የተዋናይ ጆኒ ዴፕንና ተዋናይት አምበር ኸርድን የስም ማጥፋት ክስ ሲመለከቱ የነበሩ የዩናይትድ ስቴትስ ሰባት እማኝ ዳኞች በአምበር ላይ የካሣ ብይን አሳልፈዋል።
የዴፕ የቀድሞ ሚስት ተዋናይት አምበር ለካሣ ከፈላ የተዳረገችው በ2018 ራሷን በቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባነት ገልጣ ለሕትመት ያበቃችው ፅሁፍ 'መልካም ስሜን አጉድፏል፤ ገቢዬንም አሳጥቷል' በሚል በባለቤቷ በተመሠረተባት ክስ ነው።
እማኝ ዳኞቹ አምበር ከባለቤቷ ጆኒ ጋር በትዳር ላይ በነበሩበት ወቅት ገጥሞኛል ስትል የገለጠችው ሁኔታ "ሐሰት" እንደሆነና ድርጊቷም "ጥላቻን የተላበሰ" ነው ብለዋል።
ይሁንና እማኝ ዳኞቹ ዴፕ በግል ጠበቃው በኩል የቤት ውስጥ ጥቃት ክሷ ቅጥፈት ነው በማለቱ በስም ማጥፋት ለአምበር ካሣ እንዲከፍል ተበይኖበታል።
በብይኑ መሠረት ጆኒ ዴፕ ለአምበር ኸርድ 2 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እንዲከፍል፤ አምበር ኸርድ 10.35 ሚሊየን የአሚሪካ ዶላር ለጆኒ ዴፕ እንድትከፍል ተፈርዷል።

ብይኑን ተከትሎ ተዋናይት አምበር ባወጣችው መግለጫ "ልቤ ተሰብሯል፣ ቅርም ተሰኝቻለሁ፤ ለሴቶች የኋልዮሽ ምልሰት ነው " ብላለች።
ጆኒ ዴፕ በበኩሉ ብዩኑ "የቀድሞ ሕይወቴን መልሶ ሰጥቶኛል" ብሏል።


