የቤት ዕድሳትና ግንባታ ድጎማ
የአውስትራሊያ ፌዴራል መንግሥት እየቀዘቀዘ ያለውን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እንዲያንሰራራ ለማድረግ የቤት ዕደሳ ወይም ግንባታ ለማድረግ ለሚሹ የ25ሺህ ዶላርስ ዶጎማ ሊያደርግ ነው።
የድጎማ ገንዘቡን ለዕድሳት ተግባር ማግኘት የሚችሉት ከ $150,000 እስከ $750,000 ወጪ የሚያደርጉና የቤታቸው የወቅቱ ዋጋ ከ$1.5 ሚሊየን ዶላርስ ያልበለጠ ከሆነ ይሆናል።
አዲስ ቤት ሠሪዎች የድጎማው ተጠቃሚ የሚሆኑት የሚገነቡት ቤት ወጪ ከ$750 000 ዶላርስ በላይ ካልሆነ ነው።
ድጎማው የገቢ መመዘኛ መሥፈርቶችም አሉት።
ላጤ ሆነው የዓመት ገቢያቸው ከ$125 ሺህ ዶላርስ በላይ የሆነና ጥንዶች ሆነው የዓመት ገቢያቸው በጣምራ ከ$200 ሺህ በላይ የሆኑትን አያካትትም።
ለትርፍ የሚገነቡና የሚታደሱ ወይም በራስ እጅ የሚሠሩ የቤት ፕሮጄክቶች የድጎማው ተጋሪ አይሆኑም።
የ$688 ሚሊየን ዶላርስ የቤቶች ግንባታ ድጎማ ዕቅዱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሥራዎችን ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነ የቤቶች ሚኒስትር ማይክል ሱካር ሲገልጡ፤
"ከ20 ሺህ በትንሹ ዘለል ያሉ አዳዲስ ቤቶችን ለመገንባትና ከ7 እስከ 8 ሺህ የሚደርሱ የቤት ዕድሳቶችን ለማድረግ ያስችላል። ለመገንባትና ለማደስ ባለው ጥያቄ መሠረት የሚከናወን ዕቅድ ነው። ይህን ግብር ላይ ማዋሉም የአውስትራሊያውያን ፈንታ ነው" ብለዋል።
በጆርጅ ፍሎይድ ሞት አዲስ ክሶች
የሚኔሶታ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ኪትዝ ኢሊሰን ጆርጅ ፍሎይድ አንገት ላይ ከ 8 ደቂቃዎች በላይ [[8 ደቂቃዎች ከ 46 ሰከንዶች]] በጉልበቱ ተጭኖ ይዞት በነበረው የቀድሞ የፖሊስ ሠራዊት አባል ላይ መሥርቷቸው የነበሩ ክሶቹን አሻሻለ።
ደሪክ ሾቪን ላይ የተመሠረተው ክስ ከሶስተኛ ወደ ሁለተኛ ደረጃ የግድያ ክስ ከፍ ሲል፤ በጆርጅ ፍሎይድ እሥራት ወቅት አብረው የነበሩት ሶስት የቀድሞ የፖሊስ ሠራዊት አባላት ላይም ለግድያ እገዛ የች ተመሥርተውባቸዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እየተካሔዱ ያሉ የተቃውሞ ሰልፎች እንደቀጠሉ ሲሆን፤ ከተቃውሞው ጋር ተያይዘው ሲከሰቱ የነበሩ የአመጽ ግብሮች እየቀነሱ ነው።
የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር - ማርክ ኢስፐር የፖሊስ ተግባርን ለማገዝ የወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ላይ እንደማይስማሙ ገልጠዋል።
የዓለም ጤና ድርጅትና የወባ መከላከያ መድኃኒት
የዓለም ጤና ድርጅት ለወባ መከላከያ መድኃኒትነት የሚውለውን ሃይድሮክሲክሎሮኪን ለኮቪድ - 19 መከላከያነት ይጠቅም እንደሁ ለማረጋገጥ ተቋርጠው የነበሩት ክሊኒካዊ ሙከራዎች እንዲቀጥሉ ወሰነ።
የዓለም ጤና ድርጅት ቀደም ሲል ክለሳ እስከሚያደርግ ድረስ ሙከራዎቹ እንዳይከናወኑ እቀባ ጥሎ ነበር።

