በ2013 ምርጫ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ የሌሎች ብሔር ተወላጆች በመራጭነትም ሆነ በተመራጭነት እንዲሳተፉ ሊደረግ ይገባል ሲል የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የምሁራን መማክርት ጉባኤ ጠየቀ።
የምሁራን መማክርት ጉባኤው ለ SBS አማርኛ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የ 2013 ሀገራዊ ምርጫ "ፍትሐዊ፣ አሳታፊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ዜጎች በመራጭነት ብቻ ሳይሆን በተመራጭነትም እንዲሳተፉ የሚያደርግ ምቹ ሁኔታ ሊረጋገጥ ይገባል" ብሏል።
ይህ ሳይሆን ቢቀርና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች ቢሟሉ እንኳን ምርጫው ፍትሐዊ እና ቅቡልነት ያለው ምርጫ ነው ማለት አያስችልም ብሏል መማክርቱ፡፡
" ምርጫ ዜጎች የአንድ ሀገር አካል መሆናቸው የሚረጋገጥበት አንዱ እና ዋነኛው ፖለቲካዊ ሂደት ነው" ያለው መማክርቱ በሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ፣ በዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን እና በአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብት ቻርተር እንደተደነገገው በአንድ ሀገር ውስጥ በምርጫ በመራጭነትም ሆነ በተመራጭነት መሳተፍ መሰረታዊ የሰው ልጆች መብት እንደሆነ አውስቷል።
ይህ ስለሆነም "ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ በማንነታቸው የተነሳ በተለይም በተመራጭነት እንዳይሳተፉ ማድረግ ወይም አለማመቻቸት መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ መሰል የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈፀሙም በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ተቋማት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ግዴታ እና ኀላፊነት አለባቸው" ሲል አፅንኦት ሰጥቷል።
መማክርቱ "ኢትዮጵያ ከደርግ መውደቅ ማግስት የይስሙላ ምርጫ" ማካሄዷን ጠቅሶ "ከአንኳር ጥፋቶች መካከል አንዱ በብሔራቸው ከተሰየሙ ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ዜጎች ሥርዓታዊ በሆነ መልኩ በተመራጭነት እንዳይሳተፉ መደረጉ ነው" ብሏል፡፡
ለዚህ ማስረጃውም " ከአማራ ክልል ውጭ ባሉ የክልል ምክር ቤቶቹ በክልሉ ተወላጆች ብቻ መያዛቸው እና ብዝኃነትን አለማስተናገዳቸው ነው" ሲል ምክንያቱን ገልጿል።
ስለሆነም "በ2013 ምርጫ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ የሌሎች ብሔር ተወላጆች በመራጭነትም ሆነ በተመራጭነት እንዲሳተፉ ሊደረግ ይገባል። በተለይም ገዥው ፓርቲ ብልጽግና የክልል ምክር ቤቶች እውነተኛ ሕብረ ብሔራዊ ፌደራሊዝምን የሚያንፀባርቁ እንዲሆኑ በሚወዳደርባቸው ክልሎች ሁሉ ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ ሕዝቦች በተመራጭነት እንዲወዳደሩ የማድረግ ኀላፊነት አለበት" ሲል በመግለጫው አሳስቧል፡፡
[ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ]