አቶ ሙስጠፋ የግብርና ምጣኔ ሐብት ባለሙያ ሲሆኑ፤ ዘለግ ላሉ ጊዜያት የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኛ ሆነው በአፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ ተዘዋውረው ዓለም አቀፍ ግልጋሎቶችን አበርክተዋል። በሂደቱም ልምድ ቀስመዋል፤ ክህሎታቸውን አዳብረዋል።
በሶማሌ ክልል ሰላምን ማስፈን፣ የሰብዓዊ መብቶችን ጥሰትን መግታት፣ ለሕዝብ ታማኝ አገልጋይ መሆን ከዘርፈ ብዙ ተልዕኮቻቸው መካከል ጥቂቶቹ መሆናቸውን ያመላክታሉ።

Mustafa Mohammed Omar Source: Courtesy of PD
ባለፉት በርካታ ዓመታት በሶማሌ ክልል ተከስተው ስለነበሩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ነቅሰው ሲናገሩም፤ ግድያ፣ ሰቆቃ፣ መንደሮችን ማቃጠል፣ በርካታ ሰዎችን ለስደት መዳረግ፣ ለወራት መጸዳጃ ቤት ውስጥ ሰዎችን ማሰር፣ በጅብና በነብር እስረኞችን ማሸበርን በዋነኘነት ያነሳሉ። ይህ ግፍ የተፈጸመበት የጂግጂጋ እሥር ቤት ወደ ሙዚየም ይቀየራል በማለትም ይገልጣሉ።
ሐምሌ 28 በጂግጂጋ የተካሄደው የአመጽ ጥቃት የተወጠነው በክልሉ ብቻ የተወሰነ ብጥብጥን ለማስነሳት ሳይሆን፤ በደገኛና ቆለኛው፣ በሙስሊሙና ክርስቲያኑ መካከል ግጭቶችን ፈጥሮ አገሪቷን ብጥብጥ ውስጥ ለማስገባት እንደነበረ ይጠቁማሉ።
ይህን ያስፈጸመውም መዋቅርና በጀት የነበረው “ሔጎ” የሚባል በህቡዕ ይንቀሳቀስ የነበረ የወጣቶች ድርጅት እንደነበር ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ግና አብዛኛዎቹ መዋቅሮቹ እንደፈራርሱና ቀሪዎቹንም በማፈራረስ ላይ እንዳሉ ያስታውቃሉ።
የማንነት ፖለቲካና የዜግነት ፖለቲካን አስመልክቶ ያላቸው አተያይ አደጋዎችን ጠቋሚና መፍትሔን አመላካች ነው።
“ማንነት ላይ ያተኮረ ፖለቲካ ዞሮ-ዞሮ ወደ ግጭት ነው የሚያመራው። ከማንነት ፖለቲካ ወደ ፖለቲካዊ እሳቤ ቶሎ ብንሸጋገር፤ በዜግነት ላይ ያተኮረ የመብት ጥያቄዎች የሚመለሱባት አገር ብንመሰርት ደስ ይለኛል” ባይ ናቸው።
ይህንኑ አንድነት ከክልላቸው ለመጀመር የሶማሌን ባሕልና ታሪክ የሚዘክሩ ነገሮችን መሥራት እንዳለባቸው፤ የሶማሌን አንድነት ማጉላቱ የጎሳ ትንቅንቅን ለመክላትና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖች ጋር የባሕል፣ የታሪክና ልምድ ልውውጦችን በማድረግ መቃቃሮችን በመቻቻል ባሕል ለመተካት ያስባሉ።
በተለይም “ለበርካታ ዓመታት በአማራው ላይ ስር የሰደደ አሉታዊ ስብከቶች ስለነበሩ፤ የመጀመሪያ ልዑካን ቡድናችንን በቅርቡ ወደ አማራ ክልል እንዲሄድ እናደርጋለን” በማለት የአንድነትና ብሔራዊ ማንነት ግንባታ ውጥናቸውን አጋርተውናል።
በዘር ላይ ያተኮረ ፖለቲካ ዘላቂነት የሌለው ስለመሆኑ ፅኑዕ እምነት እንዳላቸው ገልጠውም፤ ጥሩ-ጥሩ ምሁራን ተሰባስበው በመወያየት አዲስ ዕሳቤ፤ አዲስ ራዕይ መፍጠር አለባቸው ሲሉ ያሳስባሉ።

Mustafa Mohammed Omar Source: SBS Amharic
በእሳቸው በኩል ለኢትዮጵያ ያላቸውን ራዕይ ሲገልጡ፤ “የእኔ ራዕይ ሁሉን አካታች፤ ሁሉም ተጠቃሚ በሚሆንባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ፤ ሁሉም ዜጋ በፈለገው ቦታ የሚሰራባትና የሚኖርባት፣ ሰላም የሰፈነባት፣ ሲልም ለምሥራቅ አፍሪካ ማዕከል የምትሆንበት ነው። በሶማሌ አካባቢ የምናደርጋቸውም እንቅስቃሴዎች ለዚያ ትልቅ ራዕይ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ነው” ይላሉ።
ሩቅ አሳቢ፤ ቅርብ አዳሪ እንደማይሆኑ ተስፋችን ነው።

Kassahun Seboqa Negewo (L), and Mustafa Mohammed Omar (R) Source: SBS Amharic