የአድዋ ዘመቻና ባሩድ አልባው የምድር ፍልሚያ

የዐድዋ ድል የዓለምን ታሪክ ገልብጧል ይባላል፤ አዎን። የአውሮጳውያንን ውርደት በመላው ዓለም እንደ ርዕደ መሬት አንዝሯል ይባላል፤ ይህም ልክ ነው። ድሉ ለመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራትና ጌጥ ሆኗል ይባላል፤ ሁላችንንም ያስማማናል። ሆኖም የዐድዋ ጦርነት የተከወነው የኢዮትዮጵያና የጣልያን ወታደሮች በያዟቸው ጠመንጃዎች መሃል ብቻ አልነበረም። እንደ ሌሎች የዓለማችን የጦርነት ታሪኮች ሁሉ የዐድዋ ጦርነትም ዓበይት ትኩረቱን ያደረገው በባሩድ ዙሪያ ይሁን'ጂ ከምድሩም ጋር ነበር። ይህ ጽሁፍ ከምድሩ ጋር የተደረገውን ፍልሚያ በጊዜና በቦታ ለይቶ በመፈተሽ የተደረሰበትን ድምዳሜ በአጭሩ ለማሳየት ይሞክራል።

Adwa

View of Adwa from the Axum road, drawing by Eduardo Ximenes (1852-1932), May 26, 1895. Source: Getty

ፍልሚያው ባሩድ ብቻ?

ጦርነቱ በተካሄደበት ወቅት የከባቢውን ሁኔታ በበቂ ሁኔታ መርምሮ የዘገበ ባለሞያ አልነበረም። አለመኖሩም አይደንቅም። ክፍተቱ ግን ለአንዳንድ ጸሃፊያን የተሳሳቱ ድምዳሜዎች የማርያም በር ከፍቶላቸዋል። ለዚህም ነው የጣሊያን ጦር ከተሸነፈባቸው ምክንያቶች አንዱ ፍልሚያ የተካሄደበት መሬቱ ለኢትዮጵያውያን የበለጠ አመቺ ስለነበረ የሚል እንቶ ፈንቶ የምናነበው።

ታሪክ እንደጦርነት ያሉ ክስተቶችን ሲከትብ ምድሩ ለመጻፊያ ሰሌዳነት ያገለግላል ይባላልና (History focuses on events such as wars that are inscribed in geographic space) የዓድዋ ዘመቻን የዘገቡ ጸሃፍት እግረ መንገዳቸውን የጉዞውንም ሆነ ፍልሚያ የተካሄደበትን የምድር ሁኔታ በተወሰነ መልኩ ገልጸውት እናገኛለን።

ይህ መረጃ የሣሣና በወጥነት ያልተመረመረ ቢሆንም አሁን ለቀረበው ጥናት እንደ እርሾ ሆኖ አገልግሏል። ባናቱ ደግሞ የምድር መረጃ ማጠናቀሪያ ዘዴን በመጠቀም ተዛማች መረጃዎችን ከስፍራው ጋር አነባብረን መርምረናል።

በዚህ ጽሑፍ “የዐድዋ ጦርነት ቀጣና” የሚሸፍነው ከአዲስ አበባ ተነስቶ ዐድዋ እስኪደርስ ዘማቾቹ የተጓዙበትን የጉዞ መስመርን፤ ውጊያ የተካሄዱባቸውን አውድማዎችን፣ እንዲሁም ከጉዞ መስመሩ ወደ 50 ኪ/ሜትር ያህል በስተቀኝና በስተግራ ያለ መሬትን (buffer zone) ጨምሮ ነው፡፡ “መሬት” ደግሞ የአፈሩን ሁኔታ፤ የምድረገጹን (ተዳፋቱን)፣ እና የከባቢ አየሩን ሁኔታ አጠቃሎ የያዘ ነው፡፡ 

ወደ ዐድዋ የተደረገው የዘመቻ ጉዞ አምስት ወራትን አስቆጥሯል። ፍጹም ለየለት ውጊያ የተካሄዱባቸው ቀናት በአምባ አላጌ (አንድ ቀን)፤ በመቀሌ (አራት ቀናት) ና በዓድዋ (አንድ ቀን) ሆኖ በድምሩ ከ6 ቀናት ያነሰ ነው። ይህ ማለት በቀሪዎቹ ቀናት ሁሉ ጦርነት አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ በመንገድ ላይ ከሽፍቶችም ሆነ ከጣልያን ወታደሮች ጋር አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ መጠነኛ ውጊያዎች ነበሩ። ሆኖም ግን ውጊያ ኖረም አልኖረ ሠራዊቱ ጣልያንን ድል እስኪነሳ አምስቱንም ወራት ከምድሩ ፈተና ጋር ያለማቋረጥ ተፋልሟል።

እንደ ቦታው ነባራዊ ሁኔታ ምድሩ በበላዩ ለሰፈሩት ሰዎች፤ እንስሣት እና ዕጽዋት ወይ በረከት አልያም መርገምት (ፈተና) ሊሆን ይችላል፡፡ ጦርነት ሲካሄድ ዘርፈ ብዙ ፍላጎት (demand) አለና ፍላጎቶቹን ለመሙላት ተመጣጣኝ የአቅርቦት (supply) መኖር ግድ ይላል። በዚህ ጽሁፍ “ፍላጎት” ሲባል ለጦሩና ለእንስሣቱ የሚያስፈልገው ሥንቅና መኖ ነው። “አቅርቦት” ደግሞ ሠራዊቱንና ከብቱን ሊመግብ የሚችለውን የመሬቱን አቅም ነው። በፍላጎትና በአቅርቦት መጠን መሃል የሚዛን መበላለጥ አለ። ይህ መበላለጥ ደግሞ በጦርነቱ ሂደትና ውጤት ላይ አሉታዊና አወንታዊ አስተዋጾዎች ይኖሩታልና እንደሚከተለው እንመረምረዋለን።

ክተት ሠራዊት፤ ምታ ነጋሪት።

ወራሪውን የጣልያንን ጦር ለመግጠም አጤ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ከአዲስ አበባ ሲነሱ ወደ 40,000 ሠራዊት ይዘው ነበር። በክተት አዋጁ መሰረት ከሸዋ መለስ የሚነሳው ዘማች ቀድሞ እንዲደርስ የታዘዘው በወረይሉ ነው። ከወረይሉ ጀምሮ የሠራዊቱ ቁጥር እጅግ ጨምሯል። ንጉሡ ጉዟቸውን ሲቀጥሉ በየመንገዳቸው ላይ አኩርፎ የነበረውም ሆነ በናፍቆት ሲጠብቃቸው የነበረ ጦር እጅ እየነሳ ሲቀላቀላቸው የሠራዊቱ ቁጥር የበለጠ አሻቅቧል።

ደጃች ጓንጉል ዘገየ መርሳ ላይ፤ የጎጃሙ ንጉሥ ተ/ሃይማኖት በበጌምድር አድርገው መሐን ሕዝባ ላይ፤ እንዲሁም በርካታ ጦር መሪዎች ጨለቆት ላይ ንጉሠ ነገሥቱን ተቀላቅለዋል። ዓድዋ ከደረሱ በኋላ እነ ራስ ሃጎስ ተፈሪ እና ራስ ስብሃት ከነጦርና መሳሪያቸው ጣልያንኖችን በመክዳት አጤ ምኒልክን ተቀላቅለዋል። አጤ ምኒልክ አሸንጌ ሲደርሱ ሠራዊታቸው ከ100,000 በላይ፤ በዓድዋ ደግሞ ከ120,000 በላይ ዘማች እና ከ75,000 ከብቶች በላይ ደርሷል።

ካርታ 1 የኢትዮጵያ ሠራዊት የመጨረሻው ውጊያ እስከተደረገበት ዐድዋ ድረስ ቁጥሩ ሳያቋርጥ እያደገ እንደነበር ያሳያል።
Adwa
Source: Daniel Kassahun
ካርታ 1ሠራዊቱ ከአዲስ አበባ እየራቀ ሲሄድ ቁጥሩ እየበረከተ ሄዷል።

ካርታ 2ሠራዊቱ ከአዲስ አበባ እየራቀ  ሲሄድ የሥንቅ ይዞታው እየቀነሰ ሄዷል።

ካርታ 3ሠራዊቱ ከአዲስ አበባ እየራቀ ሲሄድ የአንድ ቦታ ላይ ቆይታ ረዝሟል፡፡

የሆድ ጉዞ ወይንስ የእግር?

የወታደራዊ ፍላጎት ሲባል ትጥቅ፣ ቀለብ፣ መጓጓዣ፣ ወዘተን ይጠቀልላል። ሆኖም የትጥቅ ሁኔታና ሚዛን በበርካታ ድርሳናት የተዳሰሰ በመሆኑ ይህ ጽሁፍ በቀለብ ላይ ብቻ ያተኩራል። ናፖሊዮን ቦናፓርት “የጦር ሠራዊት የሚጓዘው በሆዱ እንጂ በእግሩ አይደለም” ይላል። ቀለብ ያለው ጦር በርትቶ ሲዋጋ የተራበው ደግሞ መዋጋት አይችልምና። ኢትዮጵያ ለዐድዋ ጦርነት አፍሪካ አሳይታ የማታውቀው የሠራዊት ብዛት አሰልፋለች። ሠራዊት ሲበዛ ለወታደራዊ የበላይነት ጠቀሜታ ይኖረዋል፤ ቀለቡ ግን ክፉኛ ራስ ምታት ነው።

የናፖሊዮንን ሠራዊት ከሩስያ ጋር በተደረገው ጦርነት እጅግ የፈተነው የሚበ፟ላ ጠፍቶ አልነበር? በጳውሎስ ኞኞ መጽሃፍ ፓውሌቲ ሲናገር የምኒልክ ሠራዊት ለውጊያ የሚሄዱ ወታደሮች እንደማይመስሉና ህዝቡ በሙሉ ተነቅሎ የሚሄድ እንደሚምስል ነው። እንደ በርክሌይ ገለጻ “የኢትዮጵያ ሠራዊት ባለፈበት መንገድ ምድሩ ወደ ምድረ በዳነት ይቀየር ነበር”። 

ከግዙፍ ሠራዊት የዕለት ተለት ምግብ፤ መጠጥና ግጦሽ ማቅረብ ለኢትዮጵያውያን ከባድ ለጣልያኖቹ ደግሞ እጅግ የቀለለ ነበር። አንደኛ ከሃያ ሺህ የማይበልጡ ተዋጊዎች ነው ያሰለፉት። ሁለተኛ የሥንቅ ምንጫቸው እንደ ኢትዮጵያውያን ከየደረሱበት መሬት ሳይሆን ስጋው ከህንድ የተቀረው ከጣልያን በመርከብ ተጭኖ፣ ከምጽዋ ወደብ ተራግፎ፣ በመጨረሻም ከየምሽጎቻቸው የሚሰፈርላቸው ራሽን ነው። ሶስተኛ ጣልያኖቹ በእግር የተጓዙት አጠቃላይ ርቅት ኢትዮጵያውያኑ በባዶ እግር ከተጓዙት ርቀት ሲነጻጸር ሩቡን እንኳ አይሞላም።

በክተት አዋጁ እያንዳንዱ ዘማች የጦር መሳሪያውንና ለአስር ቀናት የሚበቃ ሥንቁን ይዞ እንዲገኝ ነበር የታዘዘው። ከቤተ መንግስቱ በከብቶች የተጫነ ሥንቅ የነበረ ቢሆንም ግልጋሎቱ ለመኳንንቱ ነበር። በወረይሉና በቦሩ ሜዳ ላይ የሥንቅ ግምጃ ቤቶች ተደራጅተው ነበረ። ለሠራዊቱ ግን ከጉዞው ቀጣና ከሚሰበሰብ ሥንቅ ነበር የታቀደው። ለዚህ ዕቅድ ማስፈጸሚያ ዓጤ ምኒልክ 10% የሚሆነው የእርሻ ምርት ለጦርነቱ ሥንቅነት እንዲውል አውጀው ነበር።

ሆኖም ግን በርካቶች ያካባቢው ኗሪዎች የሚዘረፉበት አጋጣሚም ስለነበር ለዐድዋ ጦር ቀጣና ቀርቦ የተገኘው ኗሪ ፈተና እና እሮሮ በርክቶ ነበር። ለዚህም ነው ዘርፎ የተገኘ ወታደር እርምጃ እንደሚወሰድበት የተደነገገው። ቀርቦ በመገኘት ሳቢያ ክፉኛ ጣጣ ሲመጣ ቅርበት-ወለድ ፍዳ (tragedy of proximity) ይከሰታልና በጦርነቱ ቀጣና ይኖሩ የነበሩ ዜጎች አሌ የማይባል ዋጋ ከፍለዋል፣ ጥሪታቸውን አሟጠዋል።

እዚህ ላይ ሊጤን የሚገባው ዳግማዊ ምኒልክ የዘመቻውን ማስጀመሪያ ወቅት ሲወስኑ የሥንቅ አቅርቦት ጥያቈን ባማከለ ሁኔታ ነበር። ከጦርነቱ ቀደም ብሎ ከ1880 እስከ 1884 ዓ/ም ባገሪቱ ታላቅ ርሃብ ገብቶ ስለነበር ንጉሡ ምድሩም ሆነ ሕዝቡ እስኪያገግም ጊዜ ሰጥተዋል። ጣልያኖች ከህንድ ባመጡት ደስታ በሚባል በሽታ ሳቢያ የሃገሪቱ ከብቶች ከ90% በላይ ሲያልቁ ረሃብ በመላው ሃገሪቱ ተንሰራፍቶ ነበር። በወቅቱ ጣሊያናዊው ሳሊምቢኒ በጳውሎስ ኞኞ መጽሃፍ ላይ “... ዓድዋ የመቃብር ስፍራ እንጂ ከተማ አትመስልም” ብሎ ነበር።

ለዚህም ይመስላል አጤ ምኒልክ በዓዋጁ ላይ “... እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ የሰዉን መድከም አይቼ እስካሁን [ጠላትን] ዝምብለው” የሚል ሃረግ የጠቀሱት። በመቀጠልም የጥቅምት ወር ለዘመቻው የተቆረጠው ወንዞች እስኪጎድሉ ስለጠበቁ ብቻ ሳይሆን ወቅቱ የአዝመራ መሰብሰቢያ ጊዜ ሰለሚሆንና ለዘማቹ የምግብ አቅርቦትን ለማስተማመን ነው።

አሊ (1998) እና ጸሃፌ ትዕዛዝ ገ/ሥላሴ እንደመሰክሩት የኢትዮጵያ ሠራዊት የጎንደር-ትግራይ ወሰን አካባቢ እስኪደርስ ሁለቱን ወር ሙሉ ግብር እየበላ ተጉዋዘ እንጂ የሥንቅ አቁማዳዉን አልፈታም። የሽምብራ እሸቱም ደርሶ ነበረ። ሆኖም ግን ሠራዊቱ ከመሃል አገር እየራቀ በሄደ መጠን ሥንቁን እያሟጠጠ (ካርታ 2) በሌላ በኩል ደግሞ ሠራዊቱ የሚያልፍባቸው አካባቢዎች እጅ እያጠረ መጥቷል።

ከዐድዋ ጦርነት ድል ማግስት በመሬቱ ላይ ተጨማሪ ጫና እንዳይደርስ ይመስላል ሠራዊቱ በምዕራብና በምሥራቅ በሁለት የጉዞ መስመሮች ተከፍሎ ወደ ቀዬው እንዲመለስ የተደረገው። ተመልሰው አሸንጌ ሃይቅ አካባቢ ሲደርሱ ነበር በቂ ምግብ ማግኘት የጀመሩት። 

መጓዝ ወይንስ መራ፟ብ?

ዘርፈ ብዙ ተልዕኮ የነበረው የዐድዋ ዘመቻ ጉዞ አዝጋሚ ነበር። በቀን ለአምስት ሰአታት በመጓዝ በአማካይ ስምንት ኪ/ሜትሮች ነበር የሚሸፍነው። አንደኛ የመንገዱ አስቸጋሪነት ለመፍጠን አዳጋች ነበር። ሁለተኛ ሠራዊቱና ከብቶቹ በፈጠነ ጉዞ ሳቢያ እንዳይጎዱ ጥንቃቄ ይደረግ ነበር። ሶስተኛ በየመንገዱ ፍትሕን ለማስፈን ሲባል፤ ወዘተ። በነዚህ ምክንያት የንጉሡ ጦር በየመንገዱ ሰፈራ ያደርግ ነበር። በጉዞው ላይ በድምሩ በ12 ቦታዎቸ ላይ ድንኳን እየተጣለ ሰፈራ ተደርጓል።ስፍራ ተመርጦ ድንኳን ከተጣለ በኋላ ጦሩ በአካባቢው ተዘዋውሮ ምግብ፣ መጠጥ፣ የማገዶ እንጨትና፣ የእንስሣት መኖ ያሰባስባል። በእያንዳንዱ ሰፈራ የነበረው የቀናት ርዝማኔ ይለያያል።

ካርታ 3 ላይ በመስፈሪያ ቦታዎች ላይ የነበረው ቆይታ ከአዲስ አበባ ከተማ በተራቀ ቁጥር እያደገ መምጣቱን ያሳያል። ይህም የተከሰተው ከአዲስ አበባ የራቁ ስፍራዎች ለመሰንበት አመችተው ሳይሆን የጠላት ወረዳ አካባቢ ስለነበር ነው። ሠራዊቱ አንድ ቦታ ሲከርም ከቦታው የሚጠበቀው የምግብ ፍላጎት በብዙ እጥፍ ይንራል፤ የምድርና የሕዝቡ ፈተና የከፋ ይሆናል፤ ለሠራዊቱ የሚያስፈልገውን አቅርቦት ለሟሟላት የሚሸፍነው የርቀት መጠንም (search radius) ከዕለት ወደ ዕለት እየረዘመ ይሄዳል።

ለግዙፉ የኢትዮጵያ ሠራዊት የነበረው ምርጫ ሁለት ብቻ ነበሩ፡ ወይ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ወይንም በረሃብና በኩብለላ መበታተን። ዓድዋ ላይ መሰንበታቸው ያሳሰባቸው አጤ ምኒልክ እነ ሊቀ መኳስ አባተን የመረብን አካባቢ የመሬት ለምነት እንዲቃኙ (reconnaissance survey) ልከዋቸዋል። ሆኖም የልኡካኑ ሪፖርት “የባሰ አለና አገርህን አትልቀቅ” የሚመስል ነው። እንኳንስ ግዙፍ ጦራችንን መግቦ ሊያሰነብትልን ይቅርና ላካባቢው ኗሪም ስላልበቃ እዚሁ ዐድዋ መቆየት ይሻላል ብለው ንጉሱን ባያሳምኑ ኑሮ ምናልባትም የታሪካዊው ድል ስፍራ በዐድዋ ላይሆን ይችል ነበር።
የልኡካኑ ሪፖርት “የባሰ አለና አገርህን አትልቀቅ” የሚመስል ነው። እንኳንስ ግዙፍ ጦራችንን መግቦ ሊያሰነብትልን ይቅርና ላካባቢው ኗሪም ስላልበቃ እዚሁ ዐድዋ መቆየት ይሻላል ብለው ንጉሱን ባያሳምኑ ኑሮ ምናልባትም የታሪካዊው ድል ስፍራ በዐድዋ ላይሆን ይችል ነበር።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ? 

በየአካባቢው የሚዘንበው የዝናብ መጠን የመሬቱን የመሸከም (የመቀለብ) አቅም አንዱ መለኪያ ነው። ሆኖም በዐድዋ ጦር ቀጣና የዝናብ ሥርጭቱ መጠን እኩል አይደለም። ካርታ 4 ላይ ሠራዊቱ ዐድዋ እስኪደርስ የዝናብ መጠኑና የመሬቱ እርጥበት እየቀነሰ መሄዱን ያሳያል። በዚህም ሳቢያ ሠራዊቱ ወደፊት በዘለቀ ቁጥር ከጉዞ ቀጣናው ሊገኝ የሚችለው የሥንቅ አቅርቦት እየሳሳ ሄዶ ከተፈጥሮ ጋር የሚደረገውን ፍልሚያ ያገዝፈዋል።

አገስተስ ዌልድ የተባለ እንግሊዛዊ ጋዜጠኛ በጄኔራል ባራቲዬሪ ሽንፈት ሲያላግጥ፤ የምኒልክን ጦር ለአምስት ተጨማሪ ቀናት ቢታገስ ጦራቸው ሙሉ ለሙሉ እንደሚበተን መገመት አቅቶት “ድንገተኛ ጥቃት” የሚባል ቁማር ተጫውቶ ተበላ ብሏል። በዚህ ስላቅ ውስጥ ያለውን መራራ እውነት ደግሞ መካድም አይቻልም። ፈተናው በዚህ ብቻ አያበቃም። 

ከባቢ አየሩ እርጥበትን ለምድሩ በዝናብ መልክ ሰጪ ብቻ ሳይሆን ጊዜ ጠብቆ ደግሞ ራሱ ስለሚጠማ ከምድሩ ላይ የተገኘውን ውሃ (እርጥበት) በተንነት መልክ የሚቀማ ነው። እንደ ሙቀቱ መጠን የአየሩ የማትነን አቅም (Potential Evapotranspiration) ከፍ ወይንም ዝቅ ይላል። የአየር ሙቀቱ መጠን ከፍ ሲል በምድሩ የሚገኝ እርጥበትን ሁሉ የመንጠቅ አቅሙ ያይላል፡ ከኩሬ፣ ከሃይቅ፣ ከወንዝ፣ ከእጽዋት፣ ከአፈር፣ ከሰውነታችን፣ እና ከተሰጣ ልብስ እንኳ ሳይቀር የተገኘውን እርጥበት ይዘርፋል። የውሃ ጥማችን ዋናው መንስዔ ይህንን ከሰውነት የተዘረፈ ውሃን ለመተካት የሚደረግ መሻት አይደለምን? ሠራዊቱ በተጓዘበት ቀጣና ሁሉ የአየሩ የማትነን አቅም ወጥ፟ አይደለም።

ካርታ 5 ሠራዊቱ ከአዲስ አበባ ተነስቶ እስከ ዐድዋ ድረስ የአየሩ የማትነን አቅም እንዴት እየጎለበተ እንደሚሄድ ያሳያል። ክስተቱ ደግሞ ቀድሞውኑ ዝናብ እያጠረ በሚሄድበት መሬት ላይ መሆኑ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሆንበታል። አሁንም በዚህ አያበቃም።
Adwa
Source: Daniel Kassahun


 

ካርታ 4ከአዲስ አበባ እየራቀ ሲሄድ ዝናብ-አጠር እየሆነ ይሄዳል።

ካርታ 5ከአዲስ አበባ እየራቀ ሲሄድ  የአየሩ የማትነን አቅም እየበረታ ይሄዳል።

ካርታ 6ከአዲስ አበባ እየራቀ ሲሄድ  ቆላማነቱ እየጎላ ይሄዳል።

የዐድዋ ጦር ቀጣና በእጅጉ ከፍና ዝቅ የሚል የምድር ገጽ (ካርታ 7) ብቻ ሳይሆን የተዳፋቱ መጠንም ከፍተኛ ነው።

በካርታ 8 ላይ የተዳፋት መጠን በጉዞው መስመር ላይ ከፍ እያለ ይዘልቃል።

በውጤቱም ባንድ በኩል ወደ ዐድዋ የሚደረገውን ግስጋሴ ፈታኝ ሲያደርገው በሌላ ደግሞ ለአፈር መሸርሸር ያለውን ተጋላጭነት ያጎላዋል። ተክለ ጻድቅ መኩሪያ በጉዞ ወቅት ሠራዊቱ አንድን ወንዝ 38 ጊዜ እንደተሻገረ የገለጹት የመሬቱን ፈታኝነት ጥሩ ማሳያ ነው። ለዚህ ጥናት በተከለለው የጦርነት ቀጣና ውስጥ 311 ወንዝና ጅረቶች ሲገኙ ከነኚህ ውስጥ 34ቱ አጤ ምኒልክ የተጓዙበትን መንገድ በቀጥታ ያቋርጡታል። 

የመካከለኛውና የሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል ለዘመናት መታረሱ ከመሬቱ ተዳፋትነት ጋር ተዳምሮ የአፈሩን ጥልቀትና ለምነት እጅግ ቀንሶታል። ሁርኒ የተባለ ስዊዘርላንዳዊ የአፈር አጥኚ ከአራት አሥርት አመታት በፊት ለመላው ኢትዮጵያ ካዘጋጀው የአፈር ጉስቁልና ካርታ ላይ የጦር ቀጣናውን መሬት ብቻ ቀንጭበን (clip ለማለትነው) ብንመለከት ሌላ እየገዘፈ የሚሄድ የምድር ፈተናን በካርታ 9 ላይ   እንመለከታለን።

ሠራዊቱ ከመሃል አገር በራቀ መጠን አፈሩ ለእርሻ ምርት ያለው አመቺነት በእጅጉ እያሽቆለቆለ ስለሚሄድ ሰውንም ሆነ እንሣትን የመመገብ አቅሙ እያነሰ እንደሚጓዝ ያመላክታል። ከዐድዋ አልፈን ወደ ኤርትራ ብንዘልቅ ከላይ የተጠቀሱት የምድሩ ፈተናዎች ቢብሱ'ንጂ አያንሱም። ታዲያ አንዳንድ የታሪክ ጸሃፍትና ፖለቲከኞች “አጤ ምንሊክ ከአድዋ ድል በኋላ መረብን ተሻግረው የጣልያንን ጦር ሙሉ ለሙሉ ከኢትዮጵያ ሳያስወግዱ መመለሳቸው ስህተት ነበር” ብለው የሚያቀርቡት ክስ ውሃ ያነሳ ይሆን?

እል፟ፍ ሲሉ ፍዳ?

ትንታኔው ሲቋጭ፤ ባንድ በኩል ጉዞው በገፋ ቁጥር የሠራዊቱ የቀለብ ፍላጎት ያሻቅባል። በተጓዳኝ መሬቱ ሥንቅ አቅርቦት ያለው አቅም ይመናመናል። በሌላ አገላለጽ የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ዐድዋ በተቃረቡ ቁጥር በፍላጎትና አቅርቦት ሚዛኑ እየጎደለ ከምድር ጋር የተጋረጡባቸው ፈተናዎችም እየበረታባቸው ሄዷል። የካርታ መረጃዎቹን ስንጨምቃቸው ሁኔታው ለሠራዊቱ “እል፟ፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል” ሳይሆን “እል፟ፍ ሲሉ ፍዳ ይገኛል” ሆኖበት ነበር። 

መቀሌ ላይ ኢትዮጵያውያን ሆን ብለው የውሃ ምንጩን በመቆጣጠር መሬቱ ለጣሊያኖች እንዳይመች ከደቀኑባቸው ፈተና ባሻገር ጣሊያኖቹ ከመሬት ጋር ያደረጉት ፍልሚያ ከኢትዮጵያውያን ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ይንን ሃቅ ደግሞ የጣልያን መሪዎች ያውቁታል። ለምሳሌ ኢትዮጵያውያን በባሻ አውአሎም በኩል ለጣልያኖች ካደረሱት አሳሳች መረጃዎች አንዱ “አብዛኛው ሠራዊት በረሃብ ስለተጠቃ አንድም ምግብ ፍለጋ ሌላም አጤ ምኒልክን ከድቶ ተበትኗል” የሚል ነበር። ይህ መረጃ በከፊል እውነት ነው።

ለምሳሌ ጸሃፌ ትዕዛዝ ገ/ሥላሴ ሲጽፉ የጣልያን ጦር ድንገተኛ ማጥቃት ባደረገበት ወቅት ከኢትዮጵያ ሠራዊት ውስጥ ተከዜን ተሻግረው እስከ ጽለምት ግማሹ ወደ ሽሬ የቀረውም ወደ ተምቤን ሥንቅ ፍለጋ ሄዶ እንደነበረና ቀሪውም አንድ ሲሶ ብቻ ነበር። ጄኔራል ባራትዬሪ የተጋነነውን መረጃ እንዳለ ሊገዛው የቻለበት አንዱ ምክንያት ቀድሞ ያውቅ ከነበረው ሃቅ ጋር ስለተገጣጠመለት ነበር።
Adwa
Source: Daniel Kassahun
ካርታ 7በጉዞ ቀጣናው ውስጥ የመሬቱ ከፍታ  ልዩነት እጅግ ከፍ ያለነው።

ካርታ 8የመሬቱ ተዳፋት መጠን ከአዲስ አበባ እየራቀ ሲሄድ ከፍ እያለ ይሄዳል።

ካርታ 9የአፈሩ ጥልቀትና ለምነት ከአዲስ አበባ እየራቀ ሲሄድ እየቀነሰ ይሄዳል።

እውነታው ከላይ የቀረበው ሆኖ ሳለ ከጣልያን ሽንፈት በኋላ አውሮፓውያን ታሪክ ሲጽፉ የዐድዋ ምድር ለኢትዮጵያውያን አልጋ ለጣሊያኖች ደግሞ ቀጋ እንደነበረ አስመስለው ነበር። ለምሳሌ በርክሌይ ጣልያኖቹ በደረሱበት ሁሉ የዐድዋ ምድር ቁም ስቅል እንዳሳያቸው ይገልጻል።

ተክለ ጻድቅ መኩሪያ በዐፄ ምንሊክ እና የኢትዮጵያ አንድት መጽሃፋቸው በገጽ 413 እንደገለጹት በጥቁር መሸነፍን አምኖ ላለመቀበል ሲሉ ጣልያኖቹ ከዘረዘሯቸው በርካታ ምክንያቶች ውስጥ “...በማያውቁትና ወጣ ገባ በሆነ መንገድ ሰውነታቸው ስለደከመ” የሚል ይገኝበታል። በርክሌይም በበኩሉ ካፒቴን ሜናሪኒ የተባለ ጣሊያናዊ መኮንን የዘረዘራቸውን ማስተባቢያዎች ሲግለጽ “... ለጦር ዕቅድ የተዘጋጀው ካርታችን በነበረው ግድፈት ሳቢያ ... ” የሚል ይገኝበታል። 

በአጠቃላይ የዐድዋ ታሪክ መታየት ያለበት ልክ እንደ አልማዝ ነው፡፡ አልማዝ ዙሪያው የተለያዩ ገጾች አሉት። ወደተለያየ የብርሃን አቅጣጫ ባዞርነው ቁጥር ቀድሞ ያላየነውን አዲስ ቀለም ይፈነጥቅልናል። የዐድዋ ድልንም ወደ ተለያዩ ተመራማሪዎች አይኖች ብናዘዋወረው ቀድሞ ያላየነውን አዳዲስ ግንዛቤዎችን ያስገኝልናል፡፡ ይህ ከ120,000 በላይ ዜጎችን ከ75,000 በላይ ከብቶችን አጣምሮ አምስት ወራት በፈጀ ጉዞ ከአንድ ሺህ ኪ/ሜትሮች በላይ የሆነ ርቀትን የሸፈነ ዘመቻ፤ በተለያየ የአየር ንብረትና መልክአ ምድርን አቋርጦ ዘመናዊ የተባለ የአውሮፓን ወራሪ ኃይል በጦር መሳሪያ ድል የነሳ ብቻ ሳይሆን ያልተተነገረለትን የመሬት ፈተና ድል የመንሳቱን ጉዳይ ለታሪክ ባለሙያዎች ብቻ የሚተው ጉዳይ አይደለም። ይልቁንም ድሉ በርካታ የጥናት ዘርፎችን መጋበዝና ማስተናገድ የሚያስችል ጥሬ የዕውቀት ቋት ነው።
የዐድዋ ታሪክ መታየት ያለበት ልክ እንደ አልማዝ ነው፡፡ ወደተለያየ የብርሃን አቅጣጫ ባዞርነው ቁጥር ቀድሞ ያላየነውን አዲስ ቀለም ይፈነጥቅልናል።
በመጨረሻም፡ዘላለማዊ ክብር ለሃገራችን ለተሰዉ፣ ለቆሰሉ፣ ሥንቅና ትጥቅን ለተሸከሙ፣ ተንቀሳቃሽ ኩሽና እያጓጓዙ ግዙፉን ሠራዊት ለመገቡ፣ በድምጽና በመሳሪያ የሠራዊቱን ላጀገኑ፣ የሠራዊቱን መንፈሳዊ ጥንካሬ ላበረቱ የሃይማኖት አባቶች፣ በጦሩ ቀጣና ፈታኝ በሆነ መሬት ላይ እየኖሩ ሳለ ለግዙፉ ሠራዊት ምግብ፣ ውሃ፣ የእንሣት መኖ፣ የማገዶ እንጨት፣ ወዘተ ላላቀረቡ ሁሉ፣ እንዲሁም ከድሉ በኋላ ሟቾችን በመቅበርና ቁስለኛውን አርበኝነት ለረዱ የትግራይ ገበሬዎች ይሁን።

ፀሐፊውን ዶ/ር ዳን ኤል ካሣሁንን daniel.kassahun@gmail.com ማግኘት ይቻላል።

ይህ ጽሁፍ ፌብሪዋሪ 28, 2021 በፍትሕ መጽሔት ላይ ለህትመት በቅቷል።

 

 


Share

Published

Updated

By Daniel Kassahun (PhD)

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service