የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መጋቢት 12 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
እያከናወናቸው ያሉትን የሰላምና ደኅነነት የማስጠበቅ ግብራዊ እንቅስቃሴዎች ሲገልጥም "የክልሉ መንግሥት የፀጥታ ተቋማቱን ሪፎርም በማድረግ ፤ በአዲስ መልክ ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠር ከምንጊዜውም በላይ የህዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ የሚችል ብቃት ያለው ኃይል እየገነባም ይገኛል" ብሏል፡፡
ለመግለጫው አስባብ ስለሆነው ግጭት ሲያመላክትም "የአሁኑ ግጭት በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ ጥሙጋ እና በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ አካባቢዎች የተፈጠረ ሲሆን ሐሙስ መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ጅሌ ጥሙጋ ላይ በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ ጠብ ምክንያት አንድ ሰው ህይወተ ህልፈትን ምክንያት በማድረግ የተቀሰቀሰ ነው፡፡ በግለሰቦች መካከል የነበረውን ግጭትና የደረሰውን ሞት ምክንያት በማድረግም በሀገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች እርቅ ተፈጽሞ ነበር፡፡
"ይሁን እንጂ የኦነግ ቡድንና እሱን መሰል ተባባሪ የሆኑ አካላት በሀገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች እርቀ ሰላም ወርዶ መፍትሔ ያገኘውን ክስተት ምክንያት በማድረግ ከዓርብ መጋቢት 10/2013 ዓ.ም. ጀምሮ አርሶ አደር ይይዘዋል ተብሎ በማይጠበቅ ከባድና የቡድን መሣሪያ ጭምር በመታገዝ የተደራጀና ብዛት ያለው የታጠቀ ኃይል በአጎራባቹ የሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ ከተማና አካባቢው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ነውረኛ የሆነ ጥቃት ተፈጽሟል" በማለት አስረድቷል።
ክልላዊ መንግሥቱ ድርጊቱን "ፍጹም ተቀባይነት የሌለው አደገኛና ከባድ ወንጀል" ሲል ኮንኖ "በዚህ ጥቃት ለጠፋው ህይወትና ለደረሰው የንብረት ውድመትም የክልሉ መንግሥት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልጻል" በማለት ጉዳቱ ለደረሰባቸው ቤተሰቦችና ወገኖች መልዕክቱን አስተላልፏል።
አያይዞም፤ የክልሉ መንግሥት ጥቃትን ለመግታት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን ተጨማሪ የፀጥታ አካላትን ወደ ሥፍራው በማሰማራት አስፈላጊውን ድርጊት እያከናወነ መሆኑን አብራርቷል።
አክሎም "በአጣየና በአካባቢው የተፈጸመውን ዝርዝር ጥቃት፣ የደረሰውን ሰብአዊና የንብረት ጉዳት መንግሥት በፍጥነት መረጃውን አጣርቶ ለህዝቡ ይፋ" እንደሚያደርግና በጅሌ ጥሙጋ እና በሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት "አጥፊ የወንጀለኞችን ቡድንና በድርጊቱ የተሳተፉት ተባባሪ አካላትን ሁሉ በቁጥጥር ሥር በማዋል" ለሕግ እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡
ጥቃቶችን ለመመከትም ሕዝብ ከመንግሥት ጋር እንዲቆም ጥሪ በማቅረብ፤ በሕዝብ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎም ግጭቱን ለማባባስ ጥረት የሚያደርጉ አካላት "ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ" ሲልም አስጠንቅቋል።

