ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጥቂት ጊዜያት በፊት "ሠራዊታችን ትናንት ምሽት በአዲግራት ዙሪያ ያሉትን አካባቢዎች ከተቆጣጠረ በኋላ፣ ዛሬ ደግሞ አዲግራትን ከሕወሓት ኃይል ሙሉ በሙሉ ነፃ አውጥቷል" ሲሉ አስታወቁ።
አያይዘውም "የፌደራል መንግሥት በተቆጣጠራቸው ከተማዎችና አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎች፣ በጸጥታ ኃይሎች ጥበቃ እየተደረገላቸው ወደ ዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው" መመለስ እንደጀመሩና "ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን፣ ሰብዓዊና ማኅበራዊ ፍላጎቶች የሚሟሉበትን መንገድ" መንግሥታቸው እንደሚያመቻች ገልጠዋል።
በፌዴራል መንግሥቱ የተቋቋመው ከፍተኛ ኮሚቴም አሥፈላጊና ወቅታዊ እገዛዎችን ለማቅረብ የሚያስችሉ መረጃዎችን ለማሰባሰብና ክስተቶችንም የሚያጣሩ ልዑካን ወደ ሥፍራው እንደተላከና ኮሚቴው "ባለፉት ቀናት መኖሪያቸውን ጥለው የተሰደዱትን ዜጎች ሁሉ ወደ ቀያቸው ለመመለስ እና ለማቋቋም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር መሥራቱን" እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
በማጠቃለያቸውም "የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ አጠቃላይ ደኅንነት እና ጤንነት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጥ ስለ ሆነ፣ በትግራይ ክልል መረጋጋት እንዲሰፍን እና ዜጎቻችን ከጉዳት እና እጦት ነፃ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን" ብለዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አክሱምንና አድዋን ሙሉ በሙሉ እንዲሁም የአዲግራትን ዙሪያ በትናንትናትው ዕለት መቆጣጠሩ የተገለጠ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ወደ መቀሌ እያመራ መሆኑ ተገልጧል።
በሕወሓት በኩል የከተሞችን መያዝ አስመልክቶ ለጊዜው ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ አልተደመጠም።

