Watch FIFA World Cup 2026™

LIVE, FREE and EXCLUSIVE starting June 12 2026

የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የግማሽ ቀን ውሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጫ፣ የታዛቢዎች ምልከታ፣ የፖለቲካ መሪዎች ተሳትፎ እና የሴቶች ውክልና

ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በኢትዮጵያ 7ኛው ጠቅላላ ብሔራዊ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ተከናውኗል፡፡ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል “በተወሰኑ ቦታዎች” የድምፅ መስጠት ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ የተቋረጠባቸው የምርጫ ጣቢያዎች አሉ፡፡

gettyimages-2278508116-612x612.jpg
A voter casts her ballot at the Shalla Park polling station in Addis Ababa on 1 June 2026 during the 2026 Ethiopian parliamentary elections. Ethiopians began voting on 1 June 2026 in parliamentary elections, with the party of outgoing Prime Minister Abiy Ahmed, who is running for another term, expected to win. Around 50 million voters are eligible to vote in the election for members of parliament, who will in turn select the prime minister. Credit: MARCO SIMONCELLI/AFP via Getty Images

አንኳሮች

  • 50,188 የምርጫ ጣቢያዎች በሰዓቱ የምርጫ ሥነ ሥርዓቱን አስጀምረዋል
  • 39,723 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የምርጫ ታዛቢዎች ተገኝተዋል
  • 143 የምርጫ ጣቢያዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት አልተከፈቱም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት በአብዛኛው በታቀደለት ሰዓት መጀመሩን አስታውቋል።

የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ በስካይላይት ሆቴል በሰጡት የምርጫው የግማሽ ቀን ሁኔታ መግለጫ በአጠቃላይ 50,188 የምርጫ ጣቢያዎች በሰዓቱ መከፈታቸውን ገልጸዋል።

Melatwork.png
Melatwork Hailu, Chairperson of the National Election Board of Ethiopia (NEBE). Credit: PD

ሰብሳቢዋ መራጮች ከማለዳ ጀምሮ ወደ ጣቢያዎች በመግባት ድምፃቸውን ሲሰጡ መዋላቸውንም አስረድተዋል፡፡

ቦርዱ በዕለቱ ሁሉም ጣቢያዎች በትክክል እንዳልተከፈቱ አስታውቋል።

በቦርዱ ሰበብሳ ሜላትወርቅ መግለጫ መሠረት በ695 የምርጫ ጣቢያዎች የድምፅ አሰጣጥ ከ12፡30 እስከ 1፡00 ሰዓት መካከል ዘግይቶ መጀመሩ ተመልክቷል።

የቦርዱ ሰብሳቢ እንደገለጹት “የቴክኒክና የአስፈፃሚ ዝግጅት ተግዳሮቶች በአንዳንድ ጣቢያዎች መዘግየት አስከትለዋል” ያሉ ሲሆን፤ አክለውም፤ ቦርዱ ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም 143 የምርጫ ጣቢያዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ሙሉ በሙሉ አለመከፈታቸው ተገልጿል። በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተወሰኑ አካባቢዎች ይህ ችግር የተለይቶ መታየቱ ተነግሯል።

ቦርዱ በመግለጫው “የፀጥታ ችግሮች በምርጫ ሂደት ላይ ቀጥታ ተጽዕኖ አሳድረዋል” ያሉት ሰብሳቢዋ በእነዚህ ጣቢያዎች የሚወሰን እርምጃ እንደሚኖር ጠቅሰዋል።

በአንዳንድ ክልሎች የተጀመረ የድምፅ አሰጣጥ በሂደት መቋረጡም ተመልክቷል። በተለይ በጸጥታ ተግዳሮት ያለባቸው አካባቢዎች የምርጫ እንቅስቃሴ ተቋርጧል። ቦርዱ እነዚህን ሁኔታዎች “በቅርበት እየተከታተልን ነው” ብሏል።

ምርጫው ከ52,000 በላይ የምርጫ ጣቢያዎች እና ከ369,000 በላይ የምርጫ አስፈጻሚዎች ተሳፎ እየተካሄደ መሆኑ ተመልክቷል።

በእዚሁ ምርጫ 24 አገር አቀፍ እና 45 ክልላዊ ፓርቲዎች በመሳተፍ 10,438 ዕጩዎች በውድድር ላይ እንደሚገኙ ተጠቅሷል።

በታዛቢዎች ተሳትፎ ረገድ ከ55 ሲቪክ ማኅበራት በላይ በምርጫው ላይ ተሰማርተዋል። 1,572 አስተባባሪዎች እና ከ64,770 በላይ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎች ተሳትፈዋል። በተጨማሪም 39,723 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ታዛቢዎች መገኘታቸው ተመልክቷል።

በቦርዱ መግለጫ መሰረት በ1,978 ጣቢያዎች ደግሞ የፖለቲካ ወኪሎች ሂደቱን እየተከታተሉ ናቸው።

በአፍሪካ ሕብረት የታዛቢ ቡድን መሪ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ምርጫውን በተለያዩ ጣቢያዎች በመታዘብ ላይ ናቸው። በመግለጫቸውም “የድምፅ አሰጣጡ በጥሩ ሁኔታ ተጀምሯል” ያሉ ሲሆን፤ አያይዘውም “ሂደቱ በስኬት እንደሚቀጥል ጽኑ እምነት አለን” ሲሉ ተናግረዋል።

kenyatta.png
Uhuru Kenyatta, the head of the African Union Election Observation Mission (AUEOM). Credit: PD

በተመሳሳይ የኢጋድ ታዛቢ ቡድን በዶ/ር ስፔሲዮዛ ዋንዲራ መሪነት የምርጫ ሂደቱን እየተከታተለ ይገኛል። ቡድኑ በተለይ በተለያዩ ጣቢያዎች የታየውን ሰላማዊ ሁኔታ አድንቆ ገልጿል። የመጀመሪያ ግምገማው ከሂደቱ መጨረሻ በኋላ ይፋ እንደሚደረግ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ኮንፌዴሬሽን በምርጫው ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ከፍ ያለ መሆኑን አስታውቋል። ከ54,057,861 መራጮች 49.3% ሴቶች መሆናቸውን የገለጸው ኮንፌዴሬሽኑ በዕጩዎች በኩል ግን ዝቅተኛ ድልደላ ( 25.8% ሴቶች ) መደረጉን ይፋ አድርጓል።

gettyimages-2278525091-612x612.jpg
Voters hold umbrellas to protect themselves from the sun as they queue to cast their ballots outside the Beshale Katla polling station in Addis Ababa, on 1 June 2026, during the 2026 Ethiopian parliamentary elections. Credit: MARCO SIMONCELLI/AFP via Getty Images

“ሴቶች በምርጫ ሂደት ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ አሳይተዋል” ያለው የኮንፌዴሬሽኑ መግለጫ። በአንዳንድ አካባቢ እስከ 71.4% የሴት ዕጩ ተሳትፎ መመዝገቡ ተገልጿል።

በምርጫው የተለያዩ የፖለቲካ ሰዎችና መሪዎች ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ርእሰ ብሔር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ድምፃቸውን በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ በሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ሰጥተዋል። ከድምፅ ከሰጡም በኋላ “54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መመዝገባቸው ታሪካዊ የዴሞክራሲ ተሳትፎ ማሳያ ነው።” ብለዋል። በተጨማሪም ሁሉም ዜጎች በሀገራቸው የፖለቲካ ውሳኔ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዕጩ ተወዳዳሪነት በቀረቡበት በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን የጎማ 2 ምርጫ ክልል፣ በበሻሻ የድምፅ ጣቢያ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማለዳውን ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

pm vote.png
Prime Minister Abiy Ahmed has voted in Ethiopia's 7th General Election in Beshasha, 1 June, 2026. Credit: PP

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድምፃቸውን ከሰጡ በኋላ ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የውጭ ኃይሎችና የሀገር ውስጥ ተላላኪዎቻቸው ምርጫውን ለማደናቀፍ ያደረጉትን ሙከራ ሕዝቡ በተግባር አክሽፎታል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱን ታሪካዊ ጠላቶች ያሏቸውን በማውገዝ፣ ኢትዮጵያ የውጭ ኃይሎችን አጀንዳ ሳትቀበል የራሷን የዲሞክራሲ መንገድ መቅረጽ እንደምትችል አጽንኦት ሰጥተዋል።

"የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ አይቻልም የሚል እምነት እንዲያዝ የሚገዟቸውን ኃይሎች ገዝተው በስፋት አሰማርተዋል። ይሁን እንጂ ይህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት፣ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመገንባት የሚሻውን፣ የሚፈልገውን ለመወሰን መካሪና ገሣጭ እንደማያስፈልገው ያሳየበት እርምጃ ነው"
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ሕዝቡ ማልዶ በነቂስ መውጣቱ ለመንግሥታቸው ትልቅ የሕዝብ ድጋፍ ማሳያ መሆኑንም አመላክተዋል።

EPRP.png
Mistre Selassie, Secretary of EPRP. Credit: PD

 በተቃዋሚ ፓርቲዎችና የግል ተመራጮች በኩል ተከታታይ መግለጫዎች እየተጠበቁ ነው።


3 min read

Published

Updated

By Demeke Kebede

Source: SBS


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Stream now