የአዲስ አበባ ጉዳይ በሕግ መነጽር ሲታይ

አንድ ከተማ የሁለት የሕግ አካላት ዋና ከተማ መሆን በራሱ ችግር ባይሆንም፣ የሁለቱን ባለቤቶች ድርሻ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ አለማስቀመጥ ግን የችግሮቹ ሁሉ መነሻ ይመስለኛል።

Addis Ababa

Friendship Square in the city of Addis Ababa, Ethiopia. Source: Getty

የኢትዮጵያ ፖሊቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ቅስቀሳ መስማት ካቆምኩ ቆይቻለሁ። ወድጄ አይደለም። ከሞላ ጎደል ሁላቸውም የሚያነሱት የማንነት ጥያቄና ከብልጽግና ፓርቲ መሻላቸውን እንጂ ከሱ የተሻለ ምን የኤኮኖሚና የፖሊቲካ አጄንዳ እንዳላቸው በግልጽ ለሕዝብ ስለማይነግሩን ትግላቸው የፖሊቲካ ሥልጣን ለመያዝና ሕዝቡን ደግሞ ማማ በሰማይ እያሉ ሊተገበር የማይቻል የውሸት ተስፋ ሲሰንቁለት ታይቶኝ፣ የማናቸውንም የምርጫ ቅስቀሳ ላለመከታተል ወስኜ ነበር።

ሰሞኑን ግን የአንዳንዶቹ በተለይም የኢዜማና የባልደራስ የምርጫ ቅስቀሳ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ለሕዝብ ቀርቦ ሳየው፣ እነዚህ ሰዎች ወይ ሞኝ አድርገውናል ወይም ደግሞ ራሳቸው ሞኝ ናቸው ከማለት አንዳንድ በቅስቀሳቸው ዙርያ በተለይም የአዲስ አበባን ማንነት በተመለከተ የሚያሰሟቸውን መፈክሮች ዋቢ አድርጌ የሚከተለውን ለማስፈር ተነሳሳሁ።

ዓላማዬ ከሕግ አንጻር ጉዳዩን ለመመርመርና እውኔታውን ለመራጩ ሕዝብ ለማሳወቅ እንጂ፣ የአንድም የፖሊቲካ ድርጅት አባል ወይም ደጋፊ ሳልሆን አገራዊ ጉዳዮችን በገለልተኝነት ለማየት ከሚሞክሩት ዜጎች አንዱ መሆኔ ከወዲሁ ይታወቅልኝ እላለሁ።


የአዲስ አበባ የማንነት ጥያቄ በአገሪቷ ውስጥ ካሉ የፖሊቲካ ጥያቄዎች ሁሉ እጅግ በጣም የተወሳሰበ እንደሆነ ከገባን ሰንብቷል። ችግሩ የሚመነጨው ከተማዋ የፌዴራሉም የኦሮሚያም ክልል ዋና ከተማ ከመሆኗ ይመስለኛል። የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሕገ መንግሥት አንቀጽ 6 አዲስ አበባ ዋና ከተማቸው እንደሆነ ይደነግጋሉ። አንድ ከተማ የሁለት የሕግ አካላት ዋና ከተማ መሆን በራሱ ችግር ባይሆንም፣ የሁለቱን ባለቤቶች ድርሻ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ አለማስቀመጥ ግን የችግሮቹ ሁሉ መነሻ ይመስለኛል።


ሰሞኑን አንዳንድ የፖሊቲካ ድርጅቶች የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ አዲስ አበባን በተመለከተ ከሚያነሷቸው መፈክሮች ሶስቱን ብቻ ላነሳ እወዳለሁ። የማነሳቸውም ችግር ላይ ተጨማሪ ችግርን ለመደረብ ሳይሆን፣ የችግሮቹን ምንነት ከሕግ አንጻር ለማሳየትና መፍትሔያቸውን በአጭሩም ቢሆን ለመጠቆም ነው። የማተኩርባቸው ሶስቱ መፈክሮች፣
ሀ) “አዲስ አበባን ማዳን ኢትዮጵያን ማዳን ነው”፣ ይህን የባልደራስን መፈክር በግርድፉ ካየነው ግልጽ ያልሆነና ዝም ብሎ የመራጭን ቀልብ ለመሳብ የታቀደ ይመስለኛል። ባልደራስ ለመራጩ ሕዝብ ግልጽ ያልሆነ ለሱ ግን በምስጢር የደረሰው አንድ የጎረቤት አገር ርዕሰ ከተማችንን ለማውደም ማቀዷን የጸጥታ መረጃ ደርሶት ይሆናል ብሎ መገመት ይቻላል። ይህ ከሆነ ደግሞ እናት አገራችንና ዋና ከተማችንን ከወራሪ ኃይል የመከላከሉ ኃላፊነት የባልደራስ ብቻ ሳይሆን የመላው ዜጋ ግዴታ ስለሆነ ወራሪው ኃይል ማን እንደ ሆነ በግልጽ መነገር አለበት።

ከሁሉም በላይ ደግሞ መንግሥት የዚህን የዋና ከተማችንን በውጪ ኃይል የመወረር ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶት መከላከያ ሠራዊታችንን ከያሉበት መልሶ በአምስቱም የአዲስ አበባ መግቢያ በሮች ላይ አሰልፎ የመከላከል ዝግጅቱን መጀመር አለበት። አዲስ አበባን ከውጭ ወራሪ ኃይል ማዳን እውነትም ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪ ኃይል ማዳን ነው። ባልደራስን የምንጠይቀው ግን እንደው ዝም ብሎ አዲስ አበባ ልትወረር ነው ከማለት ወራሪው ኃይል ማን እንደሆን አስቀድሞ ቢነግረን፣ የጠላታችን ማንነትና፣ ጠንካራና ደካም ጎኑን፣ ብሎም ደግሞ ከሱ ጋር አብረው ሊወጉን የሚዶልቱትን አካላት ገምግመን የመከላከል አቅማችንን በዚያው ልክ እንድናዘጋጅ ይረዳን ነበር።


ለ) “አዲስ አበባ ላይ ማንም ልዩ ጥቅም አይኖራትም”። ይህ የባልደራስም የኢዜማም መፈክር ነው። ሁለቱም ያነጣጠሩት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49(5) ሥር የሰፈረውን “የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም” ላይ ነው። የአማራ ክልል በባሕር ዳር ላይ፣ የሶማሌ ክልል በጂግጂጋ ላይ፣ የቤንሻንጉል ክልል በአሶሳ ላይ ወይም የትግራይ ክልል በመቀሌ ላይ ያላስፈለጋቸውን “ልዩ ጥቅም” የኦሮሚያ ክልል በራሱ ክልል ዋና ከተማ ላይ ለምን “ልዩ ጥቅም” እንዳስፈለገው ባይገባኝም፣ “ልዩ ጥቅም” የተባለው ሓረግ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ ተቀምጧልና አንድ ቀን መፍትሔ እስኪገኝለት ድረስ፣ ለጊዜው ዛሬ ባለው ሁኔታ ጉዳዩን በደንብ ለመረዳት ሶስት ተጓዳኝነት ያላቸውን ጉዳዮችን ጠቅሶ ማለፉ ጠቃሚ ይመስለኛል።


1) የልዩ ጥቅሙ ተጠቃሚ ማነው? የዚህ ልዩ ጥቅም ብቸኛ ተጠቃሚ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ እንደ ተቀመጠው የኦሮሚያ ክልል ነው። አንዳንዶች ግን አውቀውም ሆነ በስሕተት “የኦሮሞዎች ልዩ ጥቅም” ብለው ሕዝቡን ሲቀሰቅሱበት ይስተዋላል።
2) ልዩ ጥቅሙ ለምን አስፈለገ? ልዩ ጥቅሙ ያስፈለገበት ምክንያት ደግሞ፣ ሀ) አዲስ አበባ ከተማ ከሌሎቹ የዘጠኝ ክልሎች ዋና ከተማ በተለየ መልኩ ሁለት ሕጋዊ ባላቤት ስላላት፣ ለ) የምትገኘው በኦሮሚያ ውስጥና በሁሉም አቅጣጫ በኦሮሚያ የተከበበች ስለሆነች እና ሐ) ከ “ሀ” እና “ለ” ጋር የተያያዙ፣ የአገልግሎት አቅርቦት፣ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና ሁለቱን ባለቤቶች የሚያስተሳስር አስተዳደራዊ ጉዳዮች ስላሉ ነው።

3) ይህንን አወዛጋቢ እየሆነ ለመጣው ጉዳይ መፍትሔውስ ምን ይሆን? ችግሩ ሕገ መንግሥቱ ነው ተብሎ ከታመነበት፣ መፍትሔውም ሕገ መንግሥቱ ውስጥ መገኘት አለበት። ዛሬ ይህንን ልዩ ጥቅም ከሕገ መንግሥቱ ለመሠረዝ የሚፈልጉ ቡድኖች በለስ ቀንቶአቸው አራት ኪሎ ቢገቡ፣ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 104 እና 105 ላይ በተቀመጠው መሠረት ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል የሚወክሉትን ሕዝብ ጥያቄ ሊመልሱ ይችላሉ። ከሕገ መንግሥቱ ውጪ ሊያስኬድ የሚችል ጎዳና የለም። አብዮት እናካሄዳለን ካልተባለ በስተቀር!

ሐ) “አዲስ አበባ እስካስፈለጋት ድረስ ትሰፋለች”፣ ይህ ደግሞ የኢዜማ መፈክር ነው። አዎ ከተሞች ይሰፋሉ፣ ይጠባሉ፣ ወይም ደግሞ ከናካቴው ከምድረ ገጽ ላይ ይጠፋሉ። የሰው ልጅ ታሪክ ሶስቱንም ዓይነት አሳይቶናል። ዛሬ ካለንበት ቦታ ላይ ሆነን ስንገመግመው፣ አዲስ አበባ የመስፋት ዕድሏ የሰፋ ነው። ከተሞች ሲሰፉ ወደ አንድ ጎረቤት ወደ አለው አካል ነው። በአየር ላይ አይደለም። ዋናው ጥያቄ ጎረቤት ያለው መሬት ባዶ ሜዳ ነው ወይስ ባለቤት አለው? አዲስ አበባን የወሰድን እንደሆነ፣ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ በሁሉም አቅጣጫ በኦሮሚያ የተከበበች ስለሆነ፣ በአራቱም አቅጣጫ ብትሰፋ ወደ ኦሮሚያ ክልል ነው።

ከተሞች ደግሞ ልክ እንደ ማንኛውም በዚህ ምድር ላይ እንደሚተከሉ ሰው ሰራሽ ግንባታ/ተቋሞች የተከለለ የራሳቸው የሆነ አስተዳደራዊ ድንበር አላቸው። የአስተዳደራዊ ድንበር መኖር ጥቅሙ፣ በውስጣቸው ለሚኖሩ ዜጎች ሕጋዊ መብታቸውን ለማስጠበቅና፣ ለአስተዳደሩ ደግሞ ለኗሪው ሕዝብ አስፈላጊውን አገልግሎት ለማቅረብ ነው። ባጭሩ ከተሞች የመስፋታቸውን ያሕል፣ የግድ አስተዳደራዊ ድንበር ደግሞ ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው።

አዲስ አበባን ከመስፋት የሚያቆም ኃይል አይኖርም። እንደ ማንኛውም ከተማ ስሟን ይዛ ታድጋለች፣ ትሰፋለች። ለወደፊትም እስከ ቢሾፍቱና አዳማ፣ ሰበታና አምቦ ድረስ ልታድግ ትችላለች። የከተማዋ አስተዳደራዊ ድንበር ግን በህግ ተወስኖ ከተከለለት ውጭ ሊሰፋ አይችልም። የአዲስ አበባን የመስፋት ጥያቄ በበለጠ ለመረዳት የፌዴራል አሜሪካን ዋና ከተማ የዋሺንግተን ዲሲን ሕጋዊ ሰውነት ለአብነት መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል።

ዋሺንግተን ዲሲ በ1790 ዓ/ም የሜሪላንድና የቪርጂንያ ስቴቶች በመዋጮ በሠጡት 68 ስኩዌር ማይል ላይ የተፈጠረችና ዛሬ 700,000 ዜጎች የሚኖሩባት የፌዴራል አሜሪካ ርዕሰ ከተማ ስትሆን፣ በሂደት ግን ወደ ሜሪላንድና ቪርጂኒያ ስቴቶች ሰፍታ ዲሲ ሜትሮ ተብላ ትታወቃለች። ህጋዊ የአስተዳደር ድንበሯ ግን በ1790 ዓ/ም የፌዴራሉ ርዕሰ ከተማ እንድትሆን በህግ ተደንግጎ ከተከለለላት 68 ስኩዌር ማይል ውጪ በአንዲት ኢንች እንኳ አልጨመረም። ከተማዋ ግን ወደ ጎን ሰፍታ ዛሬ ከ 6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ “የዲሲ ሜትሮ” ነዋሪዎች የሚተዳደሩት፣ ግብር የሚከፍሉና የመምረጥም ሆነ የመመረጥ ህጋዊ መብታቸውን የሚጠቀሙት በሜሪላንድና በቪርጂኒያ ስቴቶች ሕግና ደንብ መሰረት ነው።

ከዚህ የምንረዳው ዋናው ቁም ነገር፣ ከተሞችን እንዳይሰፉ ማድረግ አይቻልም። አስተዳደራዊ ድንበር ማበጀት ግን ግዴታ ነው የሚለውን ነው። አስተዳደራዊ ድንበር የሌለው በምድራችን ላይ አንድም ከተማ የለምና!

ለመደምደም ያሕል፣

የፖሊቲካ ድርጅቶቻችን እንደው ፈርዶባቸው መፈክር ይወዳሉ። የሚያሰሙት መፈከር ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ወይም አይሆንም ብለው አስበውበት ሳይሆን የመራጩን ሕዝብ ድምጽ ለማግኘት ሲባል ብቻ “ይህን ወይም ያንን አደርግልሃለሁ” በማለት የሕዝቡን ቀልብ ይስባሉ። ሊሳካም ላይሳካም ለሚችል ነገር ሕዝቡን የውሸት ተስፋ ከመመገብ፣ “ብትመርጡንና ተሳክቶልን ፓርላማ ብንገባ ለምሳሌ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 49 ለማሻሻል ጥረት እናደርጋለን” ቢሉ የሚሻላቸው ይመስለኛል።

ሕገ መንግሥትን ማሻሻል ደግሞ ቀላል ነገር አይደለም። የሕገ መንግሥቱን አንዲት አንቀጽ ለማሻሻል ይቅርና የማሻሻል ሃሳቡን እንኳ በአጄንዳ ለማስያዝ የአሥሩንም ክልል ሕዝቦች አዎንታዊ መልስ ስለሚጠይቅና፣ አንዳንድ ክልሎች ደግሞ አንቀጹ እንዳይነካባቸው ሊፈልጉ ስለሚችሉ፣ ገና ፓርላማ ሳትገቡና ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ያላችሁን አቅም ሳትገመግሙ፣ የመራጩን ሕዝብ ልብ ማንጠልጠል በለስ ሳይቀናችሁ ቀርቶ አንቀጹን ማሻሻል ሲያቅታችሁ፣ በሕዝቡ ዘንድ አመኔታ ያሳጣችኋልና በጥብቅ አስቡበት እላለሁ። ያ እንዳለ ሆኖ ግን፣ በለስ ቀንቶአችሁ “የተከበሩ” ለመባል ያብቃችሁ እላለሁ።
******
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14 ቀን 2021 ዓ/ም
wakwoya2016@gmail.com


Share

Published

By Bayisa Wak-Woya

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service
የአዲስ አበባ ጉዳይ በሕግ መነጽር ሲታይ | SBS Amharic