የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ አዲስ አበባ ውስጥ በተጠመዱ የቦምብ ፍንዳታዎች ሳቢያ የሰዎች ሕይወት ማለፉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው አስታውቀዋል።
ኮሚሽነሩ የቦምብ ፍንዳታዎቹ የደረሱት በሶስት ቦታዎች እንደሆነና የአፈንጂዎቹም ሕይወት ጭምር ማለፉን ቢጠቅሱም ስለ ቦምብ አፈንጂዎቹ ማንነት፣ የምን ያህል ሰዎች ሕይወት እንደጠፋና ቦምቦቹ የፈነዱባቸውን ሥፍራዎች አልገለጡም።
ከሰዎች ሕይወት ባሻገርም በንብረቶች ላይ ጉዳቶች መድረሳቸውንና በአዳማ፣ ቡልቡላ፣ ሻሸመኔ፣ ዝዋይና ሐረር አካባቢዎች ሁከቶች መቀስቀሳቸውን አመልክተዋል።
በሌላም በኩል የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ በሃጫሉ አሟሟት ምክንያት በተቀሰቀሱ ጥቃቶች የ78 ሰላማዊ ዜጎችና የሶስት ፖሊስ ሠራዊት አባላት በድምሩ 81 ሕይወቶች ማለፋቸውን ተናግረዋል።
በአዳማ፣ አርሲ፣ ጅማና ባሌ ሮቤ ሁከቶች የተቀሰቀሱ መሆናቸውንም አክለው ገልጠዋል።
ምንም እንኳ በሌላ በኩል ለሃጫሉ አጎት ሕይወት ማለፍ ሰበቡ አምቦ ከተማ ተቀስቅሶ የነበረውን ሁከት ለማብረድ ጥረት እያደረጉ ሳለ በፖሊስ ጥይት ተመትተው እንደሁ ቢነገርም፤ ኮሚሽነር አራርሳ ግና ለሃጫሉ አጎት ሞት ሰበቡ በተቃዋሚዎች የተወረወሩ ቦምቦች ናቸው ሲሉ ማስተባበያ ሰጥተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ Human Rights watch ባወጣው ሪፖርት ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ስምንት ሰላማዊ ሰዎችና ሁለት ወታደሮች በጥይት የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ገልጧል።
ሪፖርቱ አክሎም፤ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ - ኦፌኮ አመራር አባል አቶ በቀለ ገርባና የኦፌኮ አባል ጃዋር መሐመድ አዲስ አበባ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንዳሉና የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ መሪ እስክንድር ነጋም በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቋል።
ሪፖርቱ የኢንተርኔት አገልግሎት መስጠት እንዲጀመር ጠይቆ፤ መንግሥት ውጥረቶችን ለማርገብ ፈጣን እርምጃዎችን ካልወሰደ ለተባባሰ ቀውስ ሊዳረግ እንደሚችል አሳስቧል።

