ቫይረስ - አፕ
የፌዴራል መንግሥቱ የኮቪድ - 19 ተከታታይ አፕን ይፋ አደረገ።
የሲንጋፖር ሶፍትዌርን የሚጠቀመው COVIDSafe አፕ የብሉቱዝ ኃይልን በመጠቀም የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎችን ዳታ ለጤና ባለ ሥልጣናት ያስተላልፋል።
መንግሥት አፑ የግል ዕለታዊ ማስታወሻን ከማገላበጥ ወይም 'የት ነበር የዋልኩት' ብሎ ለማስታወስ ከመቸገር የተሻለ መሆኑን አስገንዝቧል።
የጤና ሚኒስትር ግሬግ ሃንት ስለ ጠቀሚታው ሲያስረዱ፤
"COVIDSafe አፕ ምርመራ ሳያካሂዱ በቫይረሱ ተይዘው ማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉን ለመፈለግ፣ ሰዎች ቀደም ብለው እንዲመረመሩ፣ ሕክምና እንዲያገኙ፣ ሐኪሞቻችን፣ ነርሶቻችን፣ ቤተሰቦቻችንና ወዳጆቻችን ደህንነታቸው እንዲጠበቅ፣ ሕይወትን ለማዳንና ለመጠበቅ የሚያግዝ ነው" ብለዋል።
ቫይረስ - ሕልፈተ ሕይወቶች
አውስትራሊያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተነሳ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 83 ደረሰ።
አንድ ዕድሜያቸው 83 የሆነ አረጋዊ ቪክቶሪያ ሆስፒታል ውስጥ ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ ሌላ ዕድሜያቸው በ90ዎቹ ያሉ አዛውንት በታዝማኒያ ሜሪሲ ሆስፒታል ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል።
የቪክቶሪያ ጤና ሚኒስትር ጄኒ ሚካኮስ ቪክቶሪያ ውስጥ ሕይወታቸው ያለፈው አረጋዊ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎችን ቁጥር 17 ማድረሱን ተከትለው ሲናገሩ፤
"በአሁኑ ወቅት 21 ሰዎች ሆስፒል ውስጥ ይገኛሉ። ከዚያም ውስጥ 10ሩ የከፍተኛ ክብካቤ ሕሙማን ክፍሎች ውስጥ ይገኛሉ። 1265 ሰዎች አገግመዋል፤ ቪክቶሪያ ውስጥ 101,000 የኮቪድ - 19 ምርመራዎችን አካሂደናል" ሲሉ ገልጠዋል።
ቫይረስ - ረመዳን
የፓኪስታን ሙስሊሞች ለመጀመሪያ ጊዜ የኮረናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል መንግሥት የጣለው ገደብ ስር ሳሉ የረመዳን ጾምን ሲያካሂዱ፤ የምግባረ ሰናይ ድርጅቶች ድንጋጌውን ተከትለው ሰዎች መንገድ ዳር መፍጠር ስለማይችሉ ምግቦችን በካርቶኖች አሽገው ችግረኞች መጠለያዎቻቸው ውስጥ ሆነው እንዲፈጥሩ የረድኤት ችሮታዎቻቸውን አድለዋል።
የካራቺ ነዋሪ የሆነው አቂብ አሕመድ እንዲህ ባለ ሁነት ረመዳን ሲጾም መመልከቱ አዋኪ እንደሆነበት ገልጧል።
ፓኪስታን በአሁኑ ወቅት 12,000 ሰዎች በኮቪድ -19 የተያዙ ሲሆን፤ 256 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

