የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያን የአጎዋ ተጠቃሚነት ዕድል ማንሳቱን አስታወቀ። የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የማሊ እና የጊኒን የአጎዋ ዕድል ተጠቃሚነት አንስቷል። ማዕቀቡ ማሊና ጊኒ ላይም ተጥሏል።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ ኢትዮጵያ 237 ሚሊዮን ዶላር ምርት አጎዋን በመጠቀም ያለ ቀረጥ ወደ አሜሪካ ልካለች፡፡ ፕሬዚደንት ባይደን ማክሰኞ ዕለት ኢትዮጵያን ከ ‹‹African Growth and Opportunity Act›› (አጎዋ) ፕሮግራም ተጠቃሚነት ለማግለል የወሰኑት አንድ ዓመት ሊያስቆጥር በተቃረበው የትግራይ ጦርነት "የጅምላ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት" በመፈጸሙ እንደሆነና "ኢትዮጵያ፣ ጊኒና ማሊ የአጎዋን መመዘኛዎች ለማሟላት ቀጣይ መሻሻል ማድረጋቸው ላይ ግምገማ ማድረጋችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።
ማዕቀቡ ግብር ላይ እንዲውል የታሰበው ከጃኑዋሪ 1 ጀምሮ ነው ። ምንም እንኳ እርምጃው ለቀጣይ ምጣኔ ሃብታዊ ዕቀባ መንገድ ጠራጊ ነው ተብሎ በተወሰኑ የዋይት ሃውስ ውስጥ አወቆች ዘንድ ቢነገርም የዩናይትድ ስቴትስ የንግድ ተዋካይዋ ካትሪን ታይ ቢሮ ባወጣው መግለጫ ማዕቀቡን ከልቶ ዳግም አገራቱ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የዩናይትድ ስቴትስ አስተዳደር ከአገራቱ ጋር አብሮ እንደሚሠራ በማሳሰብ በሩ ሙሉ በሙሉ አለመዘጋቱን ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የባይደን አስተዳደር ከዚህ ውሳኔ ላይ እንዳይደርስ የተቻሉትን ጥረቶች አድርጓል። የኢትዮጵያ ንግድ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም እርምጃው "ፍትሐዊ ያልሆነ ተፅዕኖ በሴቶችና ሕፃናት ላይ ያሳድራል። ኢትዮጵያ ሆን ተብሎ ወይም ስህተቶች ተብለው የታሰቡን ለማረም የሚቻለውን ጥረት ሁሉ በማድረጉ ትቀጥላለች" ብሏል።
በተለይም ኢትዮጵያ ከአጎዋ መሰረዟ አገር ውስጥ የሚገኙት እንደ Calvin Klein, Tommy Hilfiger እና H&M የመሳሰሉ በዓለም ታዋቂ አምራቾች አገር ውስጥ መቆየታቸውን ጥያቄ ውስጥ ያስገቡም አሉ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ
ኢትዮጵያ ለስድስት ወራት ፀንቶ የሚቆይ አገር አቀፍ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አዋጀች። አዋጁን የሚያስፈፅም፣ የሚከታተልና በበላይነት የሚመራ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዝ” ይሆናል።
የአዋጁ ዋነኛ ትኩረቶች፤
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙን እንቅስቃሴ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ዓላማ የሚቃረን፣ የሚቃወም እና ለሽብር ቡድኖች ዓላማ መሳካት አስተዋፅዖ የሚያደርግ፣ የሽብር ቡድኖችን የሚያበረታታ፣ ሰላማዊ ዜጎችን የሚያሸብር ንግግር በማንኛውም መንገድ ማድረግ ወይም ማሰራጨት የተከለከለ ነው
• በየትኛውም መንገድ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሽብር ቡድኖች የገንዘብ፣ የመረጃ፣ የቁስም ሆነ የሞራል ድጋፍ ማድረግ የተከለከለ ነው
• የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መምሪያ ዕዙ በተዋረድ ውክልና ከሰጣቸው አካላት ፈቃድ ውጭ ማንኛውንም የአደባባይ ስብሰባ ወይም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የተከለከለ ነው
•ከመከላከያ፣ ከፌዴራል ፖሊስ ወይም ሌሎች ፈቃድ ከሚሰጣቸው የፀጥታ አካላት ወይም ከነዚህ አካላት እውቅናና ፈቃድ ውጭ ማናቸውንም የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው
• በከተሞች አካባቢ የነዋሪ መታወቂያ፣ የመንጃ ፈቃድ፣ የሰራተኛ መታወቂያ፣ ፓስፖርት ወይም ከነዚህ ተመጣጣኝ የሆነ መታወቂያ ሳይዙ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው
• ማንኛውም ወሳኝ በሆነ የአገልግሎት ዘርፍም ሆነ በምርት ሂደት ላይ የስራ ማስተጓጎል ወይም የኢኮኖሚ አሻጥር መፈፀም የተከለከለ ነው
• የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈፃፀም ሰበብ በማድረግ የግል ጥቅም ለማግኘት ስልጣንን አላግባብ መጠቀም፣ ምክንያታዊ የሆነ ጥርጣሬ ሳይኖር ሆን ብሎ ዜጎችን ማሰር ወይም መሰል እርምጃ መውሰድ የተከለከለ ነው የሚሉ ናቸው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚጸናው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ሲሆን ፀንቶ የሚቆየውም ለስድስት ወራት ይሆናል። በአዋጁ ላይ የስድስት ወር ጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዋጁ ተፈፀሚነት ቀሪ የሚሆንበትን ጊዜ ሊወስን እንደሚችልም ተጠቅሷል።

