የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ በወሰዳቸው የፓርቲ ዲሲፕሊን እርምጃዎች ሶስት ከፍተኛ የአመራራ አባላቱን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት አግዷል።
ፓርቲው ያገዳቸው የአመራራ አባላት አቶ ለማ መገርሳ፣ ዶ/ር ሚልኪሳ ሚደጋና ወ/ሮ ጠይባ ሃሰን ናቸው።
የአገር መከላከያ ሚኒስትር ስልጣን ላይ ተቀምጠው ያሉት አቶ ለማ መገርሳ ከብልፅግና ፓርቲ የእግድ እርምጃ ሊወሰድባቸው የቻለው የፓርቲ ዲሲፕሊን ባለመጠበቅ፣ የአቋምና የአመላከካት ልዩነቶችን በፓርቲ መድረክ ውጪ ማንጸባረቅ፣ ልዩነቶችን ለመፍታት ጥረቶች ተደርገው ከስምምነት ላይ ቢደረስም በፓርቲው መድረክም ሆነ በመደበኛ የሥራ ገበታቸው ላይ ባለመገኘታቸው እንደሆነ ፓርቲው በማጠቃለያ መግለጫው አስታውቋል።
ሁለተኛው ታጋጅ ዶ/ር ሚልኬሳ ሚዳጋም በተመሳስይ መልኩ የአተያይና የአቋም ልዩነቶችን ለፓርቲው ከማቅረብ ይልቅ ከፓርቲው ዲሲፕሊን ውጪ የሆኑ አማራጮችን እንደተጠቀሙና የፓርቲውን ምስጢር ለሌሎች ሃይሎች አሳልፎ በመስጠት የዲሲፕሊን እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተገልጧል።
ወ/ሮ ጠይባ ሃሰን በበኩላቸው በቅርቡ በምዕራብ አርሲ ተከስቶ ከነበረው የሰላም መደፍረስ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች፣ የፓርቲውን ምስጢር ለሌሎች በማቀበል፣ በፓርቲው መድረኮችም ሆነ በመደበኛ ሥራቸው ላይ ባለመገኘታቸው የእገዳ ዲስፒሊናዊ እርምጃ እደተወሰደባቸው ተነግሯል።
ይኼው በኮንፈረሱ የተላለፈው የእገዳ እርምጃ ለፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ቀርቦ ይሁንታን እንደሚያገኝ ይጠበቃል።
ውሳኔው በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከጸደቀ ከፓርቲ ዲሲፕሊናዊ እርምጃ ባሻገርም የሕጋዊ እርምጃ ምልከታዎችም እንደሚከተሉ ተጠቁሟል።
የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ በወቅታዊ አገራዊና ክፍለ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መምከሩንም የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ገልጠዋል።
አክለውም፤ ኮንፈረንሱ 'ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ ከውጭ ሀይሎች ጋር በመተባበር የታላቁን የኢትዮጵይ ህዳሴ ግድብ ግንባታን እና በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ ከውጭ ከውጭ ሀይሎች ጋር ተባብረው እየሰሩ መሆኑን ተመልክቷል' ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኮምቤን ጨምሮ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች ትናንት በመከላከያ ሠራዊት አባላት መያዛቸው ተገልጿል።
አልአይን እንደዘገበው አመራሮቹ ስብሰባ ላይ በነበሩበት ወቅት የተያዙ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ በከተማው ሁከት መከሰቱም ገልጿል።
የዞኑ አመራሮች ከክልል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከፌዴራልና ከደቡብ ክልል መንግሥት ጋር ቅራኔ ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል።
የዞኑ ክልል የመሆን ጥያቄ በደቡብ ክልል መንግሥት ተገቢው ምላሽ አልተሰጠውም በሚል ተቃውሞ በክልሉ ምክር ቤት የዞኑ ተወካዮች ራሳቸውን ከምክር ቤት አባልነት ካገለሉ ከስድስት ሳምንታት በላይ ተቆጥረዋል።