የመዋቅር ለውጥ እንዴት?

*** በክልል ልዩ ኃይል ወይም ሌላ የተደራጀ ታጣቂ ኃይል የሚባል ነገር እንዳይኖር ማድረግ፤ የፖሊስንና የፍትህ መዋቅሩን ወይም የፖሊስ መዋቅሩን ብቻ ከየክልሉ የአስተዳደርና የፖለቲካ ካርታ መዋቅር ነጥሎ በተለየ መልክ በማደራጀት ረገድ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

Dr Girma Awgichew Demeke

Dr Girma Awgichew Demeke Source: Supplied

1.እንደመግቢያ

በየወቅቱ በንፁሀን ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ማንነት ላይ ያተኮረ ጥቃት መቆምያ ያለው አይመስልም። የችግሩ ምንጭ በማንነት/"ዘር” ላይ የተመሰረተ የአስተዳደር መዋቅር እና ከሕወሓት መፈጠርና በተለይም ወደስልጣን መምጣት ጀምሮ የተነዛው (በተለይ በአማርኛ ተናጋሪው ላይ ያነጣጠረ) የጥላቻ ስብከት መሆኑ እራስን ለማታለል ካልሆነ በስተቀር ለማናችንም የተሰወረ አይደለም።

የዚህ የጥላቻ ስብከት መነሻ ከ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ጋር ይያያዛል። ገና የመጀመሪያ ድግሪ እንኳን ያልያዙ ወጣት ተማሪዎች፣ ከእነራሽያና ቻይና አብዮት የወሰዱትን ርዕዮተ ዓለም ከሀገር እውነታ ጋር ሳያዋህዱና ሳያገናዝቡ ተቀብለው የትግላቸው መነሻና (በተለይ እንደህወሀት ዓይነቱ) መዳረሻ አደረጉት።

በዋለለኝ አማካኝነት የብሄረሰብ ጥያቄ በሚል የቀረበው፣ ለዚህ ሁሉ መርዛማ ስብከት መነሻ ነው ማለት ስህተት አይመስልም። የዚያ ዘመን ትውልዶች ከ20 እና 30 ዓመት በኋላም ወደስልጣን ሲመጡ ያንንው መተግበር ጀመሩ። እነዚህ የፈጠሩት ማንነትን መሰረት ያደረገ አከላለል ለዚህ ሁሉ ችግር ዳርጎናል። 

በማንነት ላይ የተመሰረተ አከላለል ከተመሰረተ ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በአማርኛ ተናጋሪው ላይ እንደተከሰተው አይነት የዘር ጭፍጨፋ አይሁን እንጂ በተጎራባች ብሄረሰቦች መሀከል በድንበር ውዝግብ ምክንያት በርካታ ግጭቶች ተከስተዋል። በቅርቡም የተከሰቱ አሉ። በእነዚህም ግጭቶች የተነሳ የሰው ህይወትና የንብረት ውድመት ደርሷል። የማንነት/ዘር ፖለቲካ መዘዙ ለበርካታ ዘመናት ወንድሜ እህቴ ተባብለው በሚኖሩ ብሄረሰቦችም መሀከል ሳይቀር አስከፊ ግጭት መቀስቀሱ አልቀረም። ለዚህ የጌዲኦንና የጉጂን በርካታ ህዝብ ያፈናቀለና በአለማቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ የነበረን ክስተት ማንሳት ይቻላል።

የአሁኑ አስተዳደር ከቀድሞው በተሻለ ቢያንስ ሀገርን በማስቀደም የፖለቲካ ስብከት ቢያደርግም፣ ዋናውን ሰንኮፍ ነቅሎ ለመጣል አቅሙም፣ ግዜውም ያለው አይመስልም። ከምርጫ በኋላ የሚመጣው መንግስት ይህን ማንነትን መሰረት ያደረገ የአስተዳደር ክፍፍል እስከሚያስወግድ ድረስ፣ በሚቀጥለው ክፍል የፖሊስ አስተዳደሩን እና የፍትህ ስርዓቱን በተመለከተ የንፁሀንን እልቂት የአሁኑ መንግስት ለማስቆም እንዲረዳው የሚያስችሉ ሁለት አማራጮች አቀርባለሁ።

በክፍል ሶስት በየክልሉ ስለሚገኘው ጦር ከዚህ በፊት በግለሰቦችም ሆነ በድርጅቶች ሲቀርብ የነበረውን አማራጭ አነሳለሁ። እነዚህ አማራጮችን የማቀርበው መንግስት የህዝብን እልቂት ለማስቆም፣ የበለፀገች እና ሁሉም ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩባት ሀገርን ለመገንባት ቁርጠኝነቱ አለው ከሚል እምነት በመነሳት ነው።

2.የፖሊስና የፍትሕ ርዓትን በተመለከተ

ማንነትን መሰረት ያደረገ ክፍፍል እስከሚወገድ ድረስ  የፖሊስ መዋቅሩንና የህግ ስርዓቱን ከየክልሉ አስተዳደር አውጥቶ እራሱን በቻለ አዲስ አስተዳደር መተካት አንደኛው አማራጭ ሲሆን፣

ሁለተኛው ደግሞ ሁለቱንም በአንድ አጣምሮ ማስኬድ የፖለቲካ ችግር የሚያስከትል መስሎ ከታየ፣ ቢያንስ የፖሊስ አስተዳደሩን ለብቻ ማድረግ ነው። ሁለቱም ግዜ የማይፈጁ እና በቀላሉ ሊተገበሩ የሚችሉ አማራጮች ናቸው።

እነዚህ ሁለት አካላትን ነጥሎ ለማዋቀር ወይ በደርግ ግዜ ወይም በንጉሱ ግዜ በነበረው አስተዳደር መንገድ መሄድ ይቻላል። ለምሳሌ፣ የጎጃም ክፍለሀገር ፖሊስና ፍትህ አስተዳደር፣ የሸዋ ክፍለሀገር ፖሊስና ፍትህ አስተዳደር፣ የጎንደር ክፍለሀገር ፖሊስና ፍትህ አስተዳደር፣ የሀረር ክፍለሀገር ፖሊስና ፍትህ አስተዳደር፣ ወዘተ የሚሉ መዋቅር መፍጠር ይቻላል። ከዚህም የተለየ አማራጭ ማቅረብ ይቻላል።

ዋናው ነጥብ የፖሊስና የፍትህ አስተዳደሩ በቀጥታ ከየክልሉ ፖለቲካ ካርታም ሆነ የአስተዳደር መዋቅር ጋር እንዳይገጥም ማድረጉ ላይ ነው። የበጀት ጉዳይ በቀጥታ ከፌደራል መንግስት መሆን ይችላል።

ይህ ከላይ የቀረበው አማራጭ አሁን በቀላሉ ሊተገበር የሚችልበት አጋጣሚ ያለ ይመስላል።

አንደኛ፣ ለዚህ እንቅፋት የሚሆነው የህወሀት አስተዳደር እየተመታ ነው። ይህም ማለት የአሁኑ የአስተዳደር ክፍፍል መስራች የሆነው የፖለቲካው አካል ፍቃድ አያስፈልገውም። ሁለተኛ፣ የዚህ አይነቱ አስተዳደር ህዝብን ከጥፋት ሊታደግ ያለመ እና የወቅቱን ማንነትን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ሹመኞችን የማይነካ በመሆኑ ተቃውሞ እንኳ ቢነሳ የጎላ እንደማይሆን መገመት ይቻላል።

አንድ ትልቅ ችግር ህገመንግስት በሚል የቀረበው ጉዳይ ነው። ለዚህ ህገመንግስቱን ማሻሻል የሚለው የራሱን ችግር ይዞ ስለሚመጣ ያንን መጠበቅ አስፈላጊ አይሆንም። የንፁሀን ህዝብ ጭፍጨፋ በየእለቱ በሚባል ሁኔታ እየተካሄደ በመሆኑ የፖሊስ አስተዳደር መዋቅሩን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቶ ማስተካከልና መተግበር ይቻላል። ለትግበራው አዲስ የፖሊስ መዋቅርም ላያስፈልግ ይችላል። የየክልሉን ፖሊስ በፌደራል ፖሊስ ስር አደራጅቶ የአስተዳደር ክፍላቸውን ከላይ በቀረበው አማራጭ መሰረት ማዋቀር ይቻላል። የፍትህ አስተዳደሩንም በፍትህ ሚኒስትር ስር ማዋቀር ይቻላል።

ከላይ የፍትህና የፖሊስ አስተዳደሩን አሁን ካለው የፖለቲካ አደረጃጀት መነጠል ካልተቻለ የፖሊሱን ብቻ ለይቶ ማዋቀር የሚል አማራጭ አቅርቤ ነበር። ይህ አማራጭ የራሱ ችግር አለው። ትልቁ በደል እየደረሰ ያለውና በየአስተዳደር ክልል ውስጥ የሚኖረው ህዝብ ቅሬታ በፖሊስ መዋቅር ብቻ የሚፈታ አይመስልም። ለዚህ የህግ ስርዓቱን ልክ በፖሊሱ መልክ ማዋቀር ይጠይቃል። ይህ ካልሆነ ግን የተጠቀበው ንፁሀንን የመታደግ ዓላማ የሚሳካ አይመስልም።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር እያንዳንዱ ክልል የየራሱ ህግ አለውና የህግ አስፈፃሚው ከክልሉ አስተዳደር ከተነጠቀ እንዴት ሊሆን ነው የሚል ነው። ለዚህ የህግ ባለሞያዎች በአጭር ግዜ መፍትሄ እንዲያቀርቡ ማማከር ይቻላል። አሊያም በግዜያዊ መልኩ ሀገሪቱ በአጠቃላይ በአንድ አይነት የፍትህ ስርዓት እንድትተዳደር ማድረግ ይቻላል። ይህ ግዜያዊ አማራጭ በአጭር ግዜ ሊፈፀም የሚችል ሲሆን፣ ከምርጫ በኋላ ግን ህዝብ የተሳተፈበት ማንነትን መሰረት ያላደረገ የአስተዳደር መዋቅርና የህገመንግስት መሻሻል በጥናት ማቅረብ ያስፈልጋል።

3.የየክሉ ልዩ ኃይልንና ሌሎች የተደራጁ ታጣቂዎችን በተመለከተ

በየክልሉ ልዩ ኃይል በሚል የተደራጁ አካላት በሁሉም ክልል ባይሆንም ከችግር ፈጣሪ ውስጥ ምናልባትም ግንባር ቀደሞቹ ሳይሆኑ አይቀርም። ፉክክር በሚመስል መልኩ የየክልሉ ኃይል እየፈረጠመ ሲመጣ ያስተዋለ ሁሉ በየግዜው የከፋ ችግር እንዳይመጣ በማስገንዘብ ለመንግስት ውትወታ ማድረጉ አልቀረም። እነዚሁ ልዩ ኃይል የሚባሉ ታጣቂዎች በአንዳንድ አካባቢዎች በንፁሀን ግድያ ላይ በቀጥታ ተሳታፊ የነበሩበት ግዜ ትንሽ አይደለም።
በየክልሉ ልዩ ኃይል በሚል የተደራጁ አካላት በሁሉም ክልል ባይሆንም ከችግር ፈጣሪ ውስጥ ምናልባትም ግንባር ቀደሞቹ ሳይሆኑ አይቀርም።
በአለማችን ታሪክ በማእከላዊ መንግስት የማይተዳደር ጦር ሲኖር ማዕከላዊ መንግስቱንና ሀገርን መፈታተኑ የታመነ ነው። ለዚህ ከታሪክ ከሀገራችንም (ለምሳሌ ዘመነ መሳፍንቱን) ከሀገራችን ውጭም ከጥንታዊ መንግስታት እስከ ቅርብ ዘመናችን ታሪክ ያሉ በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ በጥንታዊ ግብፅ ቀዳማይ፣ መሀከለኛ እና ዳህራይ የሚባሉት ዘመናት “ፔሬድስ” ዋናው መንግስት በጦር የማዘዝ ኃይሉ ተዳክሞ የተለያዩ ግዛቶች (አብዛኛውን ግዜ የታችኛው እና የላይኛው ግብፅ ግዛቶች) የራሳቸውን መንግስታት መስርተው የኖሩበትን የሚመለከቱ ናቸው።  በአሁኑ ወቅት በትግራይ የተከሰተውም ይኸው ከማእከላዊ የጦር እዝ ስር ያፈነገጠ በክልሉ ብቻ የሚታዘዝ እራሱን የቻለ ጦር መፈጠሩ ነው።

አሁን አንድ ትልቅ ፈተና ገጥሟል። እንደተጠበቀው የትግራዩ የክልል ጦር ጦርነት በማእከላዊ መንግስት ላይ ከፍቷል። መንግስትም ቀዳሚ ተግባሩ መሪዎቹን/ወንጀለኞቹን ይዞ ያደራጁትን ጦር ትጥቅ ማስፈታት እንደሆነ ገልጿል። ይህ ሌላ መዘዝ አለው። የትግራዩ ኃይል ትጥቅ እንዲፈታ ተደርጎ በሌላው ያለው እንደታጠቀ እንዲቆይ ከተደረገ በራሱ ሌላ ፈተና ማምጣቱ የማይቀር ነው። ከዚህም በላይ ሌላው ክልል ግዜ ጠብቆ ተመሳሳይ አመፅ በማእከላዊ መንግስቱ ላይ ላለማስነሳቱ ምንም መተማመኛ የለም። ለዚህ አንድ አማራጭ ማቅረብ ይቻላል።
የትግራዩ ኃይል ትጥቅ እንዲፈታ ተደርጎ በሌላው ያለው እንደታጠቀ እንዲቆይ ከተደረገ በራሱ ሌላ ፈተና ማምጣቱ የማይቀር ነው።
ከዚህ በፊት በጉዳዩ ላይ በግለሰብም ደረጃ ሆነ በድርጅት መልክ አካሄዱ ያላማራቸው  በርካቶች ፅፈዋል፤ ምክርም ለግሰዋል። እነዚህ አካላት እንዳመላከቱት ልዩ ኃይልንና በተለያየ ስም ተደራጅቶ የሚጠራ የታጠቀ ጦርን በመደበኛው ጦር ወይም በፖሊስ ሰራዊት ውስጥ መካተት የሚፈልገውን ብቃቱን እያረጋገጡ ማካተት፣ የሲቪል ህይወት የሚፈልገውን ከጦሩ እያሰናበቱ ህይወቱን እንዲመራ ማድረግ ነው። ይህ ግዜ የሚሰጠው አይደለም። ግዜ ለመስጠት ቢታሰብም፣ በዚህ ሰዓት በትግራይ ያለው ሁኔታ አይፈቅድም።

4.ማጠቃለያ

በእዚህ አጭር መጣጥፍ ሁለት መሰረታዊ ነጥቦች ተነስተዋል። አንድ በክልል ልዩ ኃይል ወይም ሌላ የተደራጀ ታጣቂ ኃይል የሚባል ነገር እንዳይኖር ማድረግ የሚል ነው። ሁለት የፖሊስንና የፍትህ መዋቅሩን ወይም የፖሊስ መዋቅሩን ብቻ ከየክልሉ የአስተዳደር እና የፖለቲካ ካርታ መዋቅር ነጥሎ በተለየ መልክ ማደራጀት ነው። በየክልሉ ያለው የተደራጀ ጦር/ታጣቂ ሲወገድ፣ ምናልባት በእንሱ ይሸፈን የነበረ ጥበቃ (ካለ) ክፍተት ሊያመጣ ይችላል።

ይህ እንዳይሆን፣ ክፍተቱን በፖሊስ እንዲሸፈን፣ ከፖሊስ አቅም በላይ የሆነውን መከላከያ እንዲፈታው ማድረግ አግባብ ይመስላል። ለዚህ የፖሊስንና የመከላከያ ኃይልን በብቃት ከማጠናከር በተጨማሪ በሙያዊ ስነምግባር የበሰሉ በማድረግ ረገድ መንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

 


Share

Published

Updated


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service