በንግግራቸውም ወቅት አውስትራሊያውያን አገልግሎታቸውን ከግምት ውስጥ አስገብተው እሳቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት፤ ፓርቲያቸውን ለመንግሥትነት ስላበቋቸው በሕይወታቸው የተጎናፀፉት ትላቅ ክብር መሆኑን በመግለፅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፤ ይበልጡን ታትረው እንደሚሠሩም ቃል ገብተዋል።
አቶ አልባኒዚ ለሁለተኛ ጊዜ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ከመብቃታቸውም በላይ ፓርቲያቸው እስከ 87 የምክር ቤት ወንበሮችን በማሸነፍ የአብላጫ መንግሥት እንደሚመሠርቱ የምርጫ ውጤቶች እያመለከቱ ነው።
አቶ አልባኒዚ ድል መነሳታቸውን አምነው የተቀበሉትን ተሰናባቹን የተቃዋሚ ቡድን መሪ ብርቱ ፍልሚያ የተካሔደበትን የ2025 ሀገር አቀፍ ምርጫ በመልካም ቃላት ማጠናቀቃቸውን አንስተው አመስግነዋቸዋል።
አቶ ዳተን "በእዚህ ምርጫ በመልካም አልተወጣንም፤ ለእዚያም ዛሬ ምሽት ሙሉ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ። ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘንድ ስለ ዛሬ ምሽቱ ስኬታማነታቸው እንኳን ደስ አለዎት ለማለት ደውያለሁ። ለሌበር ታሪካዊ ወቅት ነው፤ ለእዚያም ዕውቅናችንን እንቸራለን" ብለዋል።

አክለውም ተቀናቃኛቸውና ድል ነስተው የምክር ቤት ወንበራቸውን የተረከቧቸው የሌበር ዕጩ አሊ ፍራንስ ዘንድም ደውለው እንኳን ደስ ያለዎት ማለታቸውንና ወ/ሮ ፍራንስ ማለፊያ ሥራን እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

ወ/ሮ ፍራንስ ለ24 ዓመታት የዲክሰንን ምክር ቤት ይዘው ቆይተው የነበሩትን ፒተር ዳተንን ለማሸነፍ የበቁት ለሶስተኛ ጊዜ ባደረጉት ጥረት ነው።

