የዩናይትድ ስቴት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ የቻይናን ማስጠንቀቂያ አሌ ብለው ወደ ታይዋን መዝለቅ በቤጂንግና ዋሽንግተን መካከል ውጥረትን አስፍኗል።
ከ25 ዓመታት በፊት ከቀድሞው የአሜሪካ አፈ ጉባኤ ኒዊት ጊንግሪች የታዋን ጉብኝት በኋላ አንድ ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣን ታይዋንን ሲጎበኝ ይህ የናንሲ ፔሎሲ ጉዞ የመጀመሪያው ነው።
በቻይና መንግሥት ዕይታ የውጭ አገር መንግሥት ባለስልጣን የታይዋን ጉብኝት የሚታየው ለደሴቲቱ ሉዓላዊ ዕውቅንና ከመስጠትና ቻይና ግዛቴ በምትለው የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት አንፃር ነው።
የአፈ ጉባኤ ፔሎሲ የታይዋይን ጉብኝት ውጥረትን ከማባባስ ባሻገር ለአሜሪካ የሚያስገኘው ረብ ያለው ጥቅም የለም የሚል ትችት ቢያስከትልም፤ ፔሎሲ ከሪፐብሊካንና ዲሞክራት ፖለቲከኞች ዘንድ ድጋፍን አላጡም።
ይህንኑ የፔሎሲ ጉብኝት አስመልክቶ የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔኒ ዎንግ ሁነቱ በተለይም ታይዋን ለሚገኙ ዜጎች "በጣሙን አሳሳቢ" መሆኑን አመላክተው አሜሪካና ቻይና ውጥረቱን ለማርገብ እንዲጥሩ አሳስበዋል።
አክለውም፤ "ሁላችንም የምንሻው በታይዋን ሰርጥ አካባቢ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ነው" ብለዋል።
የአውስትራሊያ "የአንድ ቻይና" ፖሊሲም የፀና መሆኑን ተናግረዋል።