የቫይረስ ገደቦች
በመላው አውስትራሊያ የኮሮናቫረስ መስፋፋትን ተከትሎ ተጥለው የነበሩ ገደቦች ረገብ እንዲሉ በመደረጋቸው አውስትራሊያውያን በአዲስ መልኩ ያገኙቸውን ነፃነቶች አዛብተው ዳግም የኮሮናቫይረስ ማዕበል እንዳይቀሰቀስ ልብ ማስባያ ማስጠንቀቂያዎች እየተሰጡ ነው።
ስቴትና ግዛቶች በቤት ውስጥና ዉጪ መታደሞችንና የንግድ እንቅስቃሴዎችን የማካሄድ ጅምሮች ግብር ላይ እንዲውሉ፤ ከባለ ሶስት ደረጃ ገደብ ማንሻዎች ውስጥ የመጀመሪያውን ደረጃ አላልተዋል።
አውስትራሊያውያንም ከበርካታ ሳምንታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጠጥ ቤቶች፣ ካፌዎችና ምግብ ቤቶች ተቀምጠው መመገብና መጠጣት ችለዋል።
ከኩዊንስላንድ ነዋሪዎች ውስጥ ገደቦቹ በመላላታቸው ሳቢያ ከቤት ውጭ ያለ ሕይወትን በማጣጣም የወሊድ ስጦታ ለመስጠት ከበቁት ውስጥ አንዷ ያደረባትን የደስታ ስሜት ስትገልጥ፤
"100 ፐርሰንት በሐሴት ተመልቻለሁ። ውጪ ለመውጣት በእጅጉ ናፍቀን ነበር። በጣም ጥሩ ነው። አካላዊ ርቀታችንንም መጠበቅ እንዳለብን አልዘነጋንም። ይኸው ከቤት ውጪ ሆነን እየተደሰትን ነው። ሁሉም ገደቦች መቶ - በመቶ ተነስተው ወደ አካል እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ ሥፍራዎች መሔድ፣ ከ 10 ሰዎች በላይ ሆነን ጥሩ ምግቦችን ካፌዎች ውስጥ ተቀምጠን መመገብን እስከምንጀምር ድረስ በእጅጉ እየጓጓን ነው" ብላለች።
በሌላ በኩል የኒው ሳውዝ ዌይልስ ጤና ሚኒስትር ብራድ ሃዛርድ አካላዊ ርቀትን ከመጠበቅ ሰዎች ቸል እንዳይሉ ሲያሳስቡ፤
"ሰዎች ከቤታቸው ወጣ ብለው በነፃነቶቻቸው ሲደሰቱ እየተመለከትን ነው። ይሁንና አለመታደል ሆኖ የተወሰኑቱ ለኮቪድ የተጋለጡ ናቸው። እኒህ ነፃነቶችና መስዋዕትነቶች ዋጋ የሚያገኙት የቫይረሱን ተዛማችነት እንዲያሽቆለቁል ማድረግ ሲቻል ነው። ተዛማችነቱ ሊገታ ወይም ቢያንስ በእጅጉ እንዲያሽቆለቁል ማድረግ የሚቻለው የማኅበራዊ ርቀት መርሆችን መከወን ሲቻል ነው። እራሳችሁን ልክ በኮቪድ - 19 እንደተያዘ ሰው በመመልከት ጥንቃቄ አድርጉ" በማለት ተናግረዋል።
ቫይረስ ሞርጌጅ
የአውስትራሊያ ባንኮች ማኅበር በኮቪድ - 19 የተነሳ በጠቅላላው $153.3 ቢሊየን ወይም 429 000 የሞርጌጅ ክፍያዎች መስተጓጎላቸውን አመልክቷል።
ይህም ማለት ከ14 - አንድ የሞርጌጅ ክፍያዎች የቤት ወጪያቸውን ለመሸፈን እንዲችሉ ተራዝመዋል።
ይህንኑም ተከትሎ የአውስትራሊያ ባንኮች ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ - አና ብላይ የሚቀጥሉት 12-18 ወራት ለባንኮቹና ደምበኞቻቸው ፈታኝ ጊዜ መሆኑን ገልጠዋል።
ቫይረስ ሥራ
በኮቪድ - 19 ሳቢያ የሥራ አጥነት ቁጥር በናረበት ወቅት የነርስና ከባድ መኪና ሾፌሮችን አግኝቶ ለመቅጠር አስቸግሯል።
የብሔራዊ ክህሎቶች ኮሚሽን ከኤፕሪል 24 እስከ ሜይ 8 አምስት ኢንዱስትሪዎችን አነጋግሮ ለ988 ክፍት የሥራ ቦታዎች ሠራተኞችን አግኝተው መቅጠር እንዳልቻሉ አስተዋቋል።
ክፍት የሥራው ቦታዎቹን ለመሙላት ተፈላጊዎቹ - ነርሶች፣ የችርቻሮ ሽያጭ ረዳቶች፣ የአረጋውያንና ግብረ አካል ጉዳተኞች ተከባካቢዎች፣ የብረት አቅላጭና አቃኚዎች ናቸው።
ቫይረስ አፕ
የፌዴራል መንግሥቱን በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ጋር ንኪኪ ያላቸውን ሰዎች ዳታ ተጠቅሞ አንድም በቫይረሱ የተያዘ ግለሰብ ቪክቶሪያ ውስጥ አለመመዝገቡን የቪክቶሪያ ዋና የጤና ኃላፊ ፕሮፌሰር ብሬት ሳተን ገልጠዋል።
እስካሁን ድረስ 5.5 ሚሊየን አውስትራሊያውያን ኮቪድሴፍ አፕን ሞባይሎቻቸው ላይ ጭነዋል።
ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ቪክቶሪያ ውስጥ 11 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ በሳቢያውም በጥቅሉ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁትር 1,554 ደርሷል።
አዲስ በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች ውስጥ ሁለቱ ከሲዳር ሥጋዎች ፋብሪካ ጋር የተያያዙ ሲሆኑ፤ ከዕርድ ሥጋ አቅራቢ ፋብሪካው ጋር በተነካካ በቫይረሱ የተጠቁት ሰዎች ቁጥር 98 ደርሷል።

