እናት ፓርቲ ነሐሴ 5 ባወጣው መግለጫ በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ በፈንቲ ረሱ ዞን፣ በጋሊኮማ ከተማ፣ ጋሊኮማ ጤና ጣቢያ ጦርነት ሸሽተው በተጠለሉ ንጹሓን ላይ ሐምሌ23 2013 የደረሰው አሰቃቂ ጭፍጨፋ በእጅጉ እንዳሳዘነው ጠቅሶ፤ እስከአሁን እየወጡ ባሉ መረጃዎች የጭፍጨፋው ሰለባዎች ከጦርነቱ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ከ240 በላይ ሕጸናት፣ ሴቶችና አረጋውያን መሆናቸውን የተረዳ መሆኑን ገልጧል።
ፓርቲው ድርጊቱን "ቅስም ሰባሪ" ብሎ የጠራው ሲሆን ሕወሓትንም በፅኑ አውግዟል።
አያይዞም "ለተጎጂ ቤተሰቦች፣ ለክልሉ መንግስትና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እየገለጸ፣ ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን ይመኛል። ፓርቲያችን ለተጎጂ ቤተሰቦች ለሚደረግ እገዛ ሁሉ አባላቱንና ደጋፊዎቹን በማስተባበር የአቅሙን አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ቃል ይገባል፤ መንግስትም ይህንኑ ሚናውን እንዲወጣ አበክሮ ይጠይቃል" ብሏል።
አክሎም "በዚህ አጋጣሚ መርጦ የሚያለቅሰው ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብና መገናኛ ብዙኃን ድርጊቱን በሚገባው ልክ እንዲያወግዝ እንጠይቃለን" ሲል ውግዘትና ማሳሰቢያውን አቅርቧል።