በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ “ትህትናና ቅንነት” የመልካም ስብዕና መገለጫ ናቸው። በፖለቲካው ዘርፍ ግና ዝንቅ ዕንድምታዎች አሏቸው። ሽኩቻ፣ መጠላለፍና አንጃ ገንነው ባሉበት የፖለቲካ መስክ “ትሁትና ቅን” ሆኖ መዝለቅ አዋኪ ነው። ይሁን እንጂ ስለ አቶ ደመቀ መኮንን ሲነሳ፤ “ትሁት” ፣ “ቅን” የሚሉ የባህሪይ ማጣቃሻዎች ይደመጣሉ።
አቶ ደመቀ ወደ ፖለቲካው መድረክ ብቅ ያሉት ገና በ20ዎቹ ለጋ የወጣትነት ዕድሜ ዘመናቸው በመሆኑ፤ አሁን ሰልፋቸው ከጎምቱ ፖለቲከኞች ተርታ ነው። ከዕድሜያቸው ግማሽ በላይ ለ26 ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ የፖለቲካ አመራር ዕርከኖች ላይ ቆይተዋል።
ከመምህርነት በቀጥታ የዘለቁት ወደ አማራ ክልል ከፍተኛ አመራር ነው። አነሳሳቸው ከክልል መንግሥቱ ቁጥር ሶስት የሥልጣን እርካብ ሲሆን፤ ምክትል ፕሬዚደንት፣ የብአዴን/አዴፓ ሊቀመንበር፣ የፌዴራል ሚኒስትርና ሲልም አሁን ካሉበት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር መንበር ላይ ለመሰየም በቅተዋል።
በዘመናዊ ፖለቲካ ራስን ለሕዝብ አዳምቆ መሸጥ ግድ በሚልበት ዘመን፤ ስለራሳቸው ለመናገር ቁጥብ ናቸው። በቅንጭቡም ቢሆን በእርሳቸው አንደበት ስለ ደመቀ መኮንን ማንነት እንዲነግሩን በማንሳታችን ግና ‘ከቤተሰብ ሕይወታቸው ጀምሮ ዕርቀ ሰላምን ማውረድ መውደዳቸውን፣ ሁሉንም ሰው እኩል የማየት፣ የማድመጥ፣ ነገሮችን አጣጥሞ ወደ መፍትሔ የመውሰድ ተሰጥዖዎቻቸው “አባ መላ” እንዳሰኟቸው’ ከአንደበታቸው ለማድመጥ በቅተናል።

Deputy Prime Minister Demeke Mekonnen Source: Courtesy of PD
የአጼ ምኒልክን ቀኝ እጅ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ “ሀብቴ አባ መላ”ን ያስታውሷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ፤ አስተዳደጋቸው ከኦሮሞ፣ አገው፣ ሺናሻና የጉምዝ ተወላጆች ጋር በመሆኑ ለብዝሃነት ባይተዋር እንዳልሆኑ፤ ያም የኢትዮጵያን ዝንቅ ብሔረሰባዊ ገጽታና ምልከታዎች እንዲረዱ፤ በቀላሉ ከሰዎች ጋር ተግባብተውና ተከባብረው ለመኖር አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንዳበረከተላቸው ይገልጣሉ።
በሶስቱ የለውጡ ጉዞ ዓመታት ውስጥ፤ አይነኬ የሚባሉ አስተሳሰቦችንና ተቋማትን መታገል፤ እንደ ብአዴን ሊቀመንበርነታቸውና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው የብአዴንን ፍላጎት ከፌዴራል ጋር አጣጥሞ መሄድ ፈታኝ እንደነበሩ፤ አቶ ለማና ዶ/ር ዐቢይ ሲመጡም በመመጋገብ አሁን ለተደረሰበት ደረጃ መብቃት መቻሉን በምልሰት ነቅሰው ያወጋሉ።
ስለ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሲያነሱም፤ “ትሁት፣ ብርቱ ሠራተኛ፣ ይበልጡኑ ወደ ቀለም ትምህርት የሚያተኩሩ...” ብለው በማንሳት፤ “ሥልጣን ይበቀኛል። እኔ የመፍትሔው አካል ልሁንና አገርን ልታደግ ማለት፤ በደም ሥልጣን ሲዘዋወር በነበረባት አገር ውስጥ ትልቅ ውርሰ አሻራ ሆኖ ሊወሰድ የሚችል ነው” ሲሉ ታሪክ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በማለፊያ ሚዛኑ እንዲመዝናቸው ይሻሉ።
ስለራሳቸው ውርሰ አሻራ ግና የኢትዮጵያ ሕዝብ ተገቢ የሚለውን የታሪክ ሥፍራ ቢቸራቸው ይወዳሉ።

DPM Demeke Mekonnen (L), and PM Abiy Ahmed (R) Source: Courtesy of PD

Former PM Hailemariam Desalegn (L), and DPM Demeke Mekonnen (R) Source: Courtesy of PD
አቶ ደመቀ በሁነኛ ማሳሰቢያቸው፤ “ባለፉት 27 ዓመታት ያጎደልናቸው፤ ያጠፋናቸው ነገሮች አሉ። ይቅርታ መጠየቅ አለበት። ይቅርታ የምንጠይቅባቸው ጉዳዮች አሉ” ይላሉ።
የአገር ቁስል እንዲሽር፤ ጠባሳው እንዲደበዝዝ። 

DPM Demeke Mekonnen (L), and Kassahun Seboqa (R) Source: SBS Amharic





