በአፍሪካ ግዙፉ የኃይል ማመንጫ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሁለተኛ ተርባይኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በቤንሻንጉል ጉሙዝ ጉባ ወረዳ በታደሙበት ዝግጅት ነው በዛሬው ዕለት ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት የጀመረው።
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ካሉት 13 ተርባይኖች መካከል ዩኒት 9 የሚባለው ሁለተኛው ተርባይን የተሳካ ተከላ እና ሙከራ ከተደረገ በኋላ ኃይል የማመንጨት ስራው እውን ሆኗል።
ዛሬ በይፋ ሥራ የጀመረው ሁለተኛው ዩኒት 375 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለው ተገልጿል።
በሁለተኛ ተርባይን የኃይል ምንጭ ጅመራ ላይ በሥፍራው የተገኙት የኢትዮጵይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "የሺ ትውልድ ጥያቄ በሚመለስበት ዘመን ተገኝቶ ግድቡ ሲገደብ በዓይን ማየት፣ በእጅ መዳሰስ፣ በእግር መርገጥ ባለ ዕድል ሲያደርግ፤ ለግንባታው ገንዘባቸውን፣ ዕውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ከለገሡት፣ በዲፕሎማሲና በሚዲያ ለዓባይ ከሚከራከሩት፣ ታሪክ ሠሪ ጀግኖች ወገን መሆን ደግሞ ባለ ዕድል ያደርጋል"
"እነሆ አሁን የሕዳሴ ግድብ ከንድፍ አልፎ፣ ግንባታው ተገባድዶ፣ ግዙፍ ውኃ በጉያው ይዞ ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። ዛሬ ዓባይ ተረት ሳይሆን የሚጨበጥ እውነት ነው" ብለዋል።
ETV / SBS Amharic