በአፋር ክልል ደቡባዊ ዞን በአምስት ወረዳዎች የአዋሽ ወንዝ ባደረሰዉ የጎርፍ አደጋ ከ130ሺ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸዉን የአፋር ክልላዊ መንግሥት ገለጠ፡፡
ምንም እንኳ የክልሉ መንግሥት የአዋሽ ወንዝ ደቅኖት ያለውን የጎርፍ አደጋ ለመገደብ የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥትና አዋሽ ተፋሰስ ባለስልጣን ጋር በርካታ ጥረቶችን ቢያደርግም የክረምት ዝናቡ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑ ተነግሯል፡፡
በጎርፍ ተከበው ያሉትን ሰዎች ሕይወት ለመታደግ ሁለት ሂሊኮፕተሮች ሰዎችን ከሥፍራው የማውጣት ተግባራትን እየፈጸሙ ነው።
የጎርፍ አደጋው በአፋር ክልል ደቡባዊ ዞን ባደረሰው ጉዳት ሳቢያ የአገልግሎት ተቋማትና መሠረተ ልማቶች የወደሙ ሲሆን በሺዎች ሄክታር የሚቆጠር ማሳም ከጥቅም ውጪ ሆኗል።
በጎርፉ አደጋ ለመፈናቀል የተዳረጉት ወገኖች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እርዳታዎችን መንግሥት ፈጥኖ እንዲያደርስላቸው እየጠየቁ ነው፡፡

