የትግራይ ክልል ምክር ቤት ሕወሓትንና ሶስት ተጨማሪ የፖለቲካ ድርጅቶችን አካትቶ ስድስተኛውን የክልል ምክር ቤት ምርጫ ለማካሔድ በወሰነው መሠረት አምስት የኮሚሽን አባላትን ሰይሟል።
በክልል ምርጫ ኮሚሽነርነትና አባልነት የተመደቡትም፤
- መምህር ሙሉወርቅ ኪዳነ ማርያም - የትግራይ ክልል የምርጫ ኮሚሽን ኮሚሽነር
- ወ/ሮ ጽጌረዳ ዲበኩሉ - የትግራይ ክልል የምርጫ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር
- ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ ፀሓየ - የትግራይ ክልል የምርጫ ኮሚሽን አባል
- ዶ/ር ጸጋ ብርሃን - የትግራይ ክልል የምርጫ ኮሚሽን አባል
- አቶ መሐመድ ሰዒድ ሐጎስ - የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽን አባል ናቸው።
ክልሉ በሚያካሂደው ምርጫ ከሕወሓት በተጨማሪ የሚሳተፉት ድርጅቶች ባይቶና፣ ሳልሳይ ወያነ ትግራይና ውናት ነፃነት ትግራይ ናቸው።
በክልሉ በአንጋፋ ተቃዋሚነት የሚታወቁት ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲያዊነትና ሉዓላዊነት ፓርቲና የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በምርጫው እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል።
ቀደም ሲል የትግራይ ክልል ምክር ቤት “ኮቪድ 19ኝን እየተከላከለ 6ኛውን ዙር ምርጫ ለማካሄድ የወሰነ በመሆኑ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በሚያዘው መሰረት ቦርዱ ውሳኔውን ተቀብሎ ምርጫውን እንዲያስፈፅም፣ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስፈልግ የሰው ሃይልና ሎጂስቲክስ ዝግጅት እንዲያደርግ እና ውሳኔውን ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቀን” ሲል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርቦ ቦርዱ ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽ 102 (1) ንና የቦርዱን ስልጣንና ኃላፊነትን የወሰነውን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 አንቀጽ 7.1 ን ጠቅሶ ምላሽ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አያይዞም ጁን 25 የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምርጫ በተናጠል ላካሂድ ጥያቄን ያልተቀበለው መሆኑን አስመልክቶ በሰጠው ምላሽ፤
1. 6ኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ እንዲራዘም ምክንያት የሆነው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሁኔታ እንደገና ተገምግሞ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ እስኪረጋገጥ ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል ምርጫ አያካሄድም፡፡
2. በተጨማሪም ከላይ እንደተገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፓለቲካ ፓርቲዎችን መመዝገብ፣ መቆጣጠር እና ማስተዳደር፣ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳን ማውጣት፣ የምርጫውን ከተጽእኖ ነጻ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ማስፈጸም ስልጣን ያለው ብቸኛ ተቋም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳን፣ አፈጻጸምንም ሆነ ተያያዥ ሁኔታን የሚወስነውም ቦርዱ ብቻ ነው፡፡በመሆኑም የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ውስጥ 6ተኛውን ዙር የክልል ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ ለመስጠት እንዲሁም ቦርዱ ይህንን ውሳኔውን ተቀብሎ ሊያስፈጽም ይገባል የሚልበት ህጋዊ መሠረት የለውም
ማለቱ ይታወሳል።