ዛሬ ለዓለም አቀፍ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ማብራሪያ በስካይላይ ሆቴሌ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳነሱት የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ ለሚፈልጉ ዜጎች መጥተው ማገዝ እንዲችሉ ቪዛም እንደሚዘጋጅላቸው ተናግረዋል።
አምባሳደር ሬድዋን የተባበሩት መንግስታት እርዳታዎችን ለማድረስ ወደ ትግራይ የሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖች እየተፈተሹ አዲስ አበባ ሲያርፉና ሲነሱ አስፈላጊው ትብብር እንደሚደረግላቸው ገልፀዋል። ይሁን እንጅ በትግራይ ለሚያጋጥማቸው ማንኛውም ነገር መንግስታቸው ኃላፊነቱን እንደማይወስድ ተናግረዋል።
በቴሌኮምና ባንኮች መከፈት ጉዳይም ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ማብራሪያ እንደተሰጠ የገለፁት ሬድዋን ለጋሾች የራሳቸውን ኔትወርክ መጠቀም እንደሚችሉ ፣ በክልሉ የባንክ አገልግሎት መልሶ ማስጀመርን ግን መንግስት ለጊዜው እንዳላሰበ ለትርፍ የተቋቋሙ በመሆናቸው ባንኮችንም አስገድዶ ስራ ጀምሩ ማለት እንደማይችል ይሁንና ለመክፈት ፈቃደኛ የሚሆኑ ካሉ ለመተባበር ዝግጁ መሆናቸውን አስታወቀዋል።
"ህወሓት የመብራትና የስልክ አገልግሎት መስመሮችን ቆርጦ ነበር። ለጥገና የተሰማሩ በአስሮች የሚቆጠሩ መሃንዲሶችንም ገድሏል። እነዚህን መሰረተ ልማቶች መንግስት ጠግኖ ወደ አገልግሎት መልሶ ነበር። በመሆኑም ህወሓት ይህንን የግድያ ወንጀል እየቀጠለ ባለበት በዚህ ሁኔታ የመብራትና የስልክ አገልግሎት ወደ ስራ ለማስገባት የፌዴራል መንግስት እንደሚቸገር ለዲፕሎሚቲክ ማኅበረሰቡ አስረድተናል" ብለዋል።
የፌዴራል መንግስት በትግራይ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ያሳለፈው በቁጥር ጥቂት የሆኑትን ወንጀለኞች ለመያዝ ተብሎ ብዙ ዋጋ መክፈል እንዲቆም መሆኑን የገለፁት አምባሳደር ሬድዋን ይሁንና መንግስታቸው የተናጠል የተኩስ አቁም ቢያደርግም በኮረም በኩል የትግራይ ልዩ ኃይል ተኩስ ከፍቶ እንደነበር ገልፀዋል።
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]