ዩናይትድ ስቴትስ ትናንት ረቡዕ ጥቅምት 23 ፕሪቶሪያ - ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሓት መካከል "ጠብመንጃዎችን ፀጥ" ለማሰኘት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በመልካም ጎኑ መቀበሏን በመግለጫዋ አስታወቀች።
የሰላም ስምምነቱን አስመልክቶ መግለጫውን ይፋ ያደረገው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁለቱም ወገኖች ግጭቱ እንዲቆም የወሰዱትን የስምምነት እርምጃ ተከትሎ የሁለት ዓመቱን ጦርነት ለመክላትና ሰላምን ለማስፈን በንግግራቸው እንዲቀጥሉ አበረታቷል።
ገደብ ያልተጣለባቸው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትና የሰላማዊ ሰዎች ደኅንነት ጥበቃ ግብር ላይ ለማዋል ከስምምነት ላይ መደረሱንም በማለፊያ ጎንነት ጠቅሷል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአፍሪካ ኅበረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ፋኪን፣ የአሸማጋይ ልዑክ ቡድን መሪ አባሳንጆን፣ የቡድኑ አባላትን ኡሁሩ ኬንያታና ምላምቦ ንግኩካ፣ የደቡብ አፍሪካ መንግሥትን፣ ተመድ፣ ኢጋድን አክሎ ሌሎችንም ሁለቱ ወገኖች ከስምምነት ላይ ለመድረስ እንዲችሉ ላስተባበሩ፣ እገዛ ላደረጉና ለተሳተፉ ተቋማት ሁሉ ምስጋናውን አቅርቧል።
አይይዞም፤ ዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለስምምነቱ ዳር መድረስ አስተዋፅ ላደረጉ አካላት ያቀረቡትን የምስጋና መግለጫ በመልካምነት መቀበሏን ገልጧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የሰላም ልዑክ ቡድን መሪ ሆነው በፕሪቶሪያ በመገኘት የሰላም ስምምነቱ ሰነድ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለመላ ኢትዮጵውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክታቸውን ገልጠዋል።
የሕወሓት የሰላም ልዑክ ቡድን መሪና ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ግና እስካሁን በቲዊተር ገፃቸው ወይም በጋዜጣዊ መግለጫ ስምምነቱን አስመልክቶ ያሉት የለም።
ስምምነቱ ከተፈረመ 24 ሰዓታት አንስቶ ወደ ዝርዝር ትግበራ የሚያመራ ሲሆን፤ በሂደቱም በርካታ የተናጠልና የጋራ መግለጫዎች በይፋ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።