የአፍሪካ ኅብረት ሰላምን ለማስፈን ሲባል የኢትዮጵያ መንግሥት ሕወሓት ትጥቁን የሚፈታ ከሆነ ሕወሓትን ከአሸባሪ ባሕር መዝገቡ እንዲፍቅ፣ የሕወሓትን ቅሬታዎችን እንዲያደምጥና በትግራይም ምርጫ እንዲካሔድ እንዲያደርግ ሲል ጠይቋል።
በሌላም በኩል በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት በኩል ሰላማዊ ድርድር እንዲረግ ጥረት በማድረግ ላይ ያለችው ኬንያም ተመሳሳይ ጥሪ አቅርባለች።
በሰሞኑ የአዲስ አበባ ጉብኝታቸው ወቅት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው የተወያዩት የኬንያዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሬይሼል ኦማሞ የሰሜኑን ጦርነት ለማብቃት በመንግሥት በኩል "አሳማሚ ስምምምነት" ላይ ሊደርስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት የኬንያ ቋሚ ተጠሪ ዶ/ር ማርቲን ኪማኒ ይህንኑ የመንግሥታቸውን አቋም በሚያንፀባርቅ መልኩ ከቱኒዝያ፣ ኒጄር፣ ኒዤር፣ ሴይንት ቪንሴንትና ግሪናዲኔስ (A3 Plus 1) ጋር በጋራ ባወጡት መግለጫ "የኢትዮጵያ መንግሥት ለፖለቲካዊ ንግግር ሲባል ሁሉንም የአስተዳደራዊና የፀጥታ መሰናክሎች እንዲያነሳ በአፅንዖት እናሳስባለን" ብለዋል።
አክለውም "የትግራይ ታጣቂ ተዋናዮች ሕወሓት ወይም ትዲኃ ከአጎራባች ከፍለ አገራት እንዲወጣና ከትግራይ ውጪም እንዳያመራ በአፅንዖት እናሳስባለን" በማለት ጥሪ አቅርበዋል።
ይህንኑ የ A3 Plus 1 ጥሪን ተከትሎም የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች ኮሚሽነር ባንኮሌ አዶዬ ለጋዜጠኞች በስጡት መግለጫ "በእኛ በአፍሪካ ኅብረት በኩል ወታደራዊ መፍትሔ ዕውን የመሆኑ ሁኔታ ተአማኒነት የለውም። ስኬታማም አይሆንም። ሰላማዊ ንግግርን አስመልክቶ ታጣቂ ቡድናት አመፅን እስካወገዙ ድረስ ሁሉም ተካታች እንዲሆኑ ሊበረታቱ ይገባ። ብቸኛው የመውጫ መንገድ የድርድር ስምምንት ነው" በማለት ተናግረዋል።
በመጪው ሳምንት አዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው የተሰየሙት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚደንት ኦሉሲገን አባሳንጆ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ቀንድ ጉብኝታቸውን ይጀምራሉ።
ሆኖም በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ ተጠሪ አምባሳደር ታየ አፅቀ ስላሴ ዓለም ሕወሓትን የግጭቱ ሰላባ አድርጎ የማየት የተዛባ አመለካከት እንዳለው ጠቁመው በተፃፃራሪው "ሕወሓት ወንጀለኛ ነው" ብለዋል።
አያይዘውም "የሕወሓትን የአመፅ መስፋፋትና ቀውስ በዝምታ ተውጠው ይሁንታ የቸሩቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የሕግ ማስከበር ዘመቻውን እንዲገታ ተፅዕኖ ሲያደርሱና የሰላም ጥሪ ሲያቀርቡ አስገራሚ ሆኖብናል" ብለዋል።
የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው የአፍሪካ ኅብረት አድሏዊነትን ጠቁመው፤ ድርጅታቸው ኅብረቱ ገለልተኛነቱን በግብር እንዲያሳይ የሚሻ መሆኑን አመላክተዋል።
አክለውም "ከቶውንም [የአፍሪካ ኅብረት] የትግራይ ሕዝብ ወይም መሪዎቹ ዘንድ ለመድረስ ሞክረዋልን?" ሲሉም ጠይቀዋል።

