ቫይረስ - ተማሪዎች
የብሔራዊ ኮቪድ - 19 አስተባባሪ ኮሚሽን ዋና ኃላፊ የአውስትራሊያን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መስክ ለማገዝ የውጭ አገር ተማሪዎችን ወደ አውስትራሊያ የሚያጓጉዙ ልዩ በረራዎች እንዲመቻቹ ምክረ ሃሳብ አቅረበዋል።
የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ኔቭ ፓወር መንግሥት ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ለመሳብና የቪዛ ሂደቶችንም ለማፋጠን የሚያስችለው መልካም አጋጣሚ እንዳለ ጠቁመዋል።
አቶ ፓወር ባቀረቡት ምክረ ሃሳብ ላይ ተማሪዎቹ ወደ አውስትራሊያ ለመምጣት ከመነሳታቸው በፊት የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማካሔድና አውስትራሊያም እንደደረሱ ወሸባ እንዲገቡ ይደረጋል።
ዕቅዱ የአውስትራሊያን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በማገዙ በኩል ሁነኛ ሚና ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሏል።
ቫይረስ - የእናቶች ቀን
የኒው ሳውዝ ዌይልስ ፕሪሚየር በዚህ ሳምንት መጨረሻ የሚከበረውን የእናቶች ቀን አስመልክቶ የሚላላ ተጨማሪ የኮሮናቫይረስ ገደቦች ይኖራሉ ብለው ቤተሰቦች እንዳያስቡ አሳሰቡ።
ፕሪሚየር ግላዲስ በርጂክሊያን በዚህ ወር ኒው ሳውዝ ዌይልስ ውስጥ የአኗኗር ዘይቤ ወደ አዘቦታዊነቱ እንደሚመለስ ተስፋ ፈንጥቀዋል።
የጤና ባለ ሥልጣናት የኮቪድ - 19 መስፋፋት እያሽቆለቆለ በሔደ ቁጥር ገደቦች እየረገቡ እንደሚሔዱ ይገልጣሉ።
እስካሁን አውስትራሊያ ውስጥ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 6875 ደርሷል።
97 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
5,984 አገግመዋል።
688,000 ምርመራዎች ተካሂደዋል።
የብሔራዊ ካቢኔው ነገ ዓርብ በሚያካሂደው ስብሰባው የትኞቹ የኮሮናቫይረስ ገደቦች ሊነሱና ሊለወጡ እንደሚገባ መክሮ ይወስናል።
የአውሮፓ ሕብረት - ምጣኔ ሃብት
የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በ1930ዎቹ ታላቁ የምጣኔ ሃብት ድቀቀት ካደረሰው የከፋ ጉዳት ማድረሱን አስታውቁ።
በመላው የአውሮፓ ሕብረት ቀጣና 7.5 ፐርሰንት ያህል የምጣኔ ሃብት ዕድገት ቁልቁል መንሸራተት እንደሚያሳይ ተገምቷል።
ከሕብረቱ አባል አገራት ውስጥ ግሪክ፣ ጣሊያንና ፖርቱጋል በእጅጉ ተጎጂ አገራት እንደሚሆኑም የአውሮፓ ሕብረት የምጣኔ ሃብትና ፋይናንስ ጉዳዮች ኮሚሽነር ፓውሎ ጄንቲሎኒ ጠቁመዋል።

