ተከታታይ ጦርነቶች ባንድ ስሌትና ቀመር አይጓዙምናና ተፋላሚዎቹ ከቀድሞ ተሞክሮዎቻቸው እየተማሩ (it’s a leraning process) የበለጠ ጉዳት ለማድረስ የተሻሻለ ስትራቴጂ ይነድፋሉ፤ ቀጣዩም ጦርነት አስከፊ ይሆናል። ይህ አስከፊ ሰቆቃ እያቆበቆበ ያለው ደግሞ ለመጪው ክረምት ነው። ጦርነቱ ባምናው ክረምትም ተከስቶ ነበርና የሚከተለውን ተከልሶ ቀረበ አባባል ሊያስታውሰን ይችላል።
የዝናብ ወቅትና የርስበርስ ዕልቂት፤
ቀጠሮ እንዳላቸው ሲገባ ክረምት።
ማን ያውቃል………?
ቦ ጊዜ ለኩሉ።
ለሁሉም ጊዜ አለው። ቅዱስ መጽሃፉም “ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው …” ይላል። በአገራችን የቅርብና የሩቅ ታሪክ በርካታ ከጊዜ/ወቅት ጋር የሚያያዙ በርካታ ግጥምጥሞሽ አሉ። አንዱ አስረጅ ጦርነቶች ከተወሰኑ ወራት ጋር የመያያዛቸው ጉዳይ ነው።
የግንቦትን እንውስድ፣ ጣጣ የበዛበትና ደም መገበር የለመደ ነው። አሰቃቂ የነበረው የንጉስ ምንሊክ እና የንጉስ ተክለ ሃይማኖት ጦርነት እምባቦ ላይ የተካሄደው በግንቦት 1874 ዓ.ም፣ በደርግ ላይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተደርጎ በርካታ ጄኔራሎች በአስመራና በአዲስ አበባ ከተማ ያለቁበት በግንቦት ስምንት 1981 ዓ.ም፣ በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተሳትፋችኋል በተባሉ አስራ አራት ጄነራሎች ላይ የሞት ፍርድ ተበይኖ በምሽቱ የተረሽኑት በግንቦት አሥራ አንድ 1982 ዓ.ም፣ የኢህአዴግ አማፂ ቡድን ደርግን አስወግዶ ሥልጣን የያዘው በግንቦት ሃያ 1983 ዓ.ም፣ ወዘተ ነበር።
በተመሳሳይ የካቲትም በበርካታ ጦርነትና አመጾች ታሪክ የተንቆጠቆጠ ነው። የታላቁ ዐድዋ ጦርነትና ድል በየካቲት 1888 ዓ.ም፣ በአዲስ አበባ ከተማ የግራዚያኒ ጭፍጨፋ የተካሄደው በየካቲት 1929 ዓ.ም፤ የአብዮቱ ፍንዳታ በየካቲት 1966 ዓ.ም፣ የካራማራ ጦርነትና ድል በየካቲት 1970 ዓ.ም፣ ወዘተ።
ሌላው ይቅርና ድሮ ድሮ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚዘወተር ቀላል የማይባል ዛቻስ “ቆይ ሰኔ ሰላሳ ይድረስና እንተያያለን” ወቅትን ጠብቆ የሚከሰት አይደል?
በአገራችን የክረምት ወራት ከእርሻ ሥራ በቀር ለሌሎች በርካታ ጉዳያት አይመረጥም። ትምህርት ቤቶች፣ ፍርድ ቤቶች፣ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ ወዘተ በክረምት ዕረፍት ናቸው። ዕረፍቱ በክረምት እንዲሆን ያስገደደው በዝናቡ ጠባይ ሳቢያ ይመስላል። በርካታው የኢትዮጵያ ደጋማ ስፍራ ከ75% በላይ ሕዝብ የሚኖርበት ነው። በክረምቱ ወራት ከባድ ዝናብ ስለሚጥልበት ከጭቃው ባሻገር ወንዞቹ ካፍ እስከ ገደፋቸው በውሃ ይሞላሉ።
ይህ የደጋ ክፍል የሰፈረው በአምባ (ጠረጴዛማ መሬት) ላይ ሆኖ አምባው በበርካታ ወንዞችና ጅረቶች የተቆራረጠ ብቻ ሳይሆን እጅግ ተዳፋትነት ባላቸው ሸለቆዎች የታጠረ ነው። በክረምቱ ቀበሌ ከቀበሌ፤ አውራጃ ከአውራጃ ተነጣጥሎ ይቆያል። ጦርነት ቢታሰብ እንኳ ሊካሄድ የሚችለው ከተቃራኒው ቡድን ሳይሆን ከምድረ ገጹ ጋር ይሆናል፤ ሲቀጥልም ገበሬውን በባዶ ሆድህ ተዋጋ ማለት ስለሚያስቸግር።
ጥናቶች እንደሚመሰክሩት ገበሬውን አስከፊ የምግብ እጥረት የሚገጥመው በክረምት ወቅት ነው። የመስቀል በዓል በብዙ የአገራቸን ሥፍራዎች ደምቆ የሚከበርበት አንዱ ምክንያት ዝናቡና ወንዙ ቀንሶ፣ እሸቱ ደርሶ ተለያይቶ የከረመው ህዝብ ወንዞቹን እየተሻገረ ከወራት በኋላ እርስ በርስ መገናኘት በሚፈጠረው ደስታ አይደል?
መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፣
እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ። … አይደል የሚባለው?
ክረምት ጦርነት የማይካሄድበት ወቅት ስለመሆኑ የቀደመውን የነገሥታት አስተዳደር ዘይቤን መለስ ብሎ ማየት ይቻላል። ነገሥታቱ መዲናቸውን በ1263 ዓ.ም ከላሊበላ ወደ ሸዋ ተጉለት ካመጡ በኋላ የሰለሞናዊው ሥርወ መንግሥት አንድ ቦታ ለረዥም ጊዜ በሰላም ረግቶ መቀመጥ ተስኖት ነበር። በተለይም በ16ኛው ክፍለ ዘመን የግራኝ አህመድ መስፋፋት ወቅት ነገሥታቱ ከሸዋ ተነስተው ወደ ጣና ሃይቅ አካባቢ በመሸሽ ከሁለት ምዕተ ዓመታት በላይ በተዘዋዋሪነት ቆይተዋል።
በበጋው ወራት ነገሥታቱ እስከ ሃያ ሺህ የሚቆጠሩ ታጣቂ እያስከተሉ ከስፍራ ስፍራ ተዘዋውረው ግብር እያስገበሩና ህዝቡን እያስተዳደሩ ይከርማሉ። በክረምት ወራት አጃቢው ወደየቀዬው ይበተንና ነገሥታቱም ወደ መረጡት ሥፍራ እየሄዱ ዕረፍት ያደርጋሉ። ገበሬውም ወደ እርሻው፣ ጦርኛውም ወደ ጥሞናው። በጋው ተመልሶ ሲመጣ የዘመቻው ጉዳይ ሕይወት ዘርቶ ዑደቱ ይቀጥላል።
የኢትዮጵያ ቀደምት ጦርነቶች የተከሰቱት ባመዛኙ በበጋ ወራት ነው። ዐፄ ምንሊክ የታላቁን የአድዋ ዘመቻን ሲያውጁ ክረምቱ ከወጣ በኋላ በመስከረም ሆኖ ጦርነቱ የተካሄደው በየካቲት ሃያ ሶስት 1888 ዓ.ም፣ ሁለተኛው የጣልያን ጦርነት የተከፈተው መስከረም ሃያ ሶስት በ1928 ዓ.ም፣ የታላቋ ሶማሊያ ጦር ምስራቅ ኢትዮጵያን ከወረረ በኋላ፣ በእናት አገር ጥሪ የመልሶ ማጥቃት የካራማራ ድል የተገኘው በበጋው ወር የካቲት 1970 ዓ.ም፣ ሻዕቢያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ሲባል ደርግ የቀይ ኮከብ ዘመቻን በይፋ የከፈተው በጥር 1974 ዓ.ም፣ የህወሓት ዐማፂ ቡድን ትግራይን ተቆጣጥሮ ወደ መደበኛና ሜካናይዝድ ጦር ጎልብቶ ወደተቀረው የኢትዮጵያ ክፍሎች ለመዝለቅ ኢሕአዴግን በግንቦት 1981 ዓ.ም መስርቶ ስኬታማ የሆኑ ዘመቻዎችን ያከናወነው በበጋ ወራቶች ነበር፡ “ዘመቻ ቴዎድሮስ” በየካቲት፣ “ዘመቻ ቢሉሱማ ወልቂጡማ” በመጋቢት፣ “ዘመቻ ዋለልኝ” በግንቦት፣ ወዘተ።
የክረምቱ ጣጣ።
በክረምት ወራት ጦርነት ሲካሄድ ሠራዊቱ ላይ የሚደርሰው አደጋ ይበረክታል። በአንደኛው የዓለም ጦርነት የ“ሶሜ ጦርነት” (Battle of the Somme) ሲካሄድ የህብረት ኃይሎች (Allied Forces) ከአንድ ሚሊዮን በላይ የፈረንሳይ፣ የእንግሊዝና የጀርመን ወታደሮች አልቀዋል። በታላቅ ዝናብ ሳቢያ ሠራዊቱ በጭቃ ተውጦ ከአካባቢው ፈጥኖ መውጣት ተስኖት ነበር።
የሁለተኛው ዓለም ጦርነትን ምዕራፍ የቀየረው የ”ባርባሮሳ ዘመቻ” (Operation Barbarossa) የተጀመረው በሞቃታማው ሰኔ 1941 እ.ኤ.አ በጀርመን ጦር ቆስቋሽነት ነበር። ዓላማው የቅዝቃዜው ወቅት ሳይገባ የሶቪየት ሕብረትን ግዛት ወርሮ የሞስኮ ከተማን በቅፅበታዊ ጥቃት ለመቆጣጠር ነበር። ታዲያ ምን ያደርጋል በጥቅምት ወር ላይ ከፍተኛ ዝናብ ዘንቦ መንገዱ ጭቃ በመሆኑ የጀርመን ታንኮችና የተለያዩ ማሽኖች እስከ ሁለት ሜትር በጠለቀ የጭቃ አረንቋ ውስጥ ታነቁ እንጂ። ጉዞው በመንቀራፈፉ ሳቢያ ሞስኮ ከተማ ሳይደርሱ አደገኛው የበረዷማ ቅዝቃዜ ወቅት በታህሳስ ወር ገባ። አጥንት ዘልቆ ለሚገባው ቅዝቃዜ ያልተዘጋጁት የጀርመን ወታደሮችና መሳሪያዎቻቸው መንቀሳቀስም ሆነ ጥይት መተኮስ አልቻሉም። በውጤቱም የጀርመን ጦር እንዳያንሰራራ ሆኖ አከርካሪው ተሰብሯል።
የአየር ንብረት ለውጥ ጥናቶች የሚጠቁሙት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሙቀት መጠኑ እየጨመረ ሲመጣ የጦርነት ቁጥሩም አብሮ ከፍ እያለ ሄዷል። ለምሳሌ ላለፉት 30 ዓመታት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት የተካሄዱ አስከፊ ጦርነቶች ከአየር ሙቀት መጨመር ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አሳይተዋል። በሳይንሳዊ ትንበያዎቹ መሰረት የአየር ሙቀቱ ተባብሶ ስለሚቀጥል የጦርነት ዕድሉም እያሻቀበ ይሄዳል።
በ2030 እ.ኤ.አ በአፍሪካ ሊከሰት የሚችለው የጦርነቶች ቁጥር በ54% ከፍ እንደሚል ትንበያ ተደጓል። ስለሆነም በበጋው ወራት ጣትና ቃታ ወርቅና ሰም ቢሆኑ ምን ይገርማል?
ወደ አገራችን ዜናዎች እንመለስና የታቀደው የጦርነት ጣጣ ሊከሰት የተዘጋጀው እንደ ልማዳችን በግንቦት ወይንም በየካቲት ወራት አይደለም። እንደ ታሪካችንም በበጋ ወራት የሚከሰትም አይደለም። ሳይንሳዊው ጥናት እንደነገረን የሙቀት መጠኑ ከፍ ከሚልበት ወቅት ጋር የተዛመደም አይደለም። ታዲያ የዚህ የክረምት ጦርነት ጉዳይ እንቆቅልሽ አይሆንም?
ባለፈው ሰኔ የመከላከያ ሠራዊት ባልተጠበቀ ውሳኔ መቀሌን ለቆ ከወጣ በኋላ የህወሓት ጦር ከትግራይ ክልል በመነሳት ወደተቀረው የአገሪቱ ክፍል ደፍሮ እንደማይስፋፋና ቢያስብ እንኳ የሞት ጉዞ (suicide mission) እንደሚሆን በርካታ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች በልበ ሙሉነት ተንብየው ነበር። አይፈረድባቸውም፤ ወቅቱ ክረምት ነበራ! ህወሓት ደግሞ “እንደ ዱቄት ተበትኗል” ተብሎ ነበር።
ሆኖም ግን በወቅቱ የአሜሪካኑ መንግሥት ተራድኦ ድርጅት USAID (የህወሓትን መሪዎችን የሂሳብ ማወራረድ ፍላጎት ካየ በኋላ ይመስላል) አቅርቦት በነበረው ግምገማ ጦርነቱ ሊቀጥል እንደሚችል፣ የክረምቱ ወራት ደግሞ ለትግራይ ተዋጊዎች አመቺ እንደሚሆን፣ በአንፃሩ ደግሞ የመከላለያ ሠራዊቱ ሜካናይዝድ ጦር ተንቀሳቅሶ ለመዋጋት አዳጋች እንደሚሆንበት፣ ወዘተ ጠቁሞ ነበር።
እንደተባለው አልቀረም የህወሓት ጦር በሃገርና በውጪ ፕሮፓጋንዳ ታጅቦ በርካታ የአማራ እና የአፋር ገጠርና ከተሞች በስኬት እንደተቆጣጠረ ተመልክተናል። አንድ የዩኒቨርሲቲ መምሀር ጓደኛዬ በአካባቢው በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያጫውተኝ የህወሓት ሠራዊት ይጓጓዝ የነበረው ጋራ ጋራውን ሆኖ ጭጋግን እንደ ከለላ በመጠቀም ከዕይታ ውጪ በመሆን እንደነበር ነው። በተቃራኒው ደግሞ ለቅኝትም ሆነ ለጥቃት በበጋው ሲያገለግል የነበረው የድሮን ወሬ በክረምቱ አልተደመጠም።
የድሮን ጉዳይ።
ድሮኖች የጠላት ይዞታን ለመቃኘትም ሆነ ለማጥቃት እጅግ ተመራጭ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ናቸው። የወታደራዊ ዒላማዎቹ ጂኦ-ኮርዲኔት ቀድሞውኑ የሚታወቅ ከሆነ እሰየው፡ ኦፐሬሽኑ ቀላል ነው። ሆኖም በጦርነት ወቅት ጂኦ-ኮርዲኔታቸው ገና ያልታወቀ በርካታ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ወታደራዊ ዒላማዎች ይፈጠራሉ። ድሮኖቹ ልክ እንደ ዐይናችን እኒህን ዒላማዎች መለየት፣ ማየት እና መሰብሰብ የሚያስችላቸውን ሴንሰር ይጠቀማሉ።
በድሮን ላይ የሚጠመደው ሴንሰር ዓይነት ኦፕቲካዊ (electro-optical sensor) ወይንም ሬዳራዊ (radar sensor) ሊሆን ይችላል። በኦፕቲካዊ ሴንሰር የሚገኘው መረጃ ከዐይናችን ተፈጥሯዊ ዕይታ ጋር የተቀራረበ ነው። ልክ በፎቶ ወይንም በቪዲዮ ካሜራ እንደተቀረፀ ምስል ሁሉ ማንም ሰው በድሮኖቹ መረጃ ታግዞ የጎጆ ቤትን ከታንክ፤ የተሳቢ ጭነት መኪናን ከመኖሪያ ቤት በቀላሉ መለየት ይችላል።
በተጨማሪም በኢንፍራሬድ ሞገድ የምሽት መረጃዎችን መቀበል ያስችላል። በተለይ የምስል አንባቢው በፎቶግራሜትሪ ዕውቀትና ክህሎት የጎለበተ ከሆነ ደግሞ አንድ ግለሰብ ዶማ ይሁን ጠመንጃ ስለመያዙ በድሮኑ ሴንሰር መለየት ይቻላል። ችግሩ ግን ኦፕቲካላዊ ሴንሰሮች በደመና ሽፋን ወቅት ዳፍንታም ይሆናሉ። በተቃራኒው ደግሞ የሬዳራዊው ሴንሰር የራሱን ሞገድ ልኮ ስለሚቀበል ዳመና ሽፋን አያስተጓጉለውም። ችግሩ ግን ከሬዳር የሚገኘውን ጥሬ መረጃ በቀጥታ መተርጎም አይቻልም።
በድሮኑ የተመዘገበው መረጃ ወይ በኢንተርኔት አማካይነት አሊያም ድሮኑ ራሱ ወደ ቤዝ ስቴሽን ሊያደርሰው ይገባል። በመቀጠልም ይህ መረጃ አስፈላጊ የሆኑ ሶፍትዌሮች በተጫኑባቸው ኮምፒዮተሮች ላይ ተመርኩዞ በባለሞያ ተተንትኖ ውጤቱ ለወታደራዊ አዛዦች ብሎም ለድሮን ኦፕሬተሮች በሚያመች መልኩ መድረስ ይኖርበታል። ቅኝቱ እንደሚሸፍነው የቆዳ ሥፋት መጠን፤ የባለሙያ ብዛትና ጥራት፣ የኮምፒዮተርና ሶፍትዌር ብዛትና ብቃት፣ ወዘተ ሳቢያ የሚፈለገው መረጃ ሊዘገይ፤ ዒላማውም ሥፍራውን ሊቀይር ይችላል። በመሆኑም የሬዳር መረጃ የተሻለ ጥራት ቢኖረውም እንደ ዕይታዊ መረጃ በቅፅበት ውሳኔ ሊከወንበት አይቻልም።
ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ድሮኖች ሁለቱንም ዓይነት ሴንሰሮች ሊታጠቁ ቢችሉም የትኛው ዓይነት ሴንሰር ነው በሥራ ላይ ያለው የሚለው ጥያቄ ስለመጪው ክረምት ጦርነት እሳቤዎች መጠነኛ ፍንጭ ይሰጠናል።
ሶስት መረጃዎችን አንመልከት።
አንደኛ- በባለፈው ክረምት ጦርነት ወቅት የድሮን ጥቃት ወሬ አለመኖሩ።
ሁለተኛ- “ድሮኗ በድጋሚ ሥራ ጀመረች” ተብሎ ያደመጥነው ዜና ክረምቱ አልፎ የጠራ ሰማይ ከታየ በኋላ መሆኑ።
ሶስተኛ- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጦርነቱ በተጀመረ በሶስተኛው ሳምንት አካባቢ በፓርላማ ቀርበው ስለጦርነቱ ሲያስረዱ ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ በዕኩለ ለሊት አካባቢ ሲቹዌሽን ሩም ሆነው የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት በሐገረ ማርያምና በአቢ አዲ ከተሞች መሃል ሲሸሹ በድሮን እየቃኟቸው ሳለ ያልደመሰሷቸው ቤተሰቦቻቸውና የታገቱ የመከላከያ ሠራዊት አባላት አብረው እንደነበሩ ሲናገሩ መረጃው ኦፕቲካዊ እንጂ ሬዳራዊ እንዳልነበር በቀላሉ መገመት ይቻላል።
ከላይ የተገለፁትን ጭብጥ እና መላ ምቶች ተመርኩዘን መናገር የምንችለው ምንም እንኳ የክረምት ጦርነት የሁለቱንም ተዋጊዎች ፈተና አስከፊ ቢያደርገውም ሁሉም ቡድን በእኩል መጠን አይጎዳም። በአንፃራዊነት ክረምቱ የመከላከያ ሠራዊትን የበለጠ ሊጎዳው ይችላል ተብሎ ስለሚታመን የህወሓት ሠራዊት የጦርነት አፒታይቱ ከፍ ቢል አይደንቅም። “ህወሓት በክረምት ጦርነት ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ ነው” የሚለው ዜና ምንጭም የተጠቀሰውን ሥሌት ተመርኩዞ ሊሆን ይችላል።
የመከላለያ ሠራዊት መሪዎች እንደነገሩን ከዚህ ቀደም የህወሓት ሠራዊት ሰሜን ሸዋ ከደረሰ በኋላ በመልሶ ማጥቃት ወደ ትግራይ እንዲያፈገፍግ ሲደረግ ሠራዊቱን እንጂ ከባድና ሜካናይዝድ መሣሪያውን ማሸሽ አልቻለም። ይህን አባባል እውነት ከነበር የመጪው ውጊያ የሚካሄደው በነፍስ ወከፍ መሣሪያ ብቻ በመሆኑ በርካታ የተዋጊ ማሰለፍን ይጠይቃል። እርሱን ለመመከት ደግሞ በመከላከያ፣ በልዩ ኃይል፣ በፋኖ ወዘተ የሚሳተፈው ቁጥር ስለሚበረክት በሁለቱም ወገን የጦርነቱ ቀውስ የበለጠ ሊባባስ ይችላል።
ሌላው ይቅርና ገና የአምናውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት እንኳ በዝርዝር አላሰላነውም።
እልህ ምላጭ ያስውጣል።
መጪው ክረምት ትራጀዲ የሚያመጣብን ከሆነ ለምን መስዋዕትነት ተከፍሎ በውይይት አይፈታም?
መልካም ሀሳብ ቢሆንም እጅግ ፈታኝ ነው። ጦርነት የዜጎችን ዕልቂትና ንብረት ውድመት የሚያስከትል ብቻ ሳይሆን ለአንዳንዶች ዝና እና ትሩፋትንም ያስገኛል። ለምሳሌ የዜና አውታሮችና የዩቱብ ተንታኞች የተከታታይ ቁጥራቸው አሻቅቦ ኪስ የሚያሞቅ ፍራንክ ይዞ ስለሚመጣ አንዳንዶቹ ማናቸውም የሰላም ጥረት ጅማሬን በበጎ መልኩ ማየት አይፈልጉም። ለምን ቢባል በሰላም ወቅት ሰበር ዜና አይኖርማ! ታዲያ የተከታይና የገቢ ድርቅ ቢከሰት ዩቱበሮችን አያስከፋም?
ሌላው ችግር በሁለቱም “ሁሉም ነገር ቀድሞ ወደነበረው መመለስ አለበት” የሚለው ቅድመ ሁኔታ ነው።
ችግሩ “ቀድሞ” የሚባለው ቀን ወይንም ዘመን መቼ ነው?
ሁለቱም የየራሳቸው መስፈርት አላቸውና ውይይቱን ያወሳስበዋል። ሁሉም ቡድን “የኔ” ብሎ የሚቆርጥለት የቀን ተመን ለራሱ የተሻለ ትርፍ፣ ለባላንጣው ኪሳራ ሲያስገኝ እንጂ የጋራ ትርፍ ቅድሚያ አይሰጠውም። አሸናፊነቱ በመቶ ፐርሰንት እንዲደመደም የሚፈልገው ተደራዳሪው ብቻ ሳይሆን ከጀርባ ያለው “ተፅዕኖ ፈጣሪ” ጭምር ነው።የአንድ አገር ዜጎች ነን እና ከመቶ ፐርሰንት በታች የሆነ ድልን ወይንም ድርሻን ለመቀበል ፈቃደኛ የሆነ ተደራዳሪ እንዲፈጠርና እንዲጎለብት የአሜሪካ ወይንም የአውሮፓ ሳይሆን ዕምነት ሊጣልባቸው የሚችሉ የአገር በቀል አደራዳሪዎች ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ተሞክሮ ከነበረው ጥረት ይልቅ በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ቢቻል መልካም ይሆናል።
እርግጥ ነው ድርድር ከእልህ ነጻ መሆንን ይጠይቃል፤ በእኛ ባህል ደግሞ እልህ የተትረፈረፈ ባህሪ ነው። ለምሳሌ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በባድሜው ውዝግብ ወቅት የኢትዮ-ኤርትራ ተደራዳሪ ባላስልጣናትን ባህሪ በተመለከተ በወቅቱ ከነበረው የአሜሪካ አምባሳደር ሰማሁ ብለው ሲናገሩ ኢትዮጵያውያን (ኤርትራን ጨምሮ) እጅግ በጣም እልኽኛ ስለሆኑ እርስበርስ ለማግባባት ፍፁም አዳጋች ስለመሆናቸው ባንድ ፅሁፋቸው እንዳነበብሁ አስታውሳለሁ።
በመጨረሻም።
ብናምንም ባናምንም በባለፈው በጋም ሆነ ክረምት ወራት በተካሄዱ መጠነ ሰፊ ጦርነቶች በበርካታ መመዘኛዎች ወድቀናል። ከስህተት በመማር በዘንድሮው የክረምት ጦርነት የበለጠ ውጤታማ ለመሆን በወታደራዊ ዝግጅት ላይ ትኩረት መደረጉ የተለመደና የሚጠበቅ ክስተት ነው።
ሆኖም ግን የዕርቅና ውይይቱ አጀንዳስ? ከባለፈው የላቀ ዝግጅትና ጥረት ሊደረግለት አይገባም?
እንደውም የበለጠ አትራፊ የሚሆነው የሰላም ጥረቱ “ፕላን ኤ” እንጂ “ፕላን ቢ” ሲሆን አይደለም። ክረምት የሚያምርበት ደግሞ በሬ ሲጠመድበት ነው። ክረምትን እንኳንስ በጦርነት አባክነነው ይቅርና አርሰንበትም ራሳችንን በበቂ መጠን መመገብ አልቻልንም። ዛሬ በሃገሪቱ የተከሰተው አስደንጋጭ የምግብ ዋጋ ግሽበት አንዱ መንስዔስ በርካታ ዜጎች በጦርነቱ አዙሪት በመዘፈቃቸው ሳይሆን ይቀራል?