በሁለት አጥፍቶ ጠፊዎች በተሰነዘረ የቦምብ ጥቃት 12 የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮችን ጨምሮ በታሊባን ቁጥጥር ስር የወደቀችውን አፍጋኒስታንን ለቅቀው ለመውጣት ካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ዙሪያ ተሰባስበው የነበሩ 70 ሰላማዊ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በካቡል ሰዓት አቆጣጠር ሐሙስ ከቀትር በኋላ ሲሆን 143 ያህል ሰዎችም ቆስለዋል።
ጥቃቱን አስመልክቶም እስላማዊ ስቴት ኬሆራሳን (ISIS-K) የተባለው ቡድን ኃላፊነቱን ወስዷል። እርምጃውንም የወሰደው "በአስተርጓሚዎችና የአሜሪካን ጦር ተባባሪዎች" ላይ እንደሆነ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ጥቃቱን አስመልክቶ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በሰጡት መግለጫ ድርጊቱ ጦራቸውን፣ ዜጎቻቸውንና ባለ ቪዛዎችን እስከ ኦገስት 31 ከማጓጓዝ እንደማያግዳቸው አስታውቀዋል።
አክለውም ዩናይትድ ስቴትስ የበቀል እርምጃ እንደምትወስድ ሲያስጠነቅቁ "ይቅር አንልም፤ አንረሳምም። አድነን አፀፋውን እናስከፍላችኋለን" ብለዋል። ሕይወታቸውን ያጡትን የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮችም "ጀግኖች" ብለው አወድሰዋቸዋል።
ክክስተቱ ጋር በተያያዘም አፍጋኒስታን የሚገኙ የአፍጋኒስታንያውያን-አውስትራሊያውያንን ሁኔታ አስመልክቶ ለጊዜው ይህ ይሆናል ለማለት እንደሚያውክ የአውስትራሊያ መከላከያ ሚኒስትር ፒታር ዳተን ተናግረዋል።
አውስትራሊያ በስምንት ቀናት ውስጥ 4000 ሰዎችን ከአፍጋኒስታን ያስወጣች ሲሆን ሁሉም የአውስትራሊያ ወታደሮች ለቅቀው ወጥተዋል።

