Watch FIFA World Cup 2026™

LIVE, FREE and EXCLUSIVE starting June 12 2026

ኅብረት ለምርጫ፡ በ130 የምርጫ ጣቢያዎች ያልተመዘገቡና ካርድ ያልያዙ ሰዎች ድምፅ ሰጥተዋል

የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ (CECOE) በ7ኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ያካሄደውን የመጀመሪያ ደረጃ የትዝብት ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ፣ በበርካታ የምርጫ ጣቢያዎች የሕግና የአሠራር ግድፈቶች መመዝገባቸውን አስታውቋል።

CECOE.png
Credit: CECOE

የኅብረቱን ሪፖርት ጠቅሶ የኢትዮጵያ ኢንሳይደር የምርጫ ልዩ የዘገባ ድረገጽ እንዳመለከተው፣ በ130 የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች መዝገብ ላይ ስማቸው ያልተገኘ እና የመራጭነት ካርድ ያልያዙ ከ1 እስከ 10 የሚደርሱ ሰዎች ድምፅ እንዲሰጡ ተፈቅዶላቸዋል።

በተጨማሪም በ8 ሌሎች ጣቢያዎች ከ10 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ስማቸው በመዝገብ ላይ ሳይኖር እና የመራጭነት ካርድ ሳይዙ ድምፅ እንዲሰጡ መፈቀዱ ተረጋግጧል።

 በሌላ በኩል ከታዘቧቸው 2,506 የምርጫ ጣቢያዎች መካከል በ46 ጣቢያዎች የመራጮች መዝገብ ላይ ስማቸው የሰፈረ ሕጋዊ መራጮች ድምፅ እንዳይሰጡ መከልከላቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል።

በሁለት ተጨማሪ ጣቢያዎችም ከ10 በላይ የሚሆኑ ሕጋዊ መራጮች ድምፅ እንዳይሰጡ መደረጋቸው ተጠቁሟል።

የድምፅ አሰጣጥ ምስጢራዊነትን በተመለከተም በ161 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የመራጮች ምስጢራዊነት መጣሱን ኅብረቱ ገልጿል።

ጥሰቶቹ መራጮችን ተከትሎ ወደ ምስጢራዊ ድምፅ መስጫ ክፍል መግባት ወይም መራጩ የመረጠውን የምርጫ ወረቀት ለማየት መጠየቅን ጨምሮ የተለያዩ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን እንደሚያካትቱ ተገልጿል ብሏል ኢትዮጵያ ኢንሳይደር በዘገባው።

በተጨማሪም በ19 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የምርጫ አስፈጻሚዎች ለመራጮች መመሪያ በሚሰጡበት ወቅት ለተወሰኑ ፓርቲዎች ወይም ዕጩዎች ድምፅ እንዲሰጡ ቀጥተኛ ምክር ሲሰጡ መታየታቸውን ኅብረቱ ገልጿል።

በ87 ጣቢያዎች ደግሞ መራጮች ጣታቸው ላይ የማይለቅ ቀለም ሳይቀቡ ድምፅ እንዲሰጡ መፈቀዱን ሪፖርቱ ያሳያል።

ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው፣ በ64 የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በሕግ የተደነገገው ማኅተም ሳይደረግባቸው ለመራጮች መታደላቸው ተመዝግቧል።

እንዲሁም በ40 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት በተወሰነ ጊዜ መቋረጡን ታዛቢዎቹ መመልከታቸው ተጠቁሟል።

በድምፅ ቆጠራ ሂደትም በ12 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ማስፈራራት ወይም የውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት መኖሩን ሲገልጽ፣ በ77 ጣቢያዎች የምርጫ አስፈጻሚዎች ራሳቸው በድምፅ መስጫ ወረቀቶች ላይ ምልክት ሲያደርጉ መታየታቸውን አስታውቋል።

 ኅብረት ለምርጫ እንደገለጸው፣ እነዚህ ግኝቶች በ7ኛው አገራዊ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥና የቆጠራ ሂደት ላይ የተስተዋሉ ዋና ዋና የሕግና የአሠራር ግድፈቶችን የሚያሳዩ ሲሆን፣ ዝርዝር ግምገማው በቀጣይ ሪፖርቶች እንደሚቀርብ ተገልጿል ብሏል ዘገባው።

 

 


2 min read

Published

By Demeke Kebede

Source: SBS


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Stream now