ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ አውስትራሊያ ታይዋንን አስመልክቶ ያላት አቋም ያልተቀየረ መሆኑንና በ"አንድ ቻይና" ፖሊሲ ፀንታ ያለች መሆኑን አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአውስትራሊያን አቋም ዳግም ግልፅ ለማድረግ ግድ የተሰኙት ቻይናን ካስቆጣው የዩናይትድ ስቴትስ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት ጋር ተያይዞ ነው።
ከአፈ ጉባኤ ፔሎሲ ጉዞ ጋር ተያይዞ ቻይና በታይዋን ዙሪያ ወታደራዊ ሮኬቶችን መወንጨፏ ለአካባቢው አገራት አሳሳቢ ሆኗል። ፍኖም ፔን ካምቦዲያ በሚካሔደው የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገራት ማኅበር 47ኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራት ጉባኤ ታዳሚዋ የአውስትራሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔኒ ዎንግ ውጥረቶችን እንዲረግቡ ጥሪ አቅርበዋል።
***
የአውስትራሊያ ፌዴራል መንግሥት የአየር ለውጥ ረቂቅ ድንጋጌው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ ድጋፍ አግኝቶ ማለፉን ተከትሎ "የአሠርት ዓመት ውዥቀት" አክትሟል ሲል ገለጠ።
ረቂቅ ድንጋጌው ፀድቆ በሕግነት ግብር ላይ ለመዋል የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ይሁንታን ማግኘት ግድ ይለዋል። ሆኖም 12 የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ያለው ግሪንስ ፓርቲ ለድንጋጌው መፅደቅ ድጋፉን እንደሚቸር በይፋ አስታውቋል።
ረቂቅ ድንጋጌው ለሕግነት ለመብቃት 12 የግሪንስ ፓርቲንና አንድ የግል የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባልን ድምፅ ይሻል።
ለረቂቅ ድንጋጌው ድጋፉን የነፈገው የተቃዋሚ ቡድን መሪ ፒተር ዳተን የመንግሥት 43 ፐርሰንት የአየር ብክለት ቅነሳ ዒላማ የኃይል ዋጋ ጭማሪን ሊያስከትል እንደሚችል አመላክተዋል።
ሆኖም የታዝማኒያ ሊብራል ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ብሪጅት አርቸር ከፓርቲያቸው የተቃውሞ አቋም ተነጥለው ድምፃቸውን ለሌበር መንግሥት ሰጥተዋል።