የዘውድ ምክር ቤት ፕሬዚደንቱ ኢትዮጵያውያንና የእንግሊዝ የክብር እንግዶች በተገኙበት ሕዳር 7 በተዘከረው የጎንደር ድል የእራት ግብዣ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ሕልፈተ ሕይወትና መፈናቀልን አስመልክቶ ትልቁ ጦርነት ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑን አመላክተዋል።
ይህንኑ ሲገልጡም፤
"ባለፉት ዓመታት 1.5 ሚሊየን ያህል ሰዎች ተገድለዋል፤ 26 ሚሊየን ያህል ከቤታቸው ተፈናቅለዋል። በዩክሬይንና እሥራኤል ሕልፈተ ሕይወትና ትርጉመ ሕይወት ሁኔታዎች ዓለምን በሐዘኔታ እንቀላቀላለን፤ ስለምን የመከራን ምንንነት እናውቃለንና" ብለዋል።
በዘንድሮው የጎንደር ድል በዓል በአገረ እንግሊዝ ንጉሥ ቻርልስ ሳልሳዊ ሞገስ አላባሽነት ለጎንደር ድል በክብር ለወደቁት የእንግሊዝና ኢትዮጵያ አርበኞች መዘከሪያ በዊንድዛር ቅዱስ ጊዮርጊስ ፀሎት ቤት ልዑል ኤርሚያስ ሳሕለ ሥላሴ አዲስ ዝክረ መታሰቢያ መርቀው ከፍተዋል።

ልዑልነታቸው ለንደን አጠገብ በሚገኘው በዊንድሶር ቤተመንግስት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተመቅደስ ውስጥ፤ ጃንሆይና የኢትዮጵያ አርበኞች ከታላቋ ብሪታኒያና የቅርብ አጋሮቿ ጋር በመሆን በ1934 ዓ.ም ተዋግተው የተቀዳጁትን ድል የሚያበስርና የሚያስታውስ፤ በብረት ላይ የተቀረጸ የጎንደር ድል የጽሁፍ ቅርስ ለከተማው በማበርከት አስመርቀዋል፡፡

ልዑል ኤርሚያስ የጎንደርን ድል የመታሰቢያ ቅርስ ሽፋን የገለጡት የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ፤ ልጅ ዓለማየሁ ቴዎድሮስ መቃብር ፊት ለፊት ነው።
በወቅቱም፤ የቤተመቅደሱ ካህን ጆናታን ኩር በእንግሊዝኛና በግዕዝ ቋንቋዎች ከመጽሀፈ ሄኖክ በመጥቀስ ፀሎት ማድረጋቸውንና ልዑል ኤርሚያስም ለጆናታን ኩር የኢትዮጵያንና የታላቋ ብሪታኒያን የጦር አጋርነት የሚያበስረውን የታላቁን የጎንደር ድል መዳሊያ መሸለማቸውን የዘውድ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
በሌላም በኩል ለልዑል ኤርሚያስ "የለንደን ከተማ ነፃነት" ሽልማት በለንደን ከተማ ሕዳር 7 ተበርክቶላቸዋል።

ቀደም ሲልም በ1947 አያታቸው ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ተመሳሳይ ሽልማት ከለንደን ከተማ ተቀብለዋል።

