ማንዲ ዊክስ የSBS ዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሆኑ

*** ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ኮሮናቫይረስ ዳግም ሊያገረሽ እንደሚችል አስገነዘቡ

Amharic News 03 September 2020

Mandi Wicks Source: SBS

በአሁኑ ወቅት የSBS ኦዲዮና ቋንቋ ዝግጅት ዳይሬክተር ሆነው ያሉት ማንዲ ዊክስ የSBS ዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል።

ዊክስ አዲሱ የሥራ ኃላፊነታቸውን በያዝነው ወርኃ ሴፕቴምበር መገባደጃ ላይ የሚጀምሩ ሲሆን የSBS ዜናና ወቅታዊ ጉዳዮችን መምራት "ታላቅ ዕድል" ነው ብለዋል።

አያይዘውም፤ 

"እንደ SBS ያለ የአውስትራሊያን ገጽታ የሚያንጸባርቅና የሚረዳ አንዳችም የዜና አውታር የለም። ይህንኑ ከመላው ዓለምና አውስትራሊያ ዝንቅ አተያዮችን የማቅረቡን ሁነኛ ሚና ለማስቀጠል ዕድል በማግኘቴ በእጅጉ በሐሴት ተመልቻለሁ" ሲሉ ደስታቸውንና ታትረው ለመሥራት ያላቸውን ብርቱ ተነሳሽነት ገልጠዋል።

ዊክስ ሙያቸውን የጀመሩት በጋዜጠኛነት ሲሆን ቀጥለውም በዜናዎች አስተዳደር ሚና በማኳየሪ ራዲዮ ኔትዎርክና ሳውዘርን ክሮስ ኦስቴርዮ ተዘዋውረው ሠርተዋል።  

ወደ SBS ከመጡም በኋላ የSBS ራዲዮ ዲጂታል ግልጋሎቶችን ጨምሮ በኦዲዮና ቋንቋ ዝግጅት የአመራር አስተዋፅዖዋቸውን አበርክተዋል።

በተጨማሪም የSBS ሠፈራ መምሪያና የSBS ኮሮናቫይረስ ፖርታል ተነሳሽነት ወስደው ግብር ላይ እንዲውል አድረገዋል።  

ይህንኑ አስተዋፅዖዋቸውን አስመልክቶም የSBS አስተዳደር ዳይሬክተር ጄምስ ቴይለር "ልዩ መሪና ፈጣሪ" በማለት ስለ ማንዲ ዊክስ የበኩላቸውን ቃለ ውዳሴ ቸረዋል።   

ቴይለር አያያዘውም፤ ዊክስ በእግራቸው የሚተኩትን ተሰናባቹን ጂም ካሮል ከሰባት ዓመታት በላይ ላበረኩት የላቀ ግልጋሎት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

Amharic News 03 September 2020
Jim Carroll announced his retirement in March, 2020. Source: SBS

ተሰናባቹ ጂም ካሮል ከSBS ዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ዳይሬክተር ኃላፊነታቸው የተነሱት ማርች ላይ ጡረታ ለመውጣት እንደሚሹ በማስታወቃቸው ነው።

ቫይረስ - ቪክቶሪያ

ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ እሑድ ሴፕቴምበር 6 ለቪክቶሪያ ገጠርና ከተሞች የሁለትዮሽ ፍኖተ ካርታዎቻቸውን ይፋ ለማድረግ ተቃርበው ባሉበት ዕለተ ሐሙስ 113 ሰዎች ቪክቶሪያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል፤ 15 ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ሕይወታቸውን ካጡት ውስጥ አራት ወንዶችና ሶስት ሴቶች በ80ዎቹ፣ ሁለት ወንዶችና ስድስት ሴቶች በ90ዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ነበሩ።

በአሁኑ ወቅት 361ቪክቶሪያውያን ሆስፒታል ተኝተው ሕክምና እየተከታተሉ ሲሆን 20ዎቹ በፅኑ ሕሙማን ክፍሎች 15ቱ የሰው ሠራሽ መተንፈሻ ተገጥሞላቸው በሕክምና ላይ ይገኛሉ።

ፕሪሚየር አንድሩስ እሑድ ሴፕተምበር 6 ይፋ በሚያደርጓቸው ፍኖተ ካርታዎች ለተጨማሪ ሁለት ሳምንታት የደረጃ 4 ኮሮናቫይረስ ገደቦች እንደሚቀጥሉና ከሴፕቴምበር 14 ጀምሮ፤

  • አካላዊ እንቅስቃሴ ለ2 ሰዓታት
  • ሁለት ሰዎች ከቤት ውጪ መገናኘት
  • አንድ ሰው ቤት ውስጥ ተቀብሎ ማስተናገድ እንደሚቻልና
  • ከ8pm-5am ተጥሎ ያለው ሰዓት ዕላፊ ገደብ እንደሚጸና

እንዲሁም ከሴፕቴምበር 28 በኋላ፤

  • ከ8pm-5am ተጥሎ ያለው ሰዓት ዕላፊ ገደብ ይነሳል
  • እስከ 5 ሰዎች ከቤት ውጪ መገናኘት ይችላሉ
  • ሙዋ ዕለ ሕጻናት ፈቃድ ሳይሹ ክፍት ይሆናሉ
  • ለተርም 4 ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ይመለሳሉ

ተብሎ ከወዲሁ ሾልከው የወጡ መረጃዎች በሚል ቢነገርም፤ ፕሪሚየር አንድሩስ ግና ጊዜ ያለፈበት መረጃ እንደሆነና ተጣድፈን ገደቦችን ካነሳን ቫይረሱ "ዳግም ሊያገረሽ" ይችላል ሲሉ አሳስበዋል።   

 

 

  


2 min read

Published

Updated

By NACA

Presented by Kassahun Seboqa Negewo


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now