የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፤ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግሥት በውትድርናው ዓለም የመቶ አለቃነት ማዕረግ ደርሰዋል። የዘውድ ሥርዓቱ ፓርላማ አባል ሆነው ሳለ የኢትዮጵያ ፓርላማ የዓለም ፓርላማ አባል እንዲሆን፤ የጅራፍ ግርፋት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከላ የጎላ ሚና አበርክተዋል።
አስተዋፅዖዎቻቸውም የሕይወት አሻራዎቻቸው ነፀብራቅ ሆነዋል።
በዘመነ ኢሕአዴግም በቾን ወክለው በግል ተወዳዳሪነት የፓርላማ አባል ሆነዋል። ሲልም፤ ለ12 ዓመታት የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ለመሆን በቅተዋል።
በዘመነ ፕሬዚደንትነታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የሞት ቅጣት እንዲቀር ትታረዋል። ለፍርድ ቤት ይሙት በቃ ብያኔ ይሁንታን ላለመቸር ‘የሰው ልጅ ሕይወት በሰው እጅ እንዲነጠቅ ፕሬዚደንታዊ ፊርማዬን አላሰፍርም’ ብለው ጸንተዋል።
በሕይወት ሳሉ ብርቱ ምኞታቸው ኢትዮጵያና ኤርትራን ማስታረቅ ነበር። የእሳቸው ጉልህ ሚና አሻራ ባይኖርበትም ሁለቱ አገራት የሰላም ውል ሲዋዋሉ ለመመልከትና ከፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋርም ለመገናኘት በቅተዋል።
ባለፈው ወርሃ ኦክቶበር ወደ ኢትዮጵያ ለሥራ ተጉዘን በነበረት ወቅት ትህትና በተመላው ግብዣቸው ሳቢያ ከመኖሪያ ቤታቸው ተገኝተን በግል አውግተናል። ወጎቹ ግላዊ በመሆናቸው ለአየር የሚበቁ አይደሉም።
ለዛሬው ግና ጃኑዋሪ 2 – 2014 ክቀድሞው ፕሬዚደንት ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ መዘከሪያ ይሆን ዘንድ ይዘን ቀርበናል።

የሰላም ስምምነት - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ (ግራ) እና ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ (ቀኝ) Source: Courtesy of PD

የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕረዚደንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ (ግራ) እና ጋዜጠኛ ካሳሁን ሰቦቃ (ኦክቶበር 12 - 2018 በቀድሞው ፕሬዚደንት መኖሪያ ቤት) Source: SBS Amharic