ያላሉት ነገር ይህ የተሳሳተ ካርታ በመማሪያ መጽሃፉ ላይ ብቻ የተከሰተ አልነበረም።

ጆን ያንግ የተባለ ታሪክ አጥኚና አረጋዊ በርሄ ለፒኤችዲ መመረቂያው በጻፉት የሕውሓት ታሪክ ላይ ይህንን ካርታ ተጠቅመውበት የነበረ ሲሆን ሁለቱም መረጃውን አገኘን ያሉት ከዩኤንዲፒ ነው ብለዋል።
pic 4
ምስል 5፡ በ10ኛ ክፍል መማሪያ መጽሐፍ ውስጥ የተካተተው ካርታ የቤንሻንጉል ጉሙዝን ከትግራይ ክልል ሲያዋስነው የአማራን ክልል ደግሞ ከሱዳን ድንበር ነጥሎታል። ካርታው በቴሌቪዥን ማስተዋወቂያ አባሪ (background) ሆኖም አገልግሏል። Source: D.Kassahun
ረ. “መሬት ሊወር” ያቀደው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ካርታ።

የሕዝባዊ እንቅስቃሴው ሂደት ማርሹን የቀየረው የአዲስ አበባ ከተማ ማስፋፊያ ማስተር ፕላን ይፋ ሲሆን ነበር። ሲዘጋጅ በኦሮሚያ ክልል በ17 አጎራባች ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 36 ከተሞችን እና ገጠራማ ሥፍራዎችን ከአዲስ አበባ ሜትሮፖሊታን ጋር በኢኮኖሚ ለማስተሳሰርና እድገቱን ለማፍጠን ይረዳል ተብሎ ነበር። ዕቅዱ ያካባቢውን ሕዝብ ይሁንታና ፍትሐዊ ካሳን አላካተተምና “ሰይጣናዊ ማስተር ፕላን”፣ “የኦሮሞ ገበሬን የሚያፈናቅል”፣ “የመሬት ወረራ”፣ ወዘተ የሚል ሥያሜ ተሰጠው።

በሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተጀመረው ተቃውሞ ወደ ክልሉ ሕዝብና ዳያስፖራ ተዛመተ። ለሳምንታት በዘለቀው አድማ ከመቶ በላይ ሰዎች ተገለው በሺዎች የሚቆጠሩ ታሰሩ። የማስተር ፕላኑ ካርታ በራሱ ተቃውሞን ለማስነሳት በቂ የነበረ ቢሆንም በአንድም ይሁን በሌላ የተጋነኑ ካርታዎችም ተበጅተውለት ነበር።

ለምሳሌ የፕላኑን የሽፋን መጠን እስከ 125 ኪ.ሜ. አርዝመው የአምቦ ከተማን ጭምር እንዲጠቀልል በማድረግ የሕዝቡን ቁጣ የበለጠ ማናር ችለዋል። 

ከለውጡስ በኋላ?

ከለውጡ በኋላ የተስተዋለው ነገር የካርታ ፕሮፓጋንዳው የጋራ ዒላማ የመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሳይሆን ባመዛኙ አንዱ ብሔር ከሌላው ብሔር የሚያጋጭ ሆኗል። በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ካርታ የብሔርተኞች መሳሪያ ሆኗል፣ ለወደፊቷ ኢትዮጵያም ዕዳ እያስቀመጠ ሄዷል። አባባሉን በመረጃ ለማስደገፍ ከለውጡ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ የተንሸራሸሩ ሁለት የፕሮፓጋንዳ ካርታዎችን ብቻ እንመልከት። 

በምስል 6ሀ እና 6ለ ላይ የተጋነኑት ካርታዎች ጣጣ የሚመጣው በአክቲቪስቶች ቆስቋሽነት እኒህን ካርታዎች ወደ መሬት ለማውረድ ሲሞከር ነው፡_ልክ እንደ ተጠመደ ፈንጂ ። በሁለቱ ካርታዎች የፍላጎት ሥፍራ መነራረብ ሳቢያ በ58,178 ካሬ ኪ.ሜ. ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ከሚንተከተከው የፕሮፓጋንዳው አውድማ ይጣዳሉ (ምስል 6ሐ)።

ይባስ ብሎ ሁለቱ የፕሮፓጋንዳ ካርታዎች ሊናጠቁ የሚያስቡት መሬት አንዳቸው ካንዳቸው ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን አልፎ ተርፎ የቤንሻንጉልና የአፋር ክልል ውስጥ ያሉ መሬቶችን ጭምር ነው።

በግጭት አውድማው ቀጣና ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች እንኳንስ ለትውልድ የሚተላለፍ ዘላቂ የኢኮኖሚና የተፈጥሮ ሃብት ኢንቨስትመንት ላይ ሊያተኩሩ ቀርቶ የለት ተለት ኑሯቸውን በሰቀቀን እንዲያሳልፉ ያደርጋቸዋል። በውጤቱም ዜጎችን ለአክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ቀጣይ ዒላማ ዳርጎ ለፀብና ጦርነቶች የበለጠ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።

 

ሀ.የፕሮፓጋንዳው የኦሮሚያ ክልል ካርታ

ለ.የፕሮፓጋንዳው የአማራ ክልል ካርታ

ሐ. በፕሮፓጋንዳዎቹ ካርታዎች ሊፈጠር የሚችል የግጭት አውድማ


pic 5
ምስል 6፡ የኦሮሚያና የአማራ ክልል የፕሮፓጋንዳ ካርታዎችና ሊፈጥሯቸው የሚችሉት አወዛጋቢ አካባቢዎች። Source: D.Kassahun
ምንጭ፡ http://oromoliberationfront.net/

ምንጭ፡ http://mereja.com/

በካርታዊ ጥንቅር የተገኘ ውጤት


 

ሌላው ችግር የካርታ ማጠናቀሪያው ቴክኖሎጂ በጣም አድጎ እውነተኛውን ከተሣሣተው መለየት አዳጋች ሆኖ መምጣት ነው። በጽሑፍና ንግግር መረጃ ውስጥ የሚከሰት ስህተትን የመጠርጠር ልምድ ስላለን መጠነኛ የማጣራት ሙከራ እናደርጋለን። በካርታ ላይ የሚኖር የመረጃ ግድፈትን ለመለየትና ለማወቅ የሚያስችል ልምድ ስለሌለን ሊከሰት የሚችለው ጣጣ ከባድ ነው።

በአሁኑ ወቅት ዓለማችንም ሆነ አገራችን በተጻራሪ ኃይሎች ተወጥራለች። አንደኛው globalism (ሰዎች በነፃነት ተዘዋውረው የመኖርና የመሥራት ዕድልን የሚያመቻች)፣ ሁለተኛው ደግሞ nationalism ወይንም ብሔርተኛ (አገራትና ጎሳዎች ከሌላው የሚለያቸውን አጥር የሚያጥሩበት ሂደት) ነው። በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ እየጎመራ ያለው የብሔረተኛው ቡድን ነው። ብሔረተኞች የኔ መሬት ነው ብለው የሚያጥሩት አጥር ሃቅን ብቻ ተመርጉዞ አይደለም።

ውስብስብና የሆነውን የኋላ ታሪክን በማጣቀስ ለራስ የሚጠቅመውን መረጃ ብቻ ነቅሶ በማውጣት “የኔ” የሚሉትን የመሬት መጠን በማግዘፍ ጭምር ነው። በተጋነነ ካርታ ሣቢያ የሚፈጠረው ችግር ከክልል–ክልል ወሰን ላይ ብቻ የታጠረ አይደለም፡ ከዞን–ዞን እና ከወረዳ–ወረዳ ጭምር ይዘልቃል። ለዚህ ደግሞ ሩቅ ሳይኬድ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩበትን የደቡብ ክልል ማየት ብቻ ይበቃል። 

ታዲያ የካርታ መረጃን እንዴት እንጠቀም?

ከላይ በቀረቡት ናሙና ካርታዎች ለመረዳት እንደሚቻለው የሕዝባዊ አመፁን በማቀጣጠል ረገድ እውነተኛና የተጋነኑ እንዲሁም የተሳሳቱ ካርታዎችን ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ለለውጡ እስከጠቀመና ለበጎ ዓላማ እስከተደረገ ድረስ ሁሉንም ዓይነት ካርታ መጠቀማችንን “ደግ አደረግን” ካልን ሥህተት ነው። የካርታ ማጋነኑ ልምድ አድጎ እየተወሳሰበ ይሄድና ከፍ ያለ ዋጋ ከሚያስከፍለን ደረጃ ሊያደርሰን ይችላል። 

በጥቅሉ ሲታይ አክቲቪስቶች እያንሸራሸሯቸው የሚገኙት ካርታዎች ደረጃቸው ከመደበኛ ካርታ በእጅጉ ያነሰ፣ ከካርቱን ሥዕል ደግሞ በመጠኑ ከፍ ያለ ነው ያስብላል። ስለትክክለኛነታቸው ጭራሽ ማጣራት የሚካሄድባቸው አይመስልም። ለካርታ የሚያስፈልጉ ወሳኝ አባሪ መረጃዎች (ገላጭ ርዕስ፣ ልኬት/ሚዛን፣ አቅጣጫ ጠቋሚ፣ የመረጃ ምንጭ፣ የተዘጋጀበት ጊዜ፣ ወዘተ) አይስተዋሉም።.

ባጭሩ በማኅበራዊ ሚዲያ እየተንሸራሸሩ ያሉት ብዙዎቹ ካርታዎች ጮሆ በማስጮህ የደም ፍላትን መጨመር እንጂ አዲስ ብርሃን ፈንጥቀው መሰረታዊ የባሕሪ ለውጥን የሚያጎናጽፉ አይመስሉም።

በዛሬይቱ ኢትዮጵያ በርካታ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አንዱን የማኅበረሰብ ክፍል ከሌላው የሚለየውን የወሰን ደንበር በማስፋት ወይንም በማጥበብ ሥራ ላይ ተጠምደዋል። ችግሩን የሚያጎላው ደግሞ ኢትዮጵያዊ በመሬቱና በሚስቱ ድርድር አለመቀመጡ።

ልክ እንደ ጠመንጃ ሁሉ ካርታ ጠቃሚም ሆነ ጎጂ መሳሪያ ነው። ወሳኙ ነገር የተጠቃሚው አያያዝ፣ ዒላማ አመራረጥና ግብ ነው። የዚህ ጽሑፍ ዓላማም ካርታን በጥቅሉ ለማወደስ ወይንም ለማውገዝ ሳይሆን ዜጎች ልክ እንደ ጽሑፍ መረጃ ሁሉ ለካርታ መረጃም ጤናማ ጥርጣሬ እንዲኖራቸው ለማስገንዘብ ነው።

አሁን አገሪቱ ባለችበት ሁኔታ ሥርዓት ያልተበጀለት የካርታ ፕሮፓጋንዳና አፀፋ የካርታ ፕሮፓጋንዳ ከፍተኛ አደጋ አለው። አወዛጋቢ መረጃን በመልቀቅ የበርካታ ተመልካች/አንባቢን ዕይታ ለመሳብ የሚደረግ ፍላጎት በእጅጉ ንሯል። ምክንያቱም ብዙ ዕይታ ማለት ብዙ ብር ማፈስ ነውና።

መረጃ ከተጠቃሚ የሚደርሰው (share የሚደረገው) ከጓደኛ፣ ከቤተሰብ አባል፣ ከሥራ ባልደረባ፣ ከሚያምነው አክቲቪስት ወይንም ከሚያደንቀው ዝነኛ ሰው (celebrity) ተቀባብሎ ስለሆነ በኅብረተሰቡ ውስጥ ብዙ የመንሸራሸር ዕድል ያገኛል። “viral ሆነ” እንደሚባለው።

በአንድ ሥፍራ የሚፈጠር የድንበር ይገባኛል ወሬ በካርታ ሲታጀብ ጉዳዩ ወደ “አወዛጋቢነት” ደረጃ ያድጋል። ለቀጣይ ውጥረትና ግጭት መደላድል ይፈጥራል። ይህንን ካርታ ይዞ ሜንጫም ሆነ ቆንጭራ፣ ቀስትም ሆነ ክላሽ ላነገበ ሥራ አጥ ወጣት የፀብ 'መንጃ ፈቃድ” ሆኖ ያገለግላል፤ ያጀግናል፤ ለሚወሰደው ማናቸውም የ“ፍትሐዊነት” እርምጃ ሥንቅ ይሆናል፤ ወዘተ። 

መረጃን ሳይመረምሩ መጠቀም ዋጋ ያስከፍላል። በተለይ መንግሥት ለካርታ እየሰጠ ያለው አነስተኛ ግምት ሊሻሻል ይገባል። ከ50 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች፣ በርካታ የምርምር ተቋማት፣ ኃላፊነት ያለው የካርታ ሥራ ኤጀንሲ ባለበት አገር በመማሪያ መጽሐፍ ላይ የቤንሻንጉልን ክልል እንደ ወንዝ ጠልፎ 286 ኪ.ሜ. አጓጉዞ ከትግራይ ክልል ዳርቻ ማድረስ ዕዳው የኛው የኢትዮጵያውያን ነው ብለን ልናቃልለው እንችላለን።

ሆኖም ግን የምሥራቁ የአገራችንን ድንበር ሙሉ ለሙሉ አጥፍቶ መላውን የሶማሊያ አገር አዳብሎ የኢትዮጵያ ካርታ ነው ብሎ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ ገጽ ላይ ለመላው ዓለም ይፋ ማድረግ (ምንም እንኳ በወቅቱ መንግሥት ይቅርታ ቢጠይቅም) ኦፊሴላዊ ጦርነት ከማወጅ አይተናንስም።

ቢያንስ መንግሥት ከሁለት ዐሥርት ዓመታት ቀደም ብሎ በባድሜ ውዝግብ ወቅት ለሁለት ዓመታት ከኤርትራ ጦርነትን ማካሄዱ ይታወሳል። ለአልጀርሱ ሥምምነት ይረዳ ዘንድ በእጁ የሚገኙ ታሪካዊ ካርታዎችን አደራጅቶ ማቅረብ ተስኖት ቦታዎቹን መነጠቁ ለካርታ ያለው ግንዛቤ ሊቀየር በተገባ ነበር። ሆኖም ዛሬም ሌላ ቀን ነው።

በዘላቂነት ካርታ-ወለድ ችግርን ለማስወገድ በሁለት ዘርፎች መሠራት አለበት- የአጭርና የረዥም መፍትሔ። በአጭሩ ጊዜ የካርታ ባለሞያዎችና ተጠቃሚዎች በፈቃደኝነት የሚሳተፉበት የካርታ መረጃ መገምገሚያና ማበልጽጊያ የውይይት መድረክ በመፍጠር ሲሆን፣ በረዥም ጊዜ መፍትሔ ደግሞ በትምህርት ካሪኩለሙ ላይ በመስራት ነው። ችግር ፈቺ መሆን አለበት።

ያለማጋነን የሐሰተኛ መረጃ የዘመኑ አስጊ ችግር ሆኗልና ካሪኩለሙ በጥልቅ ሊመረምረው፣ ሊያርመውና ሊያመክነው መዘጋጀት አለበት። ማናቸውም መረጃ ለግነትና ለውሸት ሊጋለጥ እንደሚችል ታምኖ የማጣሪያ ሥርዓት ክህሎት ሊዳብር ይገባል፤ በካርታም ላይ ቢሆን።

በመቀጠልም፡ የካርታ አቅም ቦታን ከቦታ ነጥሎ ለማሳየት ብቻ ሳይሆን ሕዝብን ከሕዝብ የማቆራኘትና የጋራ ሕልም የመፍጠር ዕምቅ ጉልበት እንዳለው መንግሥትም ሆነ ማናቸውም ተጠቃሚ መገንዘብ ይኖርበታል። የካርታ ቴክኖሎጂውን ትሩፋት በማበጎልበት ረገድም መሪ ተዋናይ ሊሆኑ ይገባል። ዛሬ ነገ ሳንል ለበጎ ዓላማ እንጠቀምበት።

 ዋቤዎች

 4. Young, J. (1997). Peasant Revolution in Ethiopia: The Tigray People's Liberation Front, 1975-1991. Cambridge University Press

 5. Berhe, A. (2009). A political history of the Tigray People's Liberation Front (1975-1991): Revolt, ideology and mobilisation in Ethiopia

 6. UNDP Emergencies Unit፣ 1996

 

 

 

 

 

 

 

 


Share

Published

Updated

By Daniel Kassahun (PhD)

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service