"ግድያ በማንኛውንም መሥፈርት በሁላችንም ሊወገዝ የሚገባ ኢሰብዓዊ ድርጊት ነው" - ፕ/ት ሳህለወርቅ ዘውዴ

የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን አስመልክቶ የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ግድያውን በማውገዝ የአንድነት ጥሪ አቅርበዋል።

Amharic  news 01 July, 2020

Sahle-Work Zewde, President of Ethiopia Source: Courtesy of PD

ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ በቲዊተር ገጻቸው "የሃገራችን ዝነኛና ታዋቂ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ድንገተኛ ህልፈት የሰማሁት በከፍተኛ ሃዘን ነው። ግድያ በማንኛውንም መሥፈርት በሁላችንም ሊወገዝ የሚገባ ኢሰብዓዊ ድርጊት ነው። በዚህ አጋጣሚ ህዝቡ የራሱንም ሆነ የአካባቢውን ሠላም በመጠበቅ አንድነቱን እንዲያጠናክር ጥሪዬን አቀርባለሁ። ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጆቹ፣ ለአድናቂዎቹ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን እመኛለሁ" ብለዋል።

ቀደም ሲልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የድምፃዊ ሃጫሉን አሟሟት አስመልክተው "ውድ ህይወት አጥተናል። የዚህ ድንቅና አንፀባራቂ ወጣት አርቲስት ሓጫሉ ሁንዴሳ ህይወት መቀጠፍ ከተሰማ ጀምሮ በከባድ ሀዘን ውስጥ ለምንገኝ ሁሉ መፅናናትን እመኛለሁ ። የዚህን ክፉ ድርጊት ሙሉ የፖሊስ ምርመራ ሪፖርት እየተጠባበቅን እንገኛለን " በማለት የተሰማቸውን ኃዘንና ግድያውንም ተከትሎ ሕጋዊ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ አመላክተዋል።

እምብዛም ሳይቆይ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰውና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ ማክሰኞ ምሽት በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸው ላይም ኮሚሽነር እንዳሻው የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ - ኦፌኮ አባል የሆነውን ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 35 ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል። 

አያይዘውም፤ አቶ ጃዋር ለእሥራት በተዳረጉበትም ወቅት የግል የደኅንነት ጠባቂዎቻቸው ይዘዋቸው የነበሩት ስምንት ክላንሺንኮቭ ጠብመንጃዎች፣ አምስት ሽጉጦችና ዘጠኝ የራዲዮ መገናኛዎች አብረው በፖሊስ መያዛቸውን ገልጠዋል። የሌሎች ታሳሪዎች ስም ዝርዝር ግና በወቅቱ አልተገለጠም።

ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው በማከልም "ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይደለም። ሕግ ለማስከበር የጸጥታ አካል በሚወስደው እርምጃ ሁሉም ሰው ተባባሪ መሆን አለበት። አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍል በተሳሳተ አረዳድ እነዚህ ሰዎች የታሰሩበት ሁኔታ ትክክል አይደለም ብሎ በተለያየ መንገድ ተሰልፎ ዳግም ጥፋት እንዳያጠፋ" ፖሊስ እንደሚያሳስብ ተናግረዋል። ሌሎች በግድያው ተጠርጣሪ የሆኑ ግለሰቦችንም ፖሊስ እየተከታተለ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሃጫሉን አሟሟት በተመለከተም ለህልፈተ ሕይወት የበቃው መኪናው ውስጥ ገብቶ ሳለ ተጠርጣሪዎች የመኪናውን በር ከፍተው ጥይት በመተኮስ እንደገሉት ገልጠዋል።

ሃጫሉ የሞተበት ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ የተገኘው የአራስ ባለቤቱን እህት ለመጠየቅ እንደነበረ የሚናገሩም አሉ።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አራርሳም በመግለጫቸው "በጃዋር መሐመድ የሚመራው ቡድን አስከሬኑ በቤተሰቡ ጥያቄ መሰረት ከጳውሎስ ሆስፒታል ወጥቶ ወደ አምቦ እየተሸኘ ሳለ፤ ከቤተሰቡ ፍቃድ ውጪ ቡራዩ ሲደርስ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ አድርጓል" በማለት የድምጻዊው አስከሬን ወደ አዲስ አበባ የብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ጽህፈት ቤት መመለሱንና በሳቢያውም በጥበቃ ላይ የነበረ የኦሮሚያ ፖሊስ በጥይት ሕይወቱ ማለፉን አስታውቀዋል።

የድምጻዊውን አቀባበር አስመልክቶ በመንግሥት በኩል በወላጆቹ ፈቃድ እንደሚፈጸም ሲነገር፤ በሌላ በኩል የሃጫሉ ቀብር ለኢትዮጵያውያን አርበኞችና ታላቅ አስተዋፅዖ አበርካች ዜጎች የመጨረሻ ማረፊያ በሆነው የሥላሴ ቤተክርስቲያን እንዲሆንና መንግሥታዊ የክብር የቀብር ሥነ ሥርዓት እንዲፈጸምለት ጥሪ በማቅረብ ላይ የሚገኙ ድምፆች ጥሪም እየተሰማ ነው።

በሌላም በኩል፤ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ የሆነው CPJ ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በተያያዘ የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱና ተዘግቶ ያለው የኢንተርኔት አገልግሎትም ክፍት እንዲሆን ጠይቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የድምፃዊውን አሟሟት በተመለከተ በከማኅበራዊ ሚዲያ ካስተላለፉት የኃዘን መግለጫቸው ባሻገር በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ሲናገሩ፤

"በሃጫሉ መስዋዕትነት የኢትዮጵያ አንድነት፣ የኢትዮጵያ ሰላም፣ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ጉዞ በአንጸባራቂ መንገድ ዳግም የሚመዘገብ እንጂ የሚቆም አይደለም።"

"በብሔሮች መካከል ቁርሾንና ግድያን ለመፍጠር፣ አንድነታችን እንዲናጋ፣ ሰላማችን እንዲደፈርስ፣ ያሰብናቸው ጉዳዮች እንዳይሳኩ የውስጥና የውጪ ጠላት በመቀናጀት ይህንን እኩይ ተግባር ፈጽመዋል"  ሲሉ የኢትዮጵያን አንድነትንና የለውጡን ሂደት የሚፈታተኑቱ አገር በቀሎች ብቻ ሳይሆኑ የባሕር ማዶኛ እጆችም ጭምር እንደሆኑ አመላክተዋል።    

 

 

 


3 min read

Published

By Kassahun Seboqa Negewo


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now