የዩክሬይን የምጣኔ ሃብት ማዕከል የሆነችውን የጥቁር ባሕር ወደቧ ከኸርሰን ክፍለ ግዛት በቁጥጥሯ ስር ማዋሏን ሩስያ ስታስታውቅ፤ የዩክሬይን መንግሥት ግና አስተባብሏል።
ሆኖም የከኸርሰን ከተማ ከንቲባ በበኩላቸው የሩስያ ወታደሮች በከተማይቱ መንገዶች ላይ እየተዘዋወሩ እንደሆነና ወደ ከተማይቱ ማዘጋጃ ቤት ሕንፃ ማምራታቸውን ተናግረዋል።
በዩክሬይን መንግሥት ስር የሚተዳደረው የባቡር መስመሮች ኩባንያ ሩስያ ኪየቭ አቅራቢያ ባለውና በሺህዎች የሚቆጠሩ ሴቶችና ሕፃናት ተጥልለው ያሉበት የደቡባዊ ባቡር ጣቢያ የአየር ጥቃት እንደደረሰበት አስታውቋል።
በባቡር ጣቢያው ላይ መጠነኛ ጉዳት የደረሰ መሆኑ ቢነገርም፤ የባቡር አግልግሎቶቹ የቀጠሉ ሲሆን በሰው ሕይወት ላይ ስለደረሰ አደጋ አልተገለጠም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በሩስያና ዩክሬይን መካከል የተጀመረው ንግግር ለሁለተኛ ጊዜ በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ ቤላሩስ-ፖላንድ አዋሳኝ ድንበር ላይ ለማካሔድ መሰናዶ እየተደረገ ነው።
የሩስያን ልዑካን ቡድን በኃላፊነት የሚመሩትቭላድሚር ሜድኒስኪ ቡድናቸው ውይይቱ የሚካሔድበት ድንበር ላይ ቀድሞ መድረሱን ገልጠዋል።
አክለውም " የዩክሬይን የልዑካን ቡድን ኪየቭን ለቅቆ መውጣቱን እረዳለሁ። በተስምምነታችን መሠረት እኛ ቀድመን እዚህ ደርሰናል። እነሱም ነገ እዚህ ይደርሳሉ። የጉዞ እክል እንዳለባቸው እንረዳለን። ቤላሩስ ውስጥ ደህንነታቸው ሙሉ በሙሉ የተጠበቀ መሆኑን የቤላሩስ ፀጥታ አገልግሎት ዋስትና ሰጥቷል። የኛ ጦርም ደህንነታቸው ተጠብቆ ከዩክሬይን ተነስተው እዚህ እንዲደርሱ መተላለፊያቸውን ያመቻቻል። ነገ ልናገኛቸው እየጠበቅን ነው" ብለዋል።
ተመድ ጠቅላላ ጉባኤ
የተባብሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ትናንት ረቡዕ በአብላጫ ድምፅ ባሳላፈው የአቋም መግለጫ የሩስያን የዩክሬይን ወረራ "በብርቱ" እንደሚያወግዝ ገልጧል።
የአቋም መግለጫው የጥቃት እርምጃው በአስቸኳይ እንዲቆምና ሩስያ ጦሯንም በፍጥነት ከዩክሬይን እንድታወጣ የሚጠይቅ ነው።

የአቋም መግለጫው ከ193 አባል አገራት ውስጥ በ 141 አገራት ሲደገፍ፤ ሩስያና ኤርትራን አካትቶ 5 አገራት ተቃውመውታል።
ቻይናን ጨምሮ 35 አገራት ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የ12 አገራት ድምፅ በድጋፍ፣ በተቃሞም ሆነ በድምፀ ተአቅቦ አልተመዘገበም።

