የአዲሱ ኢትዮጵያ ካቢኔ ጂኦግራፊያዊ ፍትሃዊነት ዳሰሳ

መስከረም 24 ቀን 2013 ዓም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አዲሱን ካቢኔ ፓርላማው እንዲያጸድቀው ሲያቀርቡ የእያንዳንዱን እጩ ስም፣ የትውልድ ሥፍራ፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ የትምህርት ዝግጅት፣ አንዲሁም የሥራ ልምድ መረጃዎችን ይፋ አድርገው ነበር። ከዚህ ቀደም “ብሄር” የሚለው መገለጫ ባልተለመደ መልኩ በ “ትውልድ ሥፍራ” መተካቱ ፖለቲካዊ አንድምታዎች እንደሚኖሩት ቢታመንም ሁነቱ ለዚህ አጭር የዳሰሳ ጥናት መነሳሳትንና ለትንታኔው ሂደት ደግሞ አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል።

Politics

Abiy Ahmed R takes the oath as he is sworn in as Ethiopian prime minister in Addis Ababa, Ethiopia, on Oct. 4, 2021. Source: Getty

የአንድ እጩ የትውልድ ሥፍራ መገለጹ መረጃውን መሬት ላይ ለመቸከል[1] እና ካርታ ላይ ለማንጠብ ያስችላል። ያ ማለት ደግሞ የእጩውንና የ”ተጓዳኝ ጉዳያትን”[2] በሳይንሳዊ የትነት[3] መንገድ በመጠቀም የሹመቱን ሥፍራዊ ፍትሃዊነት[4] ለመተንተን እድል ይሰጣል። በውጤቱም የምልከታ መረጃን[5] ተጠቅሞ ቀለል ባለ መንገድ ግንዛቤን ያስጨብጣል።

በቀጣዩ ቀናት የ61 ሚኒስቴር ዴኤታዎች በተሾሙበት ወቅት የትውልድ ሥፍራቸው ይፋ ይደረጋሉ ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር። ሆኖም መረጃው ባለመገኘቱ በዚህ ዳሰሳ ላይ የቀረበው ትንተና የሚያተኩረው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በ23 የካቢኔ አባላት የትውልድ ሥፍራ ላይ ብቻ ተመርኩዞ ነው።

በርካታ መንግሥታት የካቢኔ አባላቶቻቸው ስብጥር የየአገራቸውን መልክ እንዲመስል ጥረት ቢያደርጉም ብዝሃዊነታቸው ፍጹም ሆኖ አያውቅም። ለምሳሌ የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ምክትላቸውን ጥቁሯን ሴት ካመላ ሐሪስን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኋይት ሃውስ ማምጣታቸውንና ብዝሃነት ያላቸውን የካቢኔ አባላት በማዋቀራቸው “የእኔ አስተዳደር ስብጥሩ አሜሪካንን እንዲመስል የገባሁትን ቃል እየጠበቅሁ ነው” ብለው ተናግረው ነበር።

ከባይደን ቀደም ብሎ ቢል ክሊንተንም ሆነ ባራክ ኦባማ የበኩላቸውን ጥረቶቸ አድርገዋል። ሆኖም ግን የቅርቡን የአሜሪካ ታሪክ ስንመለከት እንደ ዶናልድ ትራምፕ ካቢኔ ኢ-ብዝሃዊነት አልታየም። 24 አባላት ካሉት የትራምፕ ካቢኔ 19ኙ ነጫጭ ወንዶች ነበሩ።  

የተፈጥሮ አካባቢ ብዝሃነቱ ከበረከተበት አገር፣ በተደራቢነት የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የባህል ብዝሃነት ከተነባበረበት አገር፣ አንዲሁም የፖለቲካው ቅኝት ዋልታ ከረገጠበት አውድ የካቢኔ አባላትን ፍትሃዊነት ማረጋገጥ ፈታኝ መሆኑ አይዘነጋም። ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ሌሎች “አካታችና ፍትሃዊ” ብለው የገለጹት ካቢኔ ውክልና የራሱ ውስንነት እንዳሉትም መዘንጋት የለበትም። 

የካቢኔው እጩዎቹ የተዘገኑት በምርጫው ከተሳተፉት ወደ 33 ሚሊዮን ሕዝብ (የትግራይና ሶማሌ ክልሎችን ሳይጨምር) ውስጥ ሳይሆን ቁጥራቸው አራት ሚሊዮን ገደማ ከሚገመቱ የብልጽግና ፓርቲ አባላት መሃል ነው (በዘመነ ኢሕአዴግ ሕወሓትን ጨምሮ ወደ 5 ሚሊዮን አባላት እንደነበሩ ልብ ይሏል)። ይህ ማለት ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ከተሰጡት ሶስት ቦታዎች በስተቀር በካቢኔ አባልነት ለመመረጥ ዕድል የነበራቸው ድርሻ ሲሰላ ከመራጩ ሕዝብ ውስጥ ከ12% (4/33 X100) በታች ካለበት የብልጽግና ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኞች ቋት ውስጥ ነው።

እርግጥ ነው መራጩ ሕዝብ ድምጹን ለብልጽግና ፓርቱ ሰጥቷል የሚል መከራከሪያ ሊቀርብ ይችላል። ሆኖም ግን ፖለቲካዊ ተምሳሌትነቱ ታይቶ ካልተወደሰ በቀር የካቢኔው ርዕዮተ ዓለማዊ ስብጥሩ ብዝሃነት እንደጎደለው መካድ አይቻልም። ሌሎች መንግሥታትም ቢሆኑ የሚያደርጉት ይህንኑ ስለሚሆን ላይደንቅ ይችላል። ሆኖም የዚህ ዳሰሳ ትኩረት በርዕዮተ ዓለማዊ ብዝሃዊነት ላይ አይደለምና በሥፍራዊ ፍትሃዊነቱ ጉዳይ እናተኩራለን። 

የኢትዮጵያ ምድር ውክልናና ፍትሃዊነት።

የካቢኔ አባላቱ የትውልድ ሥፍራ ስርጭት በተለይም በትሪያንግሉ ውስጥ ተወስኖ ይገኛል (ምስል 1)። በርዝመቱ (በሎንጂቲዩድ) ከደቡባዊው ነጌሌ (5.33ዲግሪ ሰሜን) እስከ ሰሜናዊው አዲግራት (14.27ዲግሪ ሰሜን)፣ በስፋቱ (በላቲቱዩድ) ደግሞ ከምዕራቡ ቄለም (34.80 ዲግሪ ምስራቅ) እስከ ምስራቁ ገለምሶ (40.52 ዲግሪ ምስራቅ) ተሰራጭቷል። የሰሜን-ደቡብ ስርጭቱ የተሻለ መመጣጠን ቢታይበትም የምዕራብ-ምስራቅ ስርጭቱ ግን አለመመጣጠንን ያሳያል። በውጤቱም የካቢኔው ስርጭት ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ አጋድሎ ይታያል።

ሆኖም ግን ይህንን ካርታ ብቻ ተመርኩዞ ከድምዳሜ መድረስ ለስህተት ይዳርጋል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ አየር ንብረት፣ አፈር፣ የውሃ አካላት፣ አፅዋት፣ የመሬት አቀማመጥ፣ ወዘተ ከሥፍራ ሥፍራ እንደሚለያይ ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሰፋፈርም አንድ ወጥ ሆኖ የተሰራጨ አይደለም። ስለዚህ የካቢኔውን የትውልድ ሥፍራ ጂኦግራፊያዊ ፍትሃዊነት ለመገምገም ከሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን ጋር አነባብሮ መተንተን ያስፈልጋል።
Map 1
ምስል 1፡ የአዲሱ ካቢኔ አባላት የትውልድ ሥፍራ ስርጭት። በምስሉ የካቢኔው አባላት በትሪያንግሉ ውስጥ ብቻ ሲወሰኑ በተጨማሪም ወደ ምዕራብ የአገሪቱ ጎን አመዝነው ይታያል። Source: D.Kassahun
ቆለኛ ወይንስ ደገኛ?

ከባህር ጠለል በላይ የሚኖረው ከፍታ የአየር ንብረትን በቀጥታ ከሚወስኑ ምክንያቶች አንዱና ዋንኛው ነው። በተለይ በኢትዮጵያ ተጽኖው እጅግ ወደር የለውም። የአየር ንብረት የሰውን ባህሪ ከሚቀርጹ አንዱ ነው”[6] እንዲሉ በቅርቡ ከቻይና፣ አውስትራሊያ፣ ብሪታኒያና አሜሪካ በተሰበሰበ ናሙና ላይ በተካሄደ ሳይንሳዊ ጥናት እንደተረጋገጠው ወይና ደጋዊ የሙቀት መጠን ባላቸው አካባቢዎች ያደጉ ሰዎች በተስማሚነት፣ በህሊና ተገዥነት፣ በተረጋጋ ስሜታዊነት፣ ወዘተ የላቀ ውጤት አስመዝግበዋል።

የከፍታ መጠንን ተመርኩዞ የኢትዮጵያ ሥነ ምድርን በአምስት ቀጣናዎች መክፈል ይቻላል። በረሃ (ከ500 ሜ. በታች)፤ ቆላ (ከ500 - 1,500 ሜ.)፣ ወይና ደጋ (ከ1,500 - 2,300 ሜ.)፣ ደጋ (ከ2,300 - 3,200 ሜ.)፣ ውርጭና ቁር (ከ3,200 ሜ. በላይ) ናቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብ አሰፋፈርም እንደ ከከፍታው መጠን ጋር ጉድኝት ቢኖረውም ትስስሩ “ቀጥተኛ ጉድኝት”[7] አይደለም።

ለምሳሌ በወቅታዊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር (2020 በዩናይትድ ኔሽንስ ትንበያ) ላይ በተመረኮዘ ትንተና 81% የሚሆነው ሕዝብ የሰፈረው በወይና ደጋና በደጋ ቀጣናዎች ውስጥ ነው። በዚሁ ተመሳሳይ ሥፍራ የ95.7% የካቢኔው አባላት ዕትብት ተቀብሯል። በወይና ደጋው 55.7% የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ የሰፈረበት ሲሆን፣ በዚሁ ሥፍራ 80% የካቢኔ አባላት መፍለቃቸው በማወቅም ይሁን በሌላ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የትኩረት አቅጣጫ ወይና ደጋ-ተኮር ያስመስለዋል። ጉዳዩ ከቀደምት የ“አካባቢያዊ ፍጹም ወሳኝነት”[8] መርሆ ጋር ይመሳሰል ይሆን?

እንደ ጥንታዊ ግሪኮች አሰራር ከልከኛ የአየር ሙቀት ሥፍራ የሚመጡ ሰዎች ጥሩ ጭንቅላት (ከፍተኛ አይ ኪው) ስለሚኖራቸው ለአስተዳደር፣ ለዳኝነት፤ ለእንደራሴነት እንዲታጩ ያደርጉ ነበር። በተቃራኒው ወደ ፅንፍ የተጠጋ ሙቀትም ሆነ ቅዝቃዜ ከሚበረታባቸው ሥፍራ የሚመጡ ሰዎች ከጭንቅላት ይልቅ ከፍተኛ የአካል ጥንካሬ ያካበቱ ናቸው ተብሎ ስለሚታመን አካላዊ ብቃትን ለሚጠይቁ የሥራ ዘርፎች ይታጩ ነበር። ሆኖም ግን ይህ አመለካከት በጊዜ ሂደት ወድቆ፣ አካባቢ የራሱ ተጽዕኖ ቢኖረውም ሰዎች በሳይንስና ቴክኖሎጂ አየታገዙ ከጊዜ ወደ ጊዜ አኗኗራቸውንና አካባቢያቸውን የበለጠ ለኑሮ አመቺ እያደረጉ በመምጣታቸው “አካባቢን መግራት ይቻላል”[9] በሚል መርህ ተተክቷል።
Map 2
ምስል 2፡ የኢትዮጵያ ሕዝብና የካቢኔው ስርጭት ከምድር ከፍታ ጋር ያለው ትስስር። ህዝቡና ካቢኔው በተመሳሳይ መልኩ ከከፍታው ጋር የሚያሳዩት ስርጭት የደወል ቅርጽን የያዘ[10] ሲሆን የመካከለኛው ከፍታ (1,500 - 2,300 ሜ.) የመኖሪያ አመቺ ሥፍራ ሆኖ ይታያል። Source: D.Kassahun
ከመሃል ነው ከዳር አገር?

በተለይም በአዳጊ አገራት በመሃልና በዳር አገር መሃል የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል ልዩነት ጎልቶ ይታያል። አልፎ አልፎ ጉዳዩ ውጥረትን ፈጥሮ የፖለቲካ አጀንዳ ስለሚሆን ጉዳዪ በርካታ የአካዳሚ ዘርፎች ይጠናል። ከነዚህም ውስጥ አንዱ “ማዕከል-ተጓዳኝ” ሞዴል[11] ነው። የዳር አገር አካባቢ ከስልጣኔም ሆነ የሃብት መጠን ብዙውን ጊዜ ኋላ ቀር ስለሚሆን በተግባርም ባይሆን በቃል ደረጃ “ለዳር አገር ተቆርቋሪ ነኝ” የሚሉ በርካታ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያችንም ነበሩ፣ አሉ።

የአዲሱ ካቢኔ ሲሰባሰብ ትኩረቱ ከመሃል ነው ከዳር አገር?

በዚህ ጥናት “የሕብረ ቀለበታዊ ቋት”[12] የሚባል የመረጃ ማጠናቀሪያ መንገድን በመጠቀም የካቢኔው አባላት ትውልድ ሥፍራ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ያላቸውን የርቀት ጠባይ በየ150 ኪሜ ርቀት ለይቶ ለማስላት ተሞክሯል። እዚህ ላይ ርቀት ሲባል ጠመዝማዛውን አውራ ጎዳና ተከትሎ ሳይሆን በወፍ በረር የቀጥታ መስመር ተለክቶ ነው። በውጤቱም 91% የሚሆኑት የካቢኔ አባላት ትውልድ ሥፍራ ከአዲስ አበባ 450 ኪሜ ርቀት ውስጥ ተገኝቷል (ምስል 3)።

በተመሳሳይ በዚህ የርቀት ክልል ውስጥ 86% የኢትዮጵያ ሕዝብ ይኖርበታል። የሚገርመው ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ምክትላቸውን ጨምሮ የበርካታ ዕጩዎች (43.5%) መገኛ ከአዲስ አበባ ከተማ ርቀቱ ከ150 እስከ 300 ኪሜ ባለው ሥፍራ መሆኑ ነው። በአንጻሩ ከ600 ኪሜ ርቀት በኋላ አንዳችም እጩ አለመኖሩ ርቀቱ ከመሃል አገር እየረዘመ ሲሄድ የካቢኔ አባል የማፍለቅ አቅሙ እየሟሸሸ[13] ስለሚሄድ ይሆን?

በግርድፉ ሲታይ አዲሱ ካቢኔ ብዙም የመሃል ብዙም የዳር አገር ያልጎላበት ስብስብ ይመስላል። ሆኖም ከአዲስ አበባ ከተማ ባለው ርቀት የታየው የካቢኔ ስርጭት ከአጠቃላይ የህዝቡ ስርጭት ጋር በአያሌው የተዛመደ ነው ማለት ያስደፍራል።
በግርድፉ ሲታይ አዲሱ ካቢኔ ብዙም የመሃል ብዙም የዳር አገር ያልጎላበት ስብስብ ይመስላል።
Map 3
ምስል 3፡ ከአዲስ አበባ ከተማ በተለያየ የርቀት ቀጣና ውስጥ የሚገኘው የካቢኔ አባላትና የአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስርጭት ጠባይ። የካቢኔውም ሆነ ህዝቡ በሁለተኛው ዞን ውስጥ በተመሳሳይ መልኩ በርክተው ይታያሉ። Source: D.Kassahun
ከለውጡ ባለውለታዎች መሃል?

ከ 2006 እስከ 2010 ዓም ድረስ የኢሕአዴግን መንግስት በመቃወም በመላ አገሪቱ በሚባል መልኩ ያልተቋረጠና ጠንካራ ተቃውሞ እንደተካሄደ ይታወሳል። ሆኖም ግን በሁሉም ሥፍራ የሚኖር ዜጋና ማኅበረሰብ በእኩል መጠን አልተፋለመም፣ አልታሰረም፣ አልደማም፣ አልሞተም በሚል የታሪክ ሽሚያ ውስጥ የገቡ እንደነበሩ አይካድም። “ለድሉ መገኘት ብዙ መስዋዕትነት (የአንበሳውን ድርሻ) ከፍለናል” ከሚሉ አካባቢዎች ጋር የፓርላማው ድርሻ ትስስር (ኮረሌሽን) ይኖረው ይሆን የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል።

በተጠቀሱት ዓመታት በኢትዮጵያ የተመዘገቡ 3,070 ግጭቶችን ልክ እንደ ምስል ሶስት በየ150 ኪሜ ርቀት ተለይቶ በመሰላቱ ውጤቱ በሰንጠረዥ 1 ቀርቧል። የቀጣና ሁለት (ከ300 እስከ 450 ኪሜ) አና ሶስት (ከ150 እስከ 300 ኪሜ) የግጭት መጠኑ ድምር 64.5% ሲሆን በተጓዳኝ የፓርላማው ድርሻም በተመሳሳይ 65.5% ሆኗል። ሆኖም ግን ከትስስር መረጃ ላይ ተንስቶ ምክንያታዊ ግንኙነትን መበየን አይቻልም። ተጨማሪ ጥናት ይጠይቃልና። 

ሰንጠረዥ 1፡ ከአዲስ አበባ ከተማ በተለያየ የርቀት ቀጣና ውስጥ የተመዘገበው የግጭቶችና የካቢኔ አባላት ብዛት ንጽጽር። ግጭቶቹም ሆነ የካቢኔው አባላት በሁለተኛውና በሶስተኛው ዞኖች (150 450 ኪሜ) በርክተው ይታያሉ።

 

ከአዲስ አበባ ያለው ርቀት (ኪሜ)

የግጭቶች ብዛት

የግጭቶች ብዛት ፐርሰንት

የካቢኔ ብዛት በፐርሰንት

<150 

752

24.5

22.1

150 - 300

990

32.2

43.5

300 - 450

991

32.3

21.7

450 - 600

239

7.8

8.7

600 - 750

93

3.0

0

750 - 900

5

0.2

0


 

የስበት ማዕከሉስ የት ነው?

አንዳንዴ በፖለቲካው ዙሪያ የባስልጣናቱ “አስኳል”[14] የት ይሆን ያለው? ተብሎ ይጠየቃል። የዕምብርቱ ሥፍራ የፖለቲካውን ስበት አሊያም ኢ-ፍትሐዊነት ቀምሮ ስለሚያሳይ የመረጃው ተፈላጊነት አያጠያይቅም። አልፎ አልፎ የአገር አንድነት አደጋ ላይ የሚወድቀውም ሆነ የመገንጠል ጥያቄ የሚመነጨውም ባመዛኙ ከዚህ ሁነት በመነሳት ነው።

የኢትዮጵያ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት አስኳል ሲሰላ “የምሶሶው ችካል”[15] የሚያርፈው ከወለንጪቲ ከተማ በስተምስራቅ አቅጣጫ 23 ኪሜ ገደማ ርቆ ነው (ምስል 4B)። በሌላ በኩል የካቢኔ አባላቱን የትውልድ ሥፍራ ኮርድኔት አማካይ ሥፍራ ስናሰላው የስበቱ ማዕከል የሚያርፈው ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ሆኖ ከጊንጪ ከተማ በስተሰሜን ወደ 37 ኪሜ ርቆ ነው (ምስል 4A)።

በሁለቱ የስበት ማዕከላት መሃል የ191 ኪሜ ገደማ ክፍተት መኖሩ የካቢኔው አባላት የትውልድ ሥፍራ አማካይ ቦታ በእጅጉ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ማጋደሉን ያሳያል። እንደ ካቢኔው የማጋደል መጠን የተጋነነ ባይሆንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ስርጭት የስበት ማዕከልም ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ የተሳበ ብቻ ሳይሆን ከ2005 (ምስል 4D) እስከ 2020 (ምስል 4C) ባሉት ጊዜያት እንኳ የስበቱ ማዕከል ወደ ደቡብ አቅጣጫ በጥቂቱ መንፏቀቁን መገንዘብ ይቻላል።

በኢትዮጵያ የግዛት ታሪክ የአስተዳደር ማዕከሉ ከአክሱም ተነስቶ በጊዜ ሂደት ወደ ደቡብ አቅጣጫ መጓዙ የአገሪቱን የስበት ማዕከል ወደ አዲስ አበባ መጎተቱ ይታወሳል። በሃገሪቱ ባለው የተበላለጠ ዲሞግራፊ ሳቢያ የህዝቡ የስበት ማዕከል ግን በአንድ ቦታ የማይጸና ነው። ወደ ደቡብ የመጓዙ ምስጢርም ከሰሜኑ ይልቅ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ እድገት በፍጥነት በማደጉ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጥናት ላይ ቀደም ባሉ ዓመታት የነበሩ የሕዝብ ስርጭት መረጃዎች ቢታከሉበት ደግሞ እጅግ በተሻለ ሁኔታ የ”ጊዜ ሂደት ለውጡን”[16] መገንዘብ ይቻላል።
በኢትዮጵያ የግዛት ታሪክ የአስተዳደር ማዕከሉ ከአክሱም ተነስቶ በጊዜ ሂደት ወደ ደቡብ አቅጣጫ መጓዙ የአገሪቱን የስበት ማዕከል ወደ አዲስ አበባ መጎተቱ ይታወሳል።
Map 4
ምስል 4፡ የካቢኔ አባላት የስበት ማዕከል ከአገሪቱ አጠቃላይ የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ስርጭት ማዕከላት ያለው ጉድኝት። በካርታው የካቢኔው አባላት ትውልድ ሥፍራ ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ በእጅጉ አዘንብሎ ይታያል። Source: D.Kassahun
የወንዜ ልጅ?

የአገራችን ወንዞች ለማኅበረሰቡም ሆነ ለዜጎች እንደ አንዱ የቁርኝት መገለጫ ሆኖ ስለማገልገሉ “የወንዜ ልጅ” የሚባለውን ዘይቤ መጥቀስ ይቻላል። የኢትዮጵያን ግዛት ለማካለል ከሚቀርቡ አማራጭ መስፈርቶች አንዱ ተፋሰስን መሰረት ያደረገ በመሆኑ የካቢኔ አባላቱን የተፋሰስ ቁርኝት መመርመሩ ተጨማሪ መረጃን ያፈልቃል። በጥናቱ ውጤት ከ15 ወንዝ ሸለቆዎቻችን መሃል እንደ የአባይ ተፋሰስ በርካታ የካቢኔ አባላትን ያበረከተ የለም።

የአባይ ተፋሰስ ስምንት እጩዎችን (34%) ሲያፈልቅ በሁለተኛ ሥፍራ ከሚገኘው የአዋሽ ተፋሰስ እጩዎች ብዛት በእጥፍ ይልቃል። ሁለቱ ተፋሰሶች 28% የሚሆነውን የአገሪቱን የቆዳ ስፋት ሲሸፍኑ በካቢኔ ድርሻ ግን 52% ይሸፍናሉ። የሸበሌና የገናሌ ተፋሰሶች 20.3% የአገሪቱን የቆዳ ስፋት ሸፍነው ሳለ እያንዳንዳቸው አንድ እጩ ብቻ ነው ያበረከቱት።
ከ15 ወንዝ ሸለቆዎቻችን መሃል እንደ የአባይ ተፋሰስ በርካታ የካቢኔ አባላትን ያበረከተ የለም።
የብላቴ፣ የደንከል እና የኦሞ ተፋሰሶች እያንዳንዳቸው ሁለት የካቢኔ አባላትን ሲያቀርቡ የተከዜ፣ የመረብ፣ የሰገን፣ የአትባራና የአንገረብ ተፋሰሶች አንዳችም እጩ ማቅረብ አልቻሉም። ዋናው ነገር የስፋት መጠን ሳይሆን የተፋሰሱ መገኛ ሥፍራ ይመስላል ከካቢኔው አባላት የተሳሰረው።

ማጠቃለያ

ስምንቱ የካቢኔ አባላት ሴቶች መሆናቸው ከሌሎች ሃገራት አንጻር የፆታ ፍትሃዊነትን ያሳያል። የተሿሚዎቹን ዕውቀትና ክህሎት በምሉዕነት ባያመላክትም በትምህርት ዝግጅት ከፍ ያለ ደረጃ ተስተውሏል። ከኦነግ ፓርቲ እጩ በስተቀር ሌሎቹ የማስተርስ ወይንም የፒኤችዲ ዲግሪን ያነገቡ ናቸው። ለሶስት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የሚኒስትርነት ሥልጣን መጋራቱም ለአካታችነቱ አስረጅ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል።

ሆኖም ግን የጂኦግራፊያዊ ጠባዩን ተመርኩዞ በተደረገው ዳሰሳ የካቢኔ ፍትሃዊነቱ መጠነኛ መፋለስ ቢያሳይም ስርጭቱ ከሞላ ጎደል ፍትሃዊ ነው ሊባል ይችላል። የ61 የሚኒስቴር ዴኤታዎቹ የትውልድ ሥፍራ መረጃ በዚህ ጥናት ተካቶ ቢሆን ኖሮ የተሻለ ውጤት ሊገኝ ይችል ነበር። ይህ አጭር ዳሰሳ ያመነጨው መረጃ ወደፊት በቀጣይነት ለሚመሰረቱ ካቢኔዎች “የመነሻ ማመሳከሪያ”[17] ሆኖ ለተሻለ አካታችና ወካይ የካቢኔ ምስረታ በጎ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

 የግርጌ ማስታወሻ

[1] “መቸከል” geo tagging የሚለውን ቴክኒካዊ ቃል ወክሏል። ትርጓሜውም በተለያዩ የመረጃ ምንጮችን  (ለምሳሌ ፎቶዎች፣ ቪዲዮዎች፣ ዌብሳይቶች፣ የጽሁፍ መልዕክቶች፣ ወዘተ) በጂኦ ኮርድኔት አበልፅጎ ስርጭታቸውን በካርታ ላይ ለማስፈርና ሥፍራዊ  ትንተና ለማካሄድ  የሚያስችል ዘዴ ነው።.

[2]  “ተጓዳኝ ጉዳያት” spatial attributes የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ይወክላል።

[3] “ሳይንሳዊ የትነት” የሚለው ሃረግ “የት” ከሚለው ቃል መንጭቶ the science of where የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ወክሏል።

[4] “ሥፍራዊ ፍትሃዊነት” spatial representativeness የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ይወክላል።

[5] “የምልከታ መረጃ” visual information  የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ይወክላል። 

[6] “የአየር ንብረት የሰውን ባህሪ ከሚቀርጹ አንዱ ነው” የሚለው አባባል Climate molds character ከሚለው የተለመደ አባባል በቀጥታ ወደ አማርኛ የተመለሰ ነው። 

[7] በጽሁፉ “ቀጥተኛ ጉድኝት” የሚለው ገለጻ linear relationship የሚለውን ሃረግ ለመተካት ነው። ትርጓሜውም የስታቲስቲካዊ ቃል ሆኖ የሁለት መረጃዎች (variables) ጉድኝት በግራፍ አማካይነት ሲታይ ቀጥተኛ መስመርን የሚፈጥር ነው። ይህ ማለት አንዱ ቫርያብል ከፍ ወይንም ዝቅ ሲል ሌላኛው ቫርያብልም አብሮ በተመሳሳይ ከፍና ዝቅ ይላል።  

[8] የ“አካባቢያዊ ፍጹም ወሳኝነት” Geographical determinism  የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ይወክላል። ትርጓሜውም የሰው ልጅ ታሪክ፣ ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ ወዘተ እጣ ፈንታ የሚወሰነው በሚኖርበት አካባቢ (አየር ንብረት፣ መልክዓ ምድር፣ ወዘተ)  ነው የሚል እሳቤ ነው። ይህ ፍልስፍና ለቅኝ ገዢዎች አመቺ መሳሪያ ሆኗል ይባላል።

[9] “አካባቢን መግራት ይቻላል” የሚለው ሃረግ Geographical possibilism የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ይወክላል። ትርጓሜውም ምንም እንኳ የተፈጥሮ አካባቢ በሰዎች ህይወት ላይ ጫና ቢኖረውም ባህልና የኢኮኖሚ እድገትን ግን በሁለንተናዊነት አይወስነውም የሚል የፍልስፍና ነው። ይህ መርህ ቀድሞ የነበረውን “አካባቢያዊ ፍጹም ወሳኝነት” የተካ ነው።  

[10] “የደወል ቅርጽን የያዘ” የሚለው ሃረግ bell-shaped curve  የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ለመግለጽ ነው።

[11] የ“ማዕከል-ተጓዳኝ” ሞዴል centre–periphery model  የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ለመግለጽ ነው።

[12] የሕብረ ቀለበታዊ ቋት ዘዴ multiple ring buffer analysis  የሚለውን የGIS ቴክኒካዊ ዘዴ ነው።

[13] የማፍለቅ አቅሙ እየሟሸሸ የሚለው ሃረግ distance decay effect  የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ለመግለጽ ነው።

[14] አስኳል nucleus የሚለውን ቃል ለመተካት ነው።

[15] “የምሶሶ ችካል” centroid  የሚለውን ቃል ለመተካት ነው።

[16] የ”ጊዜ ሂደት ለውጥ” temporal trend የሚለውን ቴክኒካዊ ሃረግ ለመግለጽ ነው።

[17] “የመነሻ ማመሳከሪያ” benchmark የሚለውን ቃል ለመተካት ነው።

የጸሐፊው ኢሜይል አድራሻ፡ daniel.kassahun@gmail.com

 

 

 


Share

Published

By Daniel Kassahun (PhD)

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service