የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ትናንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ "ዝርዝሩ በፌደራል መንግስት በስፋት እንደሚገለፅ ብንጠብቅም፤ በማይካድራ ከተማ ነዋሪ በሆኑ የአማራ ወገኖቻችን ላይ በትህነግ ጦር አማካኝነት የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈፅሞባቸዋል።" ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ "ድርጊቱ በዓለም አቀፍ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑን እናምናለን።" ብለዋል በመግለጫቸው።
አያይዘውም "ትህነግ በህዝቦች መካከል የእርስ በርስ ጦርነት (Civil War) እንዲቀሰቀስ አስቦ መሆኑን" በመግለፅ ህዝቡ እንዲረጋጋ ጠይቀዋል።
"በተለመደው አስተዋይ ባህሪህ ምስኪኑ የትግራይ ህዝብ እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም ከየትኛውም ጥቃት ጥላ ከለላ ሁነህ ይህን ጊዜ እንድታሳልፈው ይሁን። በባህል፣ በሃይማኖት፣ በማህበራዊ ትስስር፣ አልፎም በረዥሙ የአገር ግንባታ ጉዞ ከአማራ ሕዝብ ጋር የጋራ ታሪክ ያለውን የትግራይ ሕዝብ መከታና ጋሻ ሆነሁ አስተዋይነትና አብሮነት የምንጊዜም ምርጫህ እንደሆነ ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተግባር እንድታሳይ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።" ብለዋ ለአማራ ህዝብ ባቀረቡት ጥሪ።
" የትግራይ ሕዝብ እንደትላንቱ ሁሉ፣ ዛሬም ሆነ ነገ አብሮህ ይኖራል።" ያሉት አቶ አገኘሁ ይልቁንም በሕወሓት ከተጠመደ ጥፋት በራቀ ሁኔታ ህግ ለማስከበር ለሚደረገው ጥረት ትብብር እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ደመቀ ከበደ
አዲስ አበባ

