“ለሀገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ” መርሃ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀነዓ ያደታ እና የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ፋና እንደዘገበው መርሃ ግብሩ ከረፋዱ 5:30 ላይ በተለያዩ ስፍራዎች ለሁለት ደቂቃ የተካሄደ ሲሆን ከዚያ ቀደም ብሎ የተለያዩ ስነ ስርዓቶች ተካሄደዋል፡፡
በተመሳሳይ “ለሀገር መከላከያ ክብር እቆማለሁ” መርሃ ግብር በዛሬው እለት በተለያዩ አካባቢዎች ተካሂዷል።
በአዲስ አበባ በዋነኛ መርሃ ግብሩ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከረፋዱ 5:30 ላይ ለ2 ደቂቃ የተካሄደ ሲሆን ከዚያ ቀደም ብሎ የተለያዩ ስነ ስርዓቶች ተከናውነዋል።
በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች አስተባባሪነት በተዘጋጀው በዚህ ስነ ስርዓት ሁሉም ኢትዮጵያውያን በያሉበት ሆነው ለአንድ ደቂቃ ቀኝ እጃቸውን በግራ ደረታቸው ላይ አድርገው በመቆም ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ክብር እንዲገልፁ በማሰብ ነው።
እናም በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ለአንድ ደቂቃ የመቆም ሥርዓቱ ሲጠናቀቅ በቀጣዩ አንድ ደቂቃ ባሉበት ሆነው ባለማቋረጥ በማጨብጨብ ለመከላከያ ያለውን ድጋፍ መግለፃቸውን የኤስ ቢ ኤስ ዘጋቢ ተመልክቷል።
ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ሰራዊቱና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ለሃገር መከላከያ ክብር እንቆማለን በሚለው መርሃ ግብር ላይ በአበበ ቢቂላ እስታዲየም ድጋፋቸውን ገልፀዋል። በዚህ ዝግጅት በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች እንደተገኙ አዘጋጆች ለኤስቢኤስ ገልፀዋል።
በተመሳሳይ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች ለመከላከያ ሰራዊት ፣ለአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ አባላት ክብር የመግለጥ ስነ ስርዓት በድምቀት ተከናውኗል።
በባሕር ዳር የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድ አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት መከናወኑን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
አውስትራሊያን ጨምሮ በባሕር ማዶ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በሥነ ሥር ዓቱ ተሳትፈዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የትግራይ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሺያ አባላት እጃቸውን በሶስት ቀናት ለፌዴራሉ ሠራዊት እንዲሰጡ ተጥሎ የነበረው ገደብ ማክተምን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "በቀጣይ ቀናት የመጨረሻው ሕግ የማስከበር ወሳኝ ተግባር ይከናወናል" ብለዋል።
በሌላም በኩል ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት ገጥሞ ያለው ሕወሓት መሪ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረኪዳን ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ የአፍሪካ ሕብረትና ተመድ ጣልቃ እንዲገቡ ጥሪ አሰምተዋል።

