ከዜማና እንጉርጉሮ ለዘመናት ያልተለየን “ዐባይ ውሃ ቋጠረን” ዜና ስንሰማ የያ ትውልድ ወገኖችና አባላት እጅጉን ደስ ብሎናል፡፡ ዐባይ የሀገር ሀብት፣ ዐባይ የሀገር ሲሳይ፣ ዐባይ ኢትዮጵያ፣ ዐባይ የብርሃን ሲሳይ ይሆን ዘንድ ከጥንት መሪዎቻችን ሳይቀር የመላው ሕዝባችን ፍላጎትና ምኞት ነበር፡፡ ይህ ምኞትና ፍላጎት ዛሬ የመጀመሪያውን ምዕራፍ በማግኘቱ የደስታው ተካፋዮች ሁነናል፡፡
ያ ትውልድ ለሀገሩና ለሕዝቡ የነበረው ቅን አሳቢነትና ራዕይ፤ አንግቦ የጮኸላቸው መፈክሮች ዛሬም አታጋይ ለመሆናቸው ምስክር ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በልማትና ዕድገት ጎዳና ትጓዝ ዘንድ የሁሉም ሕዝብ፣ ሀገር ወዳድ እና ብሎም ፖለቲከኛ ቀዳሚው እይታ ዐባይ ነው፡፡ ዐባይን በቁጭት ዓይን እያየነው ለዘመናት ጥሎን ሄዷል፣ ዐባይ በሀገራችን ምድር እየጋለበና እያጓራ ከራሱ አልፎ አፈራችንን አግዟል፡፡
ዛሬ ግን ምስጋና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዐባይ ሀገሬን ብሏል፤ “ዐባይ ኢትዮጵያ” እውነትም ስሙን አግኝቷል፡፡ ዐባይ ወጥቶ አዳሪ ለሀገራችን ብርሃን ሊሆን ቆርጦ ተነስቷል፡፡ “ዐባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” የከያንያን እንጉርጉሮ ወደ “ዐባይ ማደሪያ አገኘ ብርሃን ይዞ ይዞራል” ሊለወጥ ተቃርቧል፡፡ ዐባይ ገጠሪቷን ኢትዮጵያ በቀጭኑ ሽቦ ሊጎበኝ እያኮበኮበ ነው፡፡ ዐባይ በምድር ብቻ ሳይሆን በአየር ሊጓዝ ነው፡፡
ዐባይ ብርሃን፣ ዐባይ ኃይል፣ ዐባይ ዳቦ፣ ዐባይ ውሃ ሊሆን እየተንደረደረ ነው፡፡ ዐባይ ማደሪያውን ህዳሴው ግድብ አድርጎ በአራቱም ማዕዘን ኢትዮጵያን ሊቃኛት ሲዘጋጅ አስደሳች ነው፡፡ የዐባይ ፈረስ ከደቡብ ሰሜን ከምዕራብ ምሥራቅ ሊጋልብ አንድ እርምጃ ጀምሯል፡፡ ለዘመናት በምኞት የኖረ ብሔራዊ አጀንዳ ምላሽ አገኘ፤ ዐባይ ወጥቶ አዳሪ ሳይሆን አድሮ ወጪ ሊሆን ቆርጦ ተነስቷል፡፡ ዕድሜ ሰጥቶን ይህን ለማየት መብቃታችን ያስደስተናል፡፡
ለሀገርና ሕዝብ እድገትና ልማት አጥንታቸውን የከሰከሱ ደማቸውን ያፈሰሱ የያ ትውልድ ፈርጦችና መላው የኢትዮጵያ ልጆች ዐባይ ከኢትዮጵያ ተቀላቅሏልና ትንሳኤአችሁ ይሁን እንላለን፡፡ የሕዝባችን ደስታ ደስታችን መሆኑን “ያ ትውልድ ተቋም” እንገልጻለን፡፡
“ያ ትውልድ ተቋም” ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ብንሆንም ሀገር ናትና ስለ ኢትዮጵያ ድምጻችን አልነጠፈም፣ የሕዝብ ልጆች ነንና ከሕዝብ አልተለየንም፣ ብሔራዊ አጀንዳ ነውና የዐባይም ልጆች ነን፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያችን ሲከፋት ያመናል፣ ሕዝባችን ሲቸገር ይርበናል፣ ዐባይ የእኛ ሲሆን እሰየው ያሰኘናል፡፡
ያኔም የታገልነው ለሕዝብ ኑሮ መሻሻል፣ ለሀገር እድገት ነበርና ዛሬም ከሀገርና ሕዝብ ጉዳይ የተለየን እንዳልሆንን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡ እንጉርጉሯችን ኢትዮጵያ ናት፡፡ ኢትዮጵያችን ደግማ ደጋግማ በዐባይ ትኩራ፣ ትበልጽግ፣ ትደግ እንላለን፡፡ የተስፋችን ዛፉ አሁንም ይለምልም፡፡
ዐባዬ በርታ በርታ፤
እንድትሆነን ጋሻ መከታ፤
ጠላትም ይፈር ባንተ ችሎታ፤
አለን ልጆችህ ቆመን በተርታ
ፍጻሜህ ልማት የማታ ማታ
ኢትዮጵያ ትብራ ባንተ ስጦታ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
ፈጣሪ ሀገራችንን እና ሕዝባችንን ይጠብቅ!!!
ያ ትውልድ ተቋም፡፡
ሐምሌ 16 ቀን 2012 ዓ.ም.
Email: yatewlid@gmail.com
website: http://www.yatewlid.com, http://www.yatewlid.org
Facebook: - Yatewlid