ቫይረስ - ኣፕ
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን አውስትራሊያውያን ኮሮናቫይረስን ከልተው ወደ አዘቦታዊ ኑሮአቸው ፈጥነው ለመመለስ፤ በተወሰነ መልኩ ግላዊ ነፃነታቸውን አሳልፈው ሊሰጡ እንደሚገባ አሳሰቡ።
የአውስትራሊያ መንግሥት የሰዎችን እንቅስቃሴዎች የሚከታተል የሞባይል አፕ ግብር ላይ ለማዋል ከሲንጋፖር ባለ ስልጣናት ጋር እየሠራ ነው።
የአፑ መጠሪያ "TraceTogether" ሲሆን፤ የተጠቃሚውን የሞባይል ስልክ ብሉቱዝ ኃይል በመጠቀም በኮሮናቫይረስ መያዙ ከታወቀ ሰው ጋር በቅርበት 15 ደቂቃና ከዚያም በላይ ማሳለፉን ይመዘግባል።
መረጃውም ቫይረሱን ለመከላከል ለሚጥሩ የጤና ባለ ስልጣናት ብቻ እንዲደርስ ያደርጋል።
አርባ ፐርሰንት ያህል አውስትራሊያን የአፑ ተጠቃሚ ለመሆን ከፈቀዱ ጥረቱ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችልም ተነገሯል።
አቶ ሞሪሰን የአፑን ፋይዳዎች ሲያመላክቱ፤
[["አፑን ለመጠቀም ግዴታ አይኖርም። አውስትራሊያ ውስጥ እንዲያ አይደረግም። ሰዎችን ቀልጥፈን ከለየንና ኮሮናቫይርሰን ፈጥነን ከደረስንበት የአያሌ ሰዎችን ሕይወቶች እንታደጋለን። ያም ማለት ምጣኔ ሃብታችንን ሰፋ አድርገን እንከፍታለን… ይህ በመጠኑም ቢሆን የጦርነት ቦንዶችን በጦርነት ወቅት የመግዛት ያህል ነው። በአዘቦቱ ቀናት የማንፈጽማቸውን እንዲህ ባሉ ጊዜያት የምንከውናቸው ድርጊቶች ይኖራሉ። እናም ያ ሰዎችን የሚታደግ ከሆነ ማድረግ ይገባል። ይህ ምናልባትም ዋጋ ለመክፈል ግድ ከሚሉን ውስጥ አንዱ ይሆናል" ብለዋል።
ቫይረስ - የተጠቂዎች ቁጥር
አውስትራሊያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ተጠቅተው ሕይወታቸ ያለፈ ሰዎች ቁጥር 63 ደርሷል።
ከ 6,400 በላይ አውስትራሊያውያን በቫይረሱ ተይዘዋል።
56 ፐርሰንት ያህሉ አገግመዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ ሁለት ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።
ከ 126 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።
ጣሊያን ከ 21 ሺህ በላይ ሰዎቿን ስታጣ፤ ስፔይን፣ ፈረንሳይና እንግሊዝ ከአሥር ሺህ በላይ የሰዎቻቸውን ሕይወት በቫይረሱ ተነጥቀዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ 478 ሺህ ሰዎች በላይ በቫይረሱ ተይዘው ለመዳን ችለዋል።
ቫይረስ - ትምህርት ቤቶች
የቪክቶሪያ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ወላጆች ልጆቻቸው በርቀት ትምህርት እንዲከታተሉ ላደረጉት ተሣትፎ ምሥጋና አቅርበዋል።
ትምህርት ቤቶች ለሁለተኛው የትምህርት ክፍለ ጊዜ የተከፈቱ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ትምህርታቸውን የሚከታተሉት ከቤታቸው ሆነው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን በማኅበራዊ ሚዲያ ኮቪድ - 19 በልጆች ዘንድ የመዛመቱ ሁኔታ በጣሙን አነስተኛ ነው የሚል የጤና ምክረ ሃሳባቸውን ደግመው ያስተላለፉ ቢሆንም፤ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ በበኩላቸው ሁሉም ተማሪዎች በአካል የመማሪያ ክፍሎች ውስጥ ተገኝተው እንዲማሩ ትምህርት ቤቶችን መክፈቱ የተሳሳተ እርምጃ ነው የሚሆነው ብለዋል።

