የወልቃይት ጉዳይ (ለውይይት መነሻ)

የወልቃይት ችግር እንደምን ይፈታ?

Mekonnen Zelelew

Mekonnen Zelelew Source: Supplied

ፕ/ር ዳኛቸው አሰፋን በአካል አላውቃቸውም የፍልስፍና ሙሁር እንደሆኑና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ያስተምሩ እንደነበር አውቃለሁ። በተለያየ መድረክና የዜና ተቋሞች እየቀረቡ በሚያደርጉት ንግግር ከማደንቃቸው ሰዎች አንዱ ናቸው። ይሁን እንጂ እኒህ ምሁር ወልቃይትን በሚመለከት የሰነዘሩት ሃሳብ አገር አቀፍ ንግግር መስሎ አልታየኝም ። ፕ/ር ዳኛቸው እንዲህ ነበር ያሉት “ ባርህርዳር ጎንደርና ደባርቅ ደርሼ ነው የተመለስኩት፣ አንዳንድ የወልቃይት ሰዎችም አግኝቼ ነበር፣ የጻፏቸውም ግጥሞች የወልቃይት ሁኔታ እንደሚገልጹ ተገንዝቤያለሁ። ወልቃይት መብቱ ተረግጧል ቋንቋው ማንነቱ ተወስዶ የሌላ ማንነት የግድ እንዲቀበል የተደረገ ፣ነጻነቱ የተገፈፈ ህዝብ ነው ። የአማራ ጭቆና ቋጠሮው የሚጀምረው ከወልቃይት ነው። የአድዋው ጦርነት በወልቃይት መደገም አለበት ።” ነበር ያሉት።

ፕ/ር ዳኛቸው ስለ ወልቃይት ህዝብ መብት ማጣት መጨቆን መግለጻቸው ትክክል ሆኖ ግን ለምን የወልቃይት ችግር በጦርነት እንዲፈታ ፈለጉ? የወልቃይት ጭቆና የሁሉ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ቀርቶ እንዴት የአማራ ቋጠሮ ብቻ ይሆናል? እንዴትስ ትግሪኛ ተናጋሪው ትግራዋይ እና አማርኛ ተናጋሪው አማራ በዘር ቋንቋ ከሁለት ተከፍሎ የአድዋው ጦርነት ዓይነት እንዲደገም ፈለጉ? ከዚህ ጦርነት በኋላ ወልቃይት የሚያገኘው ጥቅም ምንድን ነው? ድህነትና መበታተን ወይስ ነፃነትና ሰላም? አድዋ ላይ የተካሄደው ጦርነት በኢትዮጵያውያንና በጣልያን መካከል ነበር።

ፕ/ር ዳኛቸው ወልቃይት በሚመለከት ከተናገሩ በኋላ በሌላ መድረክ ሆነ እንጂ እንደሳቸው አጠራር አቦዮች ማለት የህወሓት መሪዎች መኩራራትና ማንያለብኝነት በመግለጽ ያደረጉት ንግግር በተለይ ለኔ የህወሓት ታጋይ ስለነበርኩ ውስጤን የነካ ንግግር ነበር ወድጄልዎታለሁ። የወልቃይት ህዝብ ፕ/ር እንደገለጹት መብቱና ነጻነቱ የተገፈፈ በጭቆና ውስጥ የሚኖር መሆኑ ለኢትዮጵያ ህዝብ እኔም የድርሻየን በተለያየ ወቅት በዜና ተቋሞች ለመግለጽ ሞክሬአለሁ ፣ በጽሑፍም በተደጋጋሚ ለንባብ አብቅቼ አለሁ ። ሰሚ ባለስልጣን አልተገኘም እንጂ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1993 ዓ/ም ከ 19 ዓመት በፊት በዜጋ መጽሔት “ወልቃይቴው የህወሓት ታጋይ” በሚል ርዕስ ስለወልቃይት የራሱ እምነት ባህል ወግ ልምድና አስተሳሰብ በሚረዱ ወገን ሳይሆን በማያውቃቸውና በማያውቁት አካላት በመተዳደሩ የሚያጋጥመው ያለ የፍትህ እጦት ከፍተኛ እንደሆነ የሚያስረዳ ጽሑፍ ነበር።
እንደ ፈረንጅ አቆጣጠር በግንቦት 17, 2015 “ የህወሓት ክልል ለወልቃይት ጸገደ ልማት ወይስ ጥፋት ” በሚል
ሀ/ ወልቃይት ትግርኛና አማርኛ እንደሚጠቀም ከሁለቱ አንዱን ጥሎ አንዱን ለመያዝ እንደማይፈልግ
ለ/ አማርኛ ቋንቋ እንደ ኢትዮጵያዊ እንደሚጠቀም አማርኛ የኢትዮጵያ ቋንቋ ነው ብሎ የወሰደ ህዝብ ነው።
ሐ/ የህወሓት መሪዎች የፈጸሙት የአድልዎ የመሬት ወረራና በደል በዝርዝር የሚያስረዳ ነበር ።
ሶስተኛው በፈረንጅ አቆጣጠር በነሐሴ 06, 2017 “ ያለ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊ መሆን አይቻልም “ በሚል ርዕስ
ሀ/ የህወሓት ጉዞ አና የመሪዎቹ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አንድነትና ባገር ጥቅም ፣ አቋም የለሽ መሆንና ያሳዩት ክህደት
ለ/ በትግራይ ህዝብና በህወሓት፣ በህወሓትና በሰራዊቱ የነበረው ሁኔታ ለያይቶ አለማየት በትግራይ ህዝብ ላይ ያደረሰው የተሳሳተ እይታ ከፍትኛ መሆኑን የሚጠቁም ነበር።

በኢትዮጵያ የአስተዳደር ለውጥ በመምጣቱ ምክንያት ከውጪ ሃገር ወደ ሃገር ቤት እንደተመለስኩ ከትግራይ ክልል አስተዳዳሪ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጽ/ቤታቸው በመገኘት ወልቃይት በሚመለከት በሰፊው ተነጋግረናል። እሳቸውም የተፈጸሙ ስህተቶች እንዳሉ በማመን እርማት ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸውልኛል። ከሳቸው ቀጥሎ ያገኘሁት የወልቃይት ተወላጅ፣ አቶ ፈረደ የሽወንድም ነበሩ ከሳቸው ጋርም የወልቃይትን ጉዳይ በሚመለክት በሰፊው ተወያይተናል። ከዚህ ውይይት በኋላ በተሟላ አይሁን እንጂ ባንዳንድ ቦታ ያገሩ ተወላጆች እንዲያስተዳድሩ መጀመሩን ተመልክቼ አለሁ።

ይህንን ካልኩኝ ዘንዳ እስቲ የወልቃይት እይታ ምን ይመስላል ከክልል በፊትና በኋላ ያለው ትንሽ ልበል ። እኔ የታሪክ ሰው አይደለሁም ያገሩ ተወላጅ ስለሆንኩ የማውቀውን ለመግለጽ ያህል ነው ።
ወልቃይት ከአጼ ቴዎድሮስ እስከ አጼ ሚኒሊክ ዘመነ መንግሥት በወልቃይት ተወላጆች ባህሉ ቋንቋው ወጉ በሚያውቁ መሳፍንትና መኳንንት ብቻ እየተመራ መቆየቱ ይታወቃል።ደጃዝማች አያሌው ብሩ ሰሜንና በጌምድር በሚያስተዳድሩበት ዘመን የወልቃይት አስተዳዳሪ ደጃዝማች መኮነን ወርቅነህ ማሩ ነበሩ። ደጃዝማች መኮነን ወርቅነህ ማሩ ለአርባ ዓመት ዘመን ወልቃይትን ካስተዳደሩ በኋላ በሞት ሲለዩ ደጃዝማች አያሌው ብሩ የሰሜን ተወላጅ የሆኑ ወልቃይትን እንዲያስተዳድሩ ሹመው ነበር ነገር ግን ህዝቡ አልተቀበላቸውም። ምክያቱም እኛን ሊያስተዳድሩ የሚችሉ ባላባቶች እያሉን ለምን ከሌላ ቦታ ተሹመው ተላኩ በማለት ነበር። ደጃዝማች አያሌው ብሩም በህዝቡ ምላሽ ተቆጥተው የወልቃይት ባላባት የተባሉትን በሙሉ ወደ ዳባት እንዲመጡ ካስጠሯቸው በኋላ ከዳባት እንዳይወጡ በቁም እሥር እንዲቆዩ በማዘዝ እርሳቸው የፈለጓቸውን ሰው ተመልሰው እንዲሄዱ ላኳቸው ። ይሁን እንጂ ከታሰሩት ባላባቶች በርካታዎቹ አመለጡ ያላመለጡትም ተገደሉ ። ለምሳሌ ከተገደሉት አንዱ የተከበሩ ፊታውራሪ ነጋሽ ብጫ ሲባሉ ልጆቻቸው በህይወት የሉም እንጂ እነ አዝማች ይርጋ ነጋሽ ግራዝማች ፈረደ ነጋሽ ፊታውራሪ አዛናው ነጋሽ ነበሩ ካመለጡትም አንዱ ለመጥቀስ የተከበሩ ደጃዝማች ደስታ ማሩ ነበሩ ። የደጃዝማች አያሌው ትእዛዝ ሆኖባቸው ወልቃይትን ለማስተዳደር የሄዱት ግለሰብም ለሞት መዳረጋቸው ይታወቃል ።

በአጼ ኃይለስላሴ የ44 ዓመት የግዛት ዘመን ወልቃይት ለመጀመሪያ ጊዜ በቢትወደድ አዳነ መኮነን ለ40 ዓመት ሲስተዳደር ቤተሰቦቻቸውን ወደ ወቀልቃይት በመሾም ለምሳሌ ወንድማቸው ፊታውራሪ አዲሱ መኮንን ፊታውራሪ ነጋን በመሾም ወልቃይትን ለማስተዳደር የቻሉ ሰው ነበሩ ። ቢትወደድ አዳነም ወልቃይትን በዚያ መልኩ ቢያስተዳድሩም ቅሉ ህዝቡ ደስተኛ አልነበረም፣ እሳቸውም ብዙ ዋጋ ከፍለውበታል። ቢትወደድ አዳነ መኮነን አባ ደፋር ፋሽስት ጣልያን አገራችንን በወረረች ጊዜ በጅግንነት ተዋግተው ብዙ የጀግና ሜዳሊያ ያገኙ ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም ቢትወደድ አዳነ መኮነን ሹመታቸው የጀግንነት፣ ያ አገር ወዳድነት እንጂ ባስተዳደር ህዝቡ እምብዛም የሚያደንቃቸው አልነበሩም ። ለምሳሌ ከብዙ በጢቂቱ የህዝቡ ቅሬታ እናንሳ ቢባል ትምህርት ጤና ጣብያ መንገድ ወዘተ የመሳሰሉት ይገኙበታል።

ቢትወደድ የአጼ ኃይለስላሴ መንግሥት የስልጣን ዕድሜ ሲያከትም ወታደራዊውን የደርግ መንግሥት በመቃወም በቃልኪዳናቸው ጸንተው በመሰለፍ ክቡር ህይወታቸውን ሰውተዋል ። ከሳቸው በኋላ የመጡት የወገራ አውራጃ አስተዳዳሪ ወታደራዊው መንግሥት የሾማቸው የወልቃይት ተወላጅ ቀኛ/ ኃይለማርያም ደሴ የደጃዝማች መኮነን ወርቅነህ የእህት ልጅ ሆነው የልጅ ልጅ ናቸው።ቀኛ ኃይለማርያም ደሴ ለሶስት ዓመት የወገራ አውራጃ አስተዳዳሪ ሆነው ሲመሩ ወደ ወልቃይት ሹመው የላኳቸው የወልቃይት ተወላጅ ብቻ ነበሩ ። ይህ ዝም ብሎ የሆነ ጉዳይ አልነበረም። በህዝቡ ዘንድ የተለመደና ከጥንት ወላጆቻችን ተያይዞ የመጣ ስርዓት ነው ። የወልቃይት፣ መሳፍንት በውስጣቸው የስልጣን ሽኩቻ ቢኖራቸውም ወልቃይትን ለሌላ አስተዳዳሪ አሳልፈው ሲሰጡ ታሪክ አልመዘገበም ።

ይህ ህዝብ በነበሩት ነገሥታት ያስተዳደር ዘመን ከግምት ውስጥ ያልገባ በመሆኑ ፣በህክምና በትምህርት፣ባስተዳደደር በመገናኛ እጦት የተበደለና የተረሳ ህዝብ ነበር። አገራችን ኢትዮጵያን ሊወር መጥቶ በህዝቦቿ ብርቱ ተጋድሎ ተመትቶ የተባረረው ፋሽስት ጣልያን በዚያች ትንሽ ጊዜ ውስጥ የሰራው ከሑመራ ወደ አስመራ የሚወስድ የመኪና መንገድ ብቻ እንደነበረ ይታወቃል። ወልቃይት በተከዜ ወንዝ ከትግራይ ሽሬ አውራጃ ተከልሎ ከበጌምድርና ሰሜን ክፍለ ሃገር (ያሁኑ ጎንደር) ከወገራ አውራጃ በከባድ ጫካና ገደል ታጥሮ በአንገረብና ባህረ ሰላም በሚባሉ ወንዞች ተከቦና ተለይቶ ብቻውን የሚኖር ህዝብ ነበር። ይህ ህዝብ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ሳይገናኝ ባንድ ክብ አጥር ወስጥ ገብቶ በመኖር የራሱ ወልቀታይ የሚል ማንነት ፣ የራሱ የሆነ ቀያዊና ወንዛዊ ቋንቋ ያነጋገር ዘይቤ ልምድ ታሪክ አኗኗር ፈጥሮ እንደ ኢትዮጵያዊ ለመኖር የወደደ ህዝብ ነበር።

አማራ ነህ ስትለው አይደለሁም ወልቃይቴ ኢትዮጵያዊ ነኝ ይላል ። ትግርኛ እየተናገረ ትግራዋይ ነህ ስትለው አይደለሁም ወልቃይቴ ነኝ ይላል ። በትግርኛ (ትግራዋይ ዲኻ እንተልካዮ አኾንኩን ወልቀታይ እየ ) ይላል። ወልቃይት አማርኛ የኢትዮጵያ ቋንቋ ነው ብሎ ያምናል፣ትክክል ነው እኔም አምንበት አለሁ። ማንነቱም ኢትዮጵያዊ ነው። ስለዚህ ባማርኛ ሃዘኑም ደስታውም ቢገልጽ ቢፎክር ስሜቱ እንደ ኢትዮጵያዊ እንጂ አማራ ነኝ ብሎ አያምንም ። በነገራችን ላይ ከዘመነ ህወሓት በፊት አማርኛ እንደ ቋንቋ እንጂ እንዳ ሃገር የሚታወቅ አልነበረም። ወልቃይት ትግርኛና አማርኛ ሁለቱ ቋንቋዎች የኔ ናቸው ብሎ የወሰደ ህዝብ ነው። ከሁለቱ አንዱን ይዞ አንዱን መጣል አይፈልግም ፣ከክልል በፊትም እንደዛ ነበር ። ያሁኑ ችግር ከክልል ጋር ተያይዞ የመጣ ሳይሆን አይቀርም። ወልቃይት ሁለቱ ቋንቋዎች እኩል መቀበሉና መፈለጉ ከትግራዋዩ እና ካማራው የተለየ ያደርገዋል ። ይህ መደናገር የምንመለከተው ለበርካታ ጊዜ ተለይቶ ከመኖር የተነሳ የመጣ መስሎ ይሰማኛል ቢሆንም ወልቃይት ይህ እይታው ባህሉ ልምዱ እንዲከበርለት ይፈልጋል።

ወልቃይት ህክምና ለህዝቡ፣ ትምህርት ቤት ለልጆቹ የሌለው የተረሣ ህዝብ ነበር። ይሁን እንጂ በተፈጥሮ የታደለች ለምለም መሬቱና በፈጠረው አምላክ የሚተማመን ተሰዶ የማያውቅ ህዝብ ነበር። ክብዙ ጊዜ ስቃይ በኋላ ከሑመራ ጎንደር፣ ህዝብ በማስተባበር የመኪና መንገድ እንዲሰራ ተደረገ። ቆየት ብሎም ከሽሬ እንዳስላሴ ወደ ሑመራ የሚወስድ የመኪና መንገድ ደግሞ በልዑል ራሥ መንገሻ ሥዩም ጥረት ተሰርቶ መገናኘት ተጀመረ።በዚህም የተነሳ ወልቃይትና ሑመራ ባካባቢው ታወቀ፣ ህዝቡ ከበሬ እርሻ ወደ ዘመናዊ የትራክተር እርሻ ተሸጋገረ፣ ሃብታምና የኮራ ህዝብ መሆኑም ታወቀ። እንዲያውም በሰፊውና በተፈጥሮ ለምለም በሆነ መሬቱ ምክንያት ሰራተኛውና ባለሃፍቱ ወደ ወልቃይት ሲጎርፍ ትግርኛ እና አማርኛ ቋንቋ በሚናገሩት ወገኖች ላይ የበላይነት ስሜት ተሰማው ወደ ወልቃይት የሚመጣን ሁሉ በኢኮኖሚ እጦትና በችግር የተነሳ እንደሚመጣ አድርጎ ማሰብ ተለመደ። ይህ እይታ የመጣው አጎራባች አካባቢውን ካለማወቅ የተነሳ እንደሆነ ግልጽ ነው። ከወልቃይት ውጪ በርካታ አማራዎችና ትግራዮች በጣም የበለጸጉ ሃብታሞች እንዳሉ አላየም አላወቀም ነበር።

ይህ በዚህ እንዳለ ለዚህ ህዝብ ከአጼ ኃይለስላሴ መንግሥት ማክተምና የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ደርግ መተካት ተያይዞ የመጣ ከፍተኛ ችግር ተደቀነበት ።
የወልቃይት ህዝብ ወደ ጦርነት ገባ ፣ተከፋፈለ አንድነቱ ተዳከመ ። አንዱ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ሲደግፍ ሌላው በመቃወም ተሰለፈ ። ማለት ከኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህ አፓ) ፣ከኢትዮጵያ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኢዲህ ) እና ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) ጋር ሆኖ በመሰለፍ ወደ ጦርነት ገብቶ ሞተ ተሰደደ ተበታተነ ። ባገር ውስጥ የቆየ ድህነት ውስጥ ገባ ደርግም ንብረቱ ወረሰው ። ሰላምና ምቾት ህልም ሆኖ ቀረ፣ የማይ ሰደድ ተሰደደ ፣ሃፍታም የነበረ ደኸየ፣ ቤቱ ንብረቱና መሬቱ ተወረሰ። እንደወጣ የቀረ ቤቱ ይቁጠረው ማለቱ ይቀላል ። የወልቃይት ህዝብ ወደ ሚፈልገው ድርጅት እየ ገባ ቢዋጋም በዚህ አሰልቺ ጦርነት አሸናፊ ሁነው የወጡት ህወሓትና ከኢህ አፓ ተገንጥለው የወጡ ኢህዴን ኋላ ብአዴን የተባሉት ነበሩ።

ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥትን አሸንፈው እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ 1983 ዓ/ም አዲስ አበባ ገብተው መንግሥት እንደ መሰረቱ ይታወቃል። የህወሓት ድርጅት የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኢድህ) እና የኢትዮጵያ ህዝብ አብዩታዊ ፓርቲ (ኢህ ኣፓ) በማስወገድ ቀደም ብለው በ1972 ዓ/ም ነበር ወልቃይትን የተቆጣጠሩት ። ህወሓት ወደ ወልቃይት ሲገባ ህዝቡ ደርግን በማባረር ላይ ያሉት ተጋዮች ናቸው እስቲ እንያቸው በማለት በትዕግስት ነበር የተቀበላቸው። የህወሓት መሪዎች ግን መንግሥት ከሆኑ በኋላ የፈጸሙት እንዳለ ሆኖ ፣ የወልቃይት ህዝብና ወጣቶች ልጆቹ ከህወሓት ድርጅት ጎን በመሰለፍ ክብርት ህይወታቸውን አካላቸውና ንብረታቸው ጭምር በመስጠት ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት አኩልነትና ፍትህ ሰላም መስዋዕት ከፍለዋል።

ህወሓት በ 1983 ዓ/ም የኢትዮጵያን መዲና አዲስ አበባን ከያዘ በኋላ እሱን የሚመስሉ ድርጅቶች ፈጥሮ በኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግምባር (ኢህ አዴግ) ገዢ ፓርቲነት ኢትዮጵያን መምራት ጀመረ። አገሪ ቷን በቋንቋ መስፈርት ከልልሎ ወልቃይትን ትግርኛ ተናጋሪ ስለሆነ ከጎንደር ክፍለ ሃገር ነጥሎ የትግራይ አካል እንዲሆን በማድረግ ማስተዳደር ጀመረ ።

ይህ ነገር ለወልቃይት ያልታሰበ አዲስ ፍጻሜ ነበር ። እንግዲህ ወልቃይት ትግርኛ እየተናገረ በጎንደር ክፍለ ሃገር ደግሞ እንደ ኢትዮጵያዊ አማርኛ እየተጠቀመ ትግርኛ ተናጋሪ ጎንደሬ ሆኖ ይኖር ነበር። አሁን ደግሞ ትግርኛ ተናጋሪ በመሆኑ በትግራይ ክልል ውስጥ እንዲመደብ ተደርጓል ፣ እሱ ችግር የለውም ፍላጎቱና ኢትዮጵያዊነቱ ተጠብቆ የራሱን አስተዳደር እስከተፈቀደለት ድረስ። ይሁን እንጂ የወልቃይት ህዝብ ያለፉት ነገሥታት እንደፈለጉ ሲያገላብጡት የነበረ ለመሆኑ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም የታሪክ ማህደር በመጥቀስ ያቀረቡት ማስረጃ በቂ ምስክር ነው።ይህ ህዝብ የራሱ ባህል ልምድና አስተሳሰብ ፈጥሯል ፣ ትግርኛ እየተናገረ ትግራይዋይ አይደለሁም እስከማለት የደረሰ ህዝብ ነው ። ለብቻው ተለይቶ በውስጡ የፈጠራቸው ባህል፣ ልምድ፣ ወግና ታሪክ አሉት። የህወሓት መሪዎች ይህንን ልዩነት በትዕግስትና በመልካም አቀራረብ ከትግራይ ህዝብ ተጣጥሞ እንዲኖር ካላደረጉ ችግር መፈጠሩ የግድ ነበር ተፈጥሯልም። የዚህ ህዝብ ችግር ለመፍታት ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ የሰው ልጅ እኩልነት የሚያምን ድርጅት ወይም አመራር መሆን ይጠይቃል ። ይሁን እንጂ የህወሓት መሪዎች ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ድርጅታዊ ባህል የላቸውም ።

የወልቃይት ችግርም በዚሁ ላይ ነው የተደመረው። ይህ ህዝብ በጎንደር ክፍለ አገር ሲኖርም ያስተዳደር ችግር እንደነበረው አይካድም ይሁን እንጂ ከወልቃይት ተወላጆች ውጪ ግን ያስተዳደረው አልነበረም። በትግራይ ክልልም ይህ እንዲጠበቅለት ተስፋ ነበረው ። የህወሓት መሪዎች ህዝቡን ማዳመጥ አልቻሉም እስካሁን ብዙ ዋጋ ከፍለዋል ፣እሚቆመው መቼ ነው ?

በአጼ ዮሐንስ የንጉሠ ነገሥት መንግሥት የግዛት ዘመን እንኳ ወልቃይት ያስተዳደሩት ደጃዝማች ወርቅነህ ማሩ የወልቃይት ተወላጅ ብቻ እንደነበሩ ነው የሚታወቀው። ከሳቸው በፊት ይሁን በኋላ ወደ ወልቃይት ከማህል ትግራይ ለስራ ለንግድ ለተለያዩ ጉዳዮች እንጂ በታሪክ ወልቃይትን ለማስተዳደር የመጣ የለም ። የወልቃይት ህዝብ በዚህ ሁኔታ እያለ ወደ ትግራይ ክልል አስገብተው ማስተዳደር ሲጀምሩ፣ የህዝቡን ትርታ እያዳመጡ በመወያየት፣ እንደ ልማዱ በራሱ ሰዎች በሚፈልገው እንዲመራ አላደረጉም ። ከፍተኛ ስህተት የፈጸሙት እዚህ ላይ ነው። በተጻራሪ የህወሓት መሪዎች ተከታዮቻቸው በማሰማራት እንደምርኮኛ ንብረቱና ያቺ የሚመካባት መሬቱ በመውረር ስነ ስርዓት በጎደለው አስራር መሬት አልባና ድሃ ስደተኛ አድርገውቷል ።ይህንን ሲባል ማነኛውም የትግራይ ተወላጅ ይሁን ሌላ ኢትዮጵያዊ የወልቃይት መሬት መጠቀም የለበትም ማለት አይደለም መብቱ ነው ፣የወልቃይት መብት እኩል እስከ ተጠበቀ ድረስ ። የህወሓት መሪዎች በወልቃይት ሑመራ ከ350ሺ ሜትር ካሬ በላይ የርሻ መሬት ወስደው ይጠቀማሉ። የወልቃይት መሬት ምን ያህል እንደ ተወረረ ካሁን በፊት የጻፍኩት ተመልከቱ።

የህወሓት መሪዎች ከማህል ትግራይ የተነሳባቸውን የመሬት ማግኘት ፍለጋ ጥያቄ የሳቸው ደጋፊ የሆኑትን ካድሬዎች የወልቃይትን መሬት በመስጠት የህዝቡን ጥያቄ በማድበስበስና በሁለቱ ህዝብ ቅሬታ እንዲፈጠር አንድነቱ የላላ እንዲሆን ጥረዋል። ታድያ ወልቃይት ምን ያድርግ ? ህዝቡ እንደ ትግርኛ ተናጋሪ ትግራዋይ እንኳ አያዩንም ፣አድልዎው ልክየለውም እያለ በመጮህ ላይ ነው። ስለዚህ ህዝቡ መፍትሔ አጥቶ ከልክ በላይ ተገፍቶ ህወሓት አያስተዳድረንም እኛ ትግራይ አይደለንም እስከማለት ቢደርስ ፣ ጥፋቱ የማን ነው ?

ለዚህ ጉድለት ተጠያቂው የህወሓት መሪዎች እንደሆኑ ሊታወቅ ይገባል ። ወልቃይት በህወሓት ስር ሆኖ መስተዳደር ከጀመረ እንግዲህ ከ35—40 ዓመት መሆኑ ነው ፣ የህወሓት መሪዎች ወልቃይት በትግራይ ክልል ስር አድርገው ሲያስተዳድሩ ፣ የሰሩት ነገር ቢኖር ተከዜን ከሁለት በላይ ድልድይ በመስራት፣ የሽሬ፣ የጸለምትና የጸገደ ህዝብ ከወልቃይት ህዝብ ጋር ከረምትና በጋ እንዲገናኝ በማድረግ ፣ከሽሬ አድረመጽ ከአድረምጽ ጸገደ ከደጀና ዳንሻ ከአድጎሹ ኩሊታ እስክ አድረመጽ ከሑመራ አድረመጽ ተላልቅና ተናንሽ ድልድዮች በመስራት የተሟላ አስፋልት የመኪና መንገድ ሰርተዋል ። የመብራት ሃይልና ስልክ፣ ባንክ ትምህርትና ህክምና ይዘቱ እንኳ በቂ ባይሆን ዘርግተዋል ፣ በቋንቋ በኩልም የወልቃይቱ አክሰንት ከማጥፋታቸው በስተቀር በስነ ጽሑፍ ደረጃ እንዲያድግ አድርገዋል በዚህ ስራቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ይሁን እንጂ የህወሐት መርዎች በጸረ ዴሞክራሲና ጥላቻ ብቻ ስለሚሰሩ ይህንን ህዝብ ነፃ አድርገው በሰላም ማስተዳደር አልቻሉም ። ወልቃይት ትግርኛ እየተናገረ ማንነቱ ኢትዮጵያዊ እንዲሆንና አገራዊ ቋንቋው ደግሞ አማርኛ እንዲሆን ይፈልጋል። የህወሓት መሪዎች ደግሞ ትግራዋይነትና ትግርኛ ቅድሚያ እንዲሰጠው፣ ኢትዮጵያዊነትና አማርኛ በሁለተኛ ደርጃ እንዲታይ ይፈልጋል ። እንግዲህ ይህ ልዩነት ከሌሎቹ ያስተዳደር ችግሮች ተደማምሮ ለወልቃይት ህዝብ ከባድ ሸክም ሆኖበታል፣ ሸክሙ ለማውረድ ስልጣን የህዝቡ መሆን አለበት። 

የወልቃይት ህዝብ ከዘር ቆጠራና ከዘረኞች መራቅ አለበት ። ገንዘቡ ጉልበቱ እውቀቱ በማስተባበር አንድነቱ አጠናክሮ ለፍትህ ለዴሞክራሲ በሰላማዊ ትግል ከኢትዮጵያ ወገኖቹ ጋር መታገል አለበት፣ ቦታው ለሌላ መልቀቅ በፍጹም የለበትም፣ ችግር የለውም ማለቴ አይደለም፣ የለቀከው ቦታ ተመልሰህ ለማያዝ ቀላል አይሆንም በማለት ነው። በምንም ዓይነት መሰደድ የለበትም ችግሩ እንደምንም ተቋቁሞ ነጻ መሆን ይመረጣል። ሌላው የወልቃይት ችግር ያልተገነዘቡ የውሃን ሲሆኑ ሌሎች ደግም ሆን ብለው ሊገነዘቡ የማይፈልጉ አማራ ነን በሚሉ አንዳንድ ሰዎች እየተዘገበ ያለነው ። ኢትዮጵያዊነት ይቅደም አማርኛ የኢትዮጵያ ቋንቋ ነው በማለቱ ወልቃይት አማራ ነው እያሉ ችግር መፍጠራቸው ነው ። አማርኛ ያማራ ብቻ አይደለም ። አማርኛ የተናገረ ሁሉ አማራ ነው ያለስ ማን ነው ? ወልቃይት ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ቋንቋዋ አማርኛ ነው ብሎ ያምናል ። የነበረው አሁንም በተግባር ያለው እሱ ነው ፣ አዎ አማርኛ የስራ ቋንቋ ነው የሚሉ አሉ፣ የሚጠሉትም አልጠፉም ። በኔ እይታ ቋንቋ መጥላት በሽታ ነው ብየ አምናለሁ። ወልቃይት እንደዛ አይደለም የማንም ቋንቋ አይጠላም ። ይሁን እንጂ አማርኛ የኢትዮጵያ ቋንቋ ባይሆን ኖሮ ያገሪትዋ የስራ ቋንቋ አይሆንም ነበር ። አማርኛ እንደ ኮርኬ ቢፋቅ ውስጡ ኢትዮጵያ እንደሚል አልጠራጠርም ። በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ከሰማንያ በላይ ቋንቋዎች አሉ እነሱን ማሳደግና መጠቀም ተገቢ ነው ።

አማርኛን ማቆርቆዝ፣ ወደ ኋላ መጎተት፣ መጥላት ምን ማለት ነው ? ሌላው ደግሞ አማርኛን ወደ ክልል አውርደህ ፣ የኔ ብቻ ነው ማለትና አማርኛ የተናገረ ሁሉ ፣አማራ ለማድረግ መኳተን ነው። ለምሳሌ ያአዲስ አበባ ህዝብ አማርኛ ስለተናገረ አማራ ነህ ለማለት አይቻልም ። ካማራ በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሌላ ቋንቋ ፣ከቤተሰቡ የሚያወራበት የሚጽፍበት፣ እንዳለው መታወቅ አለበት። በተለይ የኢትዮጵያ ሊሂቃን የወልቃይትን ህዝብ ችግር ሰከን ብላቹህ ብታዩት ጥሩ ይመስለኛል ። የወልቃይት ችግር ከዛ በላይ ነው እሱም ነፃ የመሆን ጥያቄ ፣ የፈለከው ቋንቋ ተናገር ነፃ መሆንና ኢትዮጵያዊ ሆኖ መገኘት ። የወልቃይት ህዝብ በትግራይ ክልል ውስጥ ያጋጠመው ችግር የመልካም አስተዳደር እጦትና ኢትዮጵያዊነት እንጂ የቋንቋ ወይም አማራ የመሆን ጉዳይ አይደለም ። 

ስለዚህ በማጠቃለል ሌሎቹ ይሁኑ የህወሓት መሪዎች የወልቃይት ህዝብ ስነ ልቦና መገንዘብ አለባቸው ይህ ታሪክ ያለው ጉዳይ ነው፣ የህዝቡ ባህል ታሪክ ወጉና ልምዱ ማወቅ ግድ ይላል። የወልቃይት ህዝብ መተዳደር የሚፈልገው በራሱ ተወላጆች ወልቀቶት ብቻ እንደሆነ መገንዘቡ ተገቢ ነው ። የህዝቡ ጥያቄ ጀሮ ዳባ ልበስ ብሎ ማድበስበስ ችግሩ እንዲስፋፋ ያደርገዋል እንጂ መፍትሔ አይሆንም፣ ጥያቄው ይመለስ !!! የወልቃይት ህዝብ የራስ አስተዳደርና ፍትህ ሰላም ይፈልጋል ። በአድልዎና በፍርድ እጦት የተወሰደው መሬት እንደገና መታየት አለበት፣ የተወረረው መሬት ይመለስ። በደርግ የተወረሰው ንብረቱ እንደገና በህወሓት ካድሬ መወረስ የለበትም፣ ንብረቱ የህዝቡ ነው ይመለስ። በወልቃይት መሬት የተተከለው የስኳር ፋቭሪካም የወልቃይት ህዝብ ያሳተፈ መሆን አለበት። የተበተነው ህዝብ ችግሩ በውይይት ይፈታ ዘንድ ከያለበት አህጉር ጥሪ ይደረግለትና ወደ ትውልድ ቦታው ወልቃይት ይመለስ ። ካልሆነ ውጤቱ የከፋ እንዳይሆን ስጋት አለኝ ። የህወሓት ምክር ቤት ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ ሳይሆን ቢመክርበት ይሻላል። ይህንን የወልቃይት ችግር ህወሓት ሳይመሽበት ካልፈታው የትግራይ ጭቁን ህዝብም ወልቃይት ወገኑ ስለሆነ ይደግፈዋል። ሌላውም ለውጥ ደጋፊ ኢትዮጵያዊ በሙሉ።
መኮንን ዘለለው (ዮሴፍ)
ኢትዮጵያ ለዘልዓለም ትኑር፣ ዘረኝነት ይውደም
Mokonnenz@gmail.com
ግንቦት 15, 2012


Share

Published

Updated


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service
የወልቃይት ጉዳይ (ለውይይት መነሻ) | SBS Amharic