ቫይረስ - የወባ መድኃኒት
የዓለም ጤና ድርጅት የፀረ-ወባ መድኃኒትን ለኮቪድ - 19 መድኃኒትነት ወይም መከላከያነት ጥቅም ላይ እንዳይውል አስጠነቀቀ።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕና የብራዚሉ አቻቸው ጃይር ቦልሶናሮ የፀረ-ወባ መድኃኒቱን በመጠቀሙ ላይ አዎንታዊ ድጋፍ እየሰጡ ነው።
አቶ ትራምፕ በየቀኑ ሃይድሮክሲክሎሮኪን እየወሰዱ መሆኑን ሲገልጡ፤ ፕሬዚደንት ቦልሶናሮ በበኩላቸው ብራዚላውያን የኮቪድ - 19 ስሜት እንደተሰማቸው ወዲያውኑ ክሎሮኪን እንዲወስዱ ያበረታታሉ።
በመላው ዓለም የመድኃኒቱን ፍቱንነት ለመፈተን ክሊኒካዊ ሙከራዎችን እየተደረጉ ያለ ሲሆን፤ የዓለም ጤና ድርጅቱ ዶ/ር ማይክል ራያን በርካታ አገራት መድኃኒቱ ብርቱ ጎጂነት ስላለው አጠቃቀሙ ላይ ገደብ ማድረጋቸውን ሲገልጡ፤
"አያሌ አገራት የመድኃኒቱን አጠቃቀም ለክሊኒካዊ ሙከራዎች፣ ወይም በክሊኒካዊ ሙከራዎች ወቅት ወይም ሆስፒታል ውስጥ በክሊኒክ ባለሙያዎች ቁጥጥር አማካይነት ካልሆነ በስተቀር። ያ የሚሆነውም በተለይም ኮቪድ - 19ኝን በተመለከተ ነው። ስለምን - የተለያዩ ጎጂ ጎኖች ስለተከሰቱና ሊከሰቱም ስለሚችሉ። ይህንንም ስለ መድኃኒቱ አጠቃቀም ክብደት መስጠትና መረጃዎችን መገምገም የእያንዳንዱ አገር ውሳኔ ይሆናል" ብለዋል።
ሳይክሎን አምፋን
ሳይክሎን አምፋን ባስከተለው ብርቱ ንፋስና ዝናብ ሳቢያ በምሥራቃዊ ሕንድና ባንግላዴሽ የ15 ያህል ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል።
ሳይክሎን አምፋን ሕንፃዎችን ደርምሶ ለአፈር ዳርጓል፣ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን ገርድሶ ጥሏል፣ እንዲሁም ዛፎችን ከሥራቸው ነቅሏል።
ልዕለ - ሳይክሎኑ ከመዳረሱም በፊት ሶስት ሚሊየን ሰዎችን ከአካባቢው ማራቅ ግድ ይላል።
የሕንድ ብሔራዊ የጉዳት ግብረ ምላሽ ኃይል ዋና ዳይሬክተር ፕራድሃን - ብዙዎቹ አደጋው የደረሰባቸው አካባቢዎች የዝቅተኛ ኑሮ ነዋሪ ቀዬዎች መሆናቸውን ገልጠዋል።
ቫይረስ ወሰኖች
ከኮቪድ - 19 የጤና ጉዳይ ጋር በተያያዘ የወሰኖች መዘጋትና መከፈት በስቴትና የጋራ ብልፅግናው ባለ ሥልጣናት መካከል ውጥረት ያለው አለመግባባትን አስነስቷል።
ኩዊንስላንድ የወሰኗ መዘጋት ከሴፕቴምበር አልፎ እንደሚቆይ አስታውቃለች።
ይሁንና የጋራ ብልፅግናው ምክትል የሕክምና ኃላፊ - ዶ/ር ፖል ኬሊ በርካታ ስቴትና ግዛቶች ላለፉት ጥቂት ቀናትና ሳምንታት አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች እንዳልተመዘገበባቸውና ሲድኒና ሜልበርንም ቢሆኑ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ወሸባ ገብተው ያሉ በመሆኑ ከሕክምና ምልከት አኳያ የወሰኖቹ መዘጋት አስፈላጊነት እንደማይታቸው ገልጠዋል። ያም ሆኖ ውሳኔ የማሳለፉ ጉዳይ የስቴትና ግዛቶች መሆኑን ተናግረዋል።
ቫይረስ - በመላው ዓለም
የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ - 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ በሉላዊ ደረጃ በዕለታዊ ክስተት ከተመዘገቡት ከፍተኛ የቫይረስ መስፋፋት ቁጥር መመዝገቡን አስታወቀ።
በድርጅቱ ሪፖርት መሠረትም 106 000 ሰዎች በመላው ዓለም በቫይረሱ መያዛቸውን ጠቁሞ፤ የቫይረሱ ወደ ደሃ አገራት መስፋፋትም በእጅጉ ያሳሰበው መሆኑን ገልጧል።
እስካሁን ከ 323,000 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲሞቱ፤ ከ 4.9 ሚሊየን በላይ ተይዘዋል።

