የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቶች አብዛኛውን ጊዜ እንደ ተምሳሌታዊ ሁነት ቢታዩም የዘንድሮው የአህጉሪቱና የዓለም መሪዎች ንግግር ግን የአፍሪካን የወደፊት አቅጣጫ የሚወሰኑ ጥልቅ መዋቅራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ያመላከተና ያሉትን ፖለቲካዊ፣ ፋይናንሳዊና ተቋማዊ ውጥረቶች ያመላከተ ነበር ማለት ይቻላል።
የውሃ ዋስትና እንደ ኢኮኖሚያዊ መሠረተ-ልማት
የአንጎላ ፕሬዝዳንትና ተሰናባቹ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ዠዋው ማኑኤል ጎንሳልቬስ ሎሬንሶ ጉባኤውን ሲከፍቱ የውሃን ቀውስ በስትራቴጂካዊ ምልከታ ሊገልጹት ሞክረዋል።
“ውሃ የልማት ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ የፖለቲካ፣ የሞራል እና የስትራቴጂ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ጭምር ነው።” ሲሉ አፅንኦት ሰጥተውታል።
የሎሬንሶ ንግግር የጉዳዩን አሳሳቢነት የገለፀ መሆኑን በቁጥር ማስቀመጥ የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል።
በሕብረቱ መረጃ መሰረት ከ400 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን ንጹህ የመጠጥ ውሃ አያገኙም፤ የንፅህና አጠባበቅ ጉድለትም የህዝብ ጤናን፣ ምርታማነትንና የጾታ እኩልነትን እየጎዳ ይገኛል።
የአየር ንብረት ለውጥ በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ድርቅን እያባባሰ ነው፤ ፈጣን የከተሞች መስፋፋት ደግሞ በዋና ዋና ከተሞች ያለውን የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት ከአቅም በላይ እየሆነ ነው።
የውሃ ጉዳይ ከአፍሪካውያን ህልውና ጋር የተሳሰረ ነው። ውሃ በአፍሪካ ከግብርና ምርታማነትና ከምግብ ዋስትና ጋር፣ ከውሃ ኃይል ማመንጫና ከኢነርጂ መረጋጋት ጋር፣ በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) ሥር ከሚከናወን የኢንዱስትሪ መስፋፋት ጋር፣ ከአየር ንብረት ለውጥ መቋቋምና ከአደጋ መከላከል ጋር እና ከሕዝብ ጤና ሥርዓትና ለወረርሽኝ ካለ ዝግጁነት ጋር የተሳሰረ ነው።
ከውሃ ሁለንተናዊነት ባልተናነሰ የፋይናንስ እጥረት አሁንም የአፍሪካ ዕድገት ዋነኛው ማነቆ ነው። የአፍሪካ ዓመታዊ የመሠረተ-ልማት ፋይናንስ ፍላጎት ክፍተት ከ68 ቢሊዮን እስከ 108 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይገመታል።
ጠንካራ የአገር ውስጥ ሀብት ማሰባሰብና አዳዲስ የፋይናንስ ማዕቀፎች ካልተዘረጉ በቀር የውሃ ዋስትና ከምኞት ባለፈ በተግባር ላይ መዋል አይችልም። በሕብረቱ የመክፈቻ ንግግሮችም ትኩረት የተሰጠው ለዚህ ይመስላል።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) እና መዋቅራዊ ማነቆዎች
ፕሬዝዳንት ሎሬንሶ በመክፈቻ ንግግራቸው የአህጉሪቱ ተስፋ በሆነው የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና (AfCFTA) ላይ የታየውን መሻሻል አንስተዋል።
ሆኖም በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ አገራት እርስ በእርስ የሚያደርጉት ንግድ ከጠቅላላ የንግድ ልውውጣቸው ከ20 በመቶ በታች ነው። ይህም ከአውሮፓና ከእስያ የንግድ ትስስር አንጻር እጅግ ዝቅተኛ ነው።
የውሃና የኃይል እጥረት ለንግድ መስመሮች፣ ለግብርና ምርቶች ኤክስፖርትና ለኢንዱስትሪ መንደሮች እንደ መዋቅራዊ ገዲብ ሁነት ሆነው እያገዱ ይገኛሉ።
AfCFTA የኢኮኖሚ ትስስር ሞተር ከሆነ የውሃና የኃይል መሠረተ-ልማት ደግሞ የሞተሩ ነዳጅ ናቸው። የንግድ ቀጠናው የአህጉሪቱን የንግድ ዋጋ ሰንሰለት በማሳደግ ረገድ የሚሳካለት ከሆነ "አፍሪካ የተቀነባበሩ ምርቶችን ወይስ ጥሬ ዕቃዎችን መላኳን ትቀጥላለች?" የሚለው በውሃ መሠረተ-ልማት ጥንካሬ ይወሰናል።
የመሪነት ቀጣናዊ ሽግግር
የብሩንዲው ፕሬዝዳንት ኤቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ የ2026 የሕብረቱ ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸው አህጉራዊ መሪነቱ ወደ ምስራቅ አፍሪካ መዞሩን ያሳያል። የአፍሪካ ጅኦፖለቲካ አሁንም ከሽክርክሪት አለወጣም።
ሱዳን አሁንም በግጭት እየታመሰች ትገኛለች። በምስራቅ ኮንጎ (DRC) ያለው አለመረጋጋት ቀጣናዊ ስጋትነቱ ቀጥሏል። የሳህል ቀጠና ቀጣይነት ያለው የደህንነት ሽግግር ላይ ነው። የሶማሊያ መረጋጋት አሁንም በስሱ ላይ ነው።
የአፍሪካ ሕብረት አቅም፣ ተሰሚነትና ተዓማኒነት በ2026 የሚመዘነው በሚያወጣቸው መግለጫዎች ርዝመት ሳይሆን በሽምግልና በሚያመጣቸው ውጤቶችና በሚከተለው ስልታዊ ወጥነት ነው።
ጥያቄው ሕብረቱ የፖሊሲ ማዕቀፎች አሉት ወይ የሚለው ሳይሆን እነዚያን ለማስፈጸም የሚያስችል የፖለቲካ ተጽዕኖና የፋይናንስ ነፃነት አለው ወይ የሚለው ነው።
ሰላም፣ ብዙኃናዊነትና መዋቅራዊ ለውጥ
ፕሬዝዳንት ሎሬንሶ በሕብረቱ የስልጣን ዘመናቸው “የጠመንጃን ድምፅ ማጥፋት” ጥሪ ደጋግመው ቢያቀርቡም በአፍሪካ የሚመሩ የሰላም ተልዕኮዎች አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ በውጭ እርዳታ ላይ ጥገኞች መሆናቸው ውጤታቸው እምብዛም ነበር።
የጠመንጃን ድምፅ የማጥፋቱን ዓለምአቀፋዊ ትብብር በጎ ነበር በሚል ያሞካሹትም አልጠፉም። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ለጉባኤው ባደረጉት ንግግር ሕብረቱን “የባለብዙ ወገን ትብብር (Multilateralism) ተምሳሌት” ሲሉ ጠርተውታል።
በእርግጥ ዋና ጸሐፊው የዓለም አቀፍ አስተዳደር ለውጥ እንደሚያስፈልግ ሲያሳስቡ እንዲህ ብለዋል። "ይህ 2026 እንጂ 1946 አይደለም፤ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ሊኖራት ይገባል" ሲሉም አክለዋል።
ዳሩ ግን 54 አገራትንና 1.4 ቢሊዮን ሕዝብን የምትወክለው አፍሪካ አሁንም በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ተወካይ የላትም። ይህ የማሻሻያ ጥያቄ ከሞራል ግፊት ባለፈ ወደ መዋቅራዊ አስፈላጊነት መሸጋገር እንዳለበት ያመላክታል።
ተቋማዊ ሪፎርምና የፋይናንስ ሉዓላዊነት
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ተቋሙ ያለበትን የተጠያቂነት ጉዳይ በተመለከተ “ዜጎቻችን በተለይም ወጣቶችና ሴቶች ከእኛ የሚጠብቁት ተግባርን እንጂ መግለጫን አይደለም።” ብለዋል።
የሕብረቱ የሪፎርም አጀንዳ የ0.2 በመቶ የገቢ ዕቃ ቀረጥን ጨምሮ የፋይናንስ ነፃነትን የሚያረጋግጡ ስልቶችን ያካትታል። ሆኖም አፈጻጸሙ ወጥ አይደለም፤ የአገራት መዋጮ የመክፈል ሁኔታም አሁንም ለጋራ ዲሲፕሊን ፈተና ሆኖ ቀጥሏል።
ለዚህም ነው "የውጭ ለጋሾች ለሕብረቱ ፕሮግራሞች ከፍተኛ ድርሻ እስካዋጡ ድረስ ስልታዊ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ አዳጋች ሆኖ ይቆያል" የሚባለው።
የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ሽግግር አቅጣጫ
ኢትዮጵያ በመስተንግዶ ከዚህ ቀደሞቹ ጉባኤዎች የላቀ ትኩረት መስጠቷን አስመስክራበታለች። በከተማዋ የተሰሩ ስራዎችን በማስጎብኘትና አዲስ አበባ ለኮንፍረንስ ቱሪዝም ያላትን ዝግጁነት በተግባር ለማሳየት ጥረት የታየበትም ነበር።
ከቤተ መንግስት የእራት ግብዣ እና ከጎንዮች የመሪዎች ንግግሮች በተጨማሪ በአዲሱ የኮንቬንሽን ሴንተር የጣሊያን አፍሪካ ጉባኤን በማካሄድም የከተማዋን አዲስ ሁኔታ ለማስቃኘት የተደረገው ዝግጅት በአፍሪካውያን መሪዎች ዘንድ ውዳሴ ተችሮታል።
በሌላ መልኩ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት የሕብረቱ ጉባኤ የመክፈቻ ንግግር አፍሪካ ከዓለም አቀፍ ክስተቶች ተቀባይነት ወጥታ የራሷን አጀንዳ ወደ መቅረጽ መሸጋገር እንዳለባት አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) እና ዲጂታል መሠረተ-ልማትን በመጥቀስ ቴክኖሎጂን የሉዓላዊነት ምሰሶ አድርገው መሪዎች እንዲያተኩሩ ጥሪ አቅርበዋል።
“እውነተኛ ሉዓላዊነት የራሳችንን ትረካ እና የቴክኖሎጂ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ባለቤት መሆንን ያካትታል።” ያሉት ጠ/ሚ/ር ዐቢይ የአህጉራዊ ቴክኖሎጂያዊ ለውጥን አስፈላጊነት አመላክተዋል። በእሳቸው እይታ በአካላዊ መሠረተ-ልማት ላይ የሚደረገው ሽግግር በፍጥነት እየተለወጠ ባለው የዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል በዲጂታል ዘመናዊነት መታጀብ አለበት።
ሰብዓዊው የአፍሪካ ገጽታና የጉባኤው አንድምታ
ከጉባኤ አዳራሾች ውጭ የውሃ እጥረት የብዙዎች አፍሪካውያን የዕለት ተዕለት ስቃይ መሆኑ እሙን ነው። ዛሬም ውሃ ፍለጋ ኪሎ ሜትሮችን የሚጓዙ የገጠር ሴቶች እልፍ ናቸው። ንጹህ የመፀዳጃ ቤት አገልግሎት የሌላቸው የከተማ ነዋሪዎችም እንዲሁ። በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ቀያቸውን ጥለው የሚሰደዱ ወገኖች ህልቆ መሳፍርት የላቸውም።
ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው የአፍሪካ ሕዝብ ዕድሜው ከ25 ዓመት በታች በመሆኑ በዚህ የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤም ሆነ በየሀገራቱ ምክር ቤቶች የሚወሰኑ የመሠረተ-ልማት ውሳኔዎች የትውልዱን መረጋጋት ይወስናሉ። የውሃ ዋስትና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ስብጥር ስጋት (Demographic risk) አመራር ጉዳይ ጭምር ነው የሚለው የምሑራን አስተያየት ግዘፍ የሚነሳው የአፍሪካን ሰብአዊ ቀውስ ባሰብን ጊዜ ነው።
ከንግግር ወደ መዋቅራዊ አፈጻጸም
ጉባኤውን እንደታደመ ጋዜጠኛ (በእኔ ትዝብት) የ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ መክፈቻ ንግግሮች በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ያዘነበሉ ነበሩ።
- የውሃ ዋስትና የኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት አንኳር ማሰሪያ የመሆኑ ጉዳይ፣
- በፋይናንስ ነፃነት ላይ የተመሰረተ ተቋማዊ ሪፎርም (ለውጥ) አስፈላጊነት፣ እና
- የዓለም አቀፍ አስተዳደር ሥርዓት ወቅታዊ ሁኔታን እንዲያንጸባርቅ የማድረግ ጥያቄ ናቸው።
ይሁንና እነዚህ ሁሉ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች አንድ ፈተና ይጠብቃቸዋል የመፈፀምና የአፈጻጸም ቁርጠኝነት። በአጭሩ ውሃ ፖለቲካዊ ኃይል ከሆነ፣ ኃይል ደግሞ የኢኮኖሚ ምርታማነት ነው፤ ምርታማነት ደግሞ የህልውና ሉዓላዊነት ነው። ይህ ለማንም ግል የሆነ ያልተወሳሰበ አመክንዮ ነው።
በመሆኑም 39ኛው የመሪዎች ጉባኤ የአፍሪካ ትልቅ የለውጥ ምዕራፍ ወይም ሌላው ተራ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ የሚያልፍ መሆኑ የሚወሰነው በንግግሮች ሳይሆን በተግባራዊ አፈጻጸም ቀርጠኝነት ይሆናል።
ጉባኤው ትልቅ ግብ አስቀምጧል፤ ታሪክ ደግሞ ውጤቱን ይመዘግባል። ሁሉንም የምናየው ይሆናል።
*** ማስታዎሻ ፡ ይህ ትንታኔ ትኩረቱን ያደረገው በ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ በቀረቡ ይፋዊ ንግግሮች ላይ መሆኑን ለማስታዎስ እንወዳለን!
---
ደመቀ ከበደ ፡ ከአዲስ አበባ

