የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉን በሕግ ድጋፍ ከቆሙላት አንዲት ሴት ወሲባዊ ጥቃት ጋር አያይዘው በተጠርጣሪነት ያነሱት ጠበቃ ጉዳዩ ገና ዕልባት ያላገኘ መሆኑን ገለጡ።
ይሁንና ዐቃቤ ሕግ ክሪስቲያን ፖርተር ከቶውንም በሴቲቱ ላይ ወሲባዊ ጥቃት አልፈጸምኩም ሲሉ አስተባብለዋል።

ምንም እንኳ የኒው ሳውዝ ዌይልስ ፖሊስ ከወሲባዊ ጥቃት ጋር ምርመራውን የዘጋ ሲሆን፤ የደቡብ አውስትራሊያ ኮሮነር ዴቪድ ዊትል ግና የግለሰቧ አሟሟት በውል ያልተቋጨ ስለሆነ ፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ እንዲያካሂድ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል በጅሮንድ ጆሽ ፍራይደንበርግ አቶ ፖርተር በተጠረጠሩበት ጉዳይ በሕግ ተጠያቂነታቸው እስካልሆኑ ድረስ ከወንጀል ድርጊት ነፃ የመሆናቸው ሕጋዊ መብት ሊጠበቅላቸው እንደሚገባና እንደ ሥራ ባልደረባነታቸውም ድጋፋቸውን እንደሚቸሯቸው ገልጠዋል።
ይሁንና የግለሰቧ ጓደኛና የሕግ ባለሙያ የሆኑት ማይክል ብራድሌ ማስተባበያ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ ይፋ የሆነ ምርመራ ሊካሄድ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሌበር መሪ አንቶኒ አልባኒዚም በበኩላቸው በተመሳሳይ መልኩ በቀድሞው የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ዳይሰን ሄይደን ላይ የተካሄደው ዓይነት የወሲባዊ ጥቃት ምርመራ እንዲካሄድ አተያያቸውን ሰንዝረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የመከላከያ ሚኒስትር ሊንዳ ሬይኖልድስ የቀድሞ የሚዲያ አማካሪያቸውንና ቢሯቸው ውስጥ ወሲባዊ ጥቃት ደርሶብኛል ብላ አቤት ብላ ያለችውን ብሪታኒ ሂገንስን "lying cow" ብለው በመሳደባቸው ከሚኒስትርነት ኃላፊነታቸው እንዲነሱ ጥሪዎች እየቀረቡባቸው ነው።
ሚኒስትሯ ሂገንስን "lying cow" ማለታቸውን ያላስተባበሉ ሲሆን ያን ያሉት ግና ለሂገንስ የሰጡት ድጋፍ በሂገንስ ተዛብቶ በመቅረቡ እንደሆነ አልሸሸጉም። ሚኒስትር ሬይኖልድስ በልብ ሕመም ምክንያት በሐኪም ፈቃድ ዕረፍት ላይ ይገኛሉ።

የዋሪንጋህ የግል የምክር ቤት ተመራጯ ዛሊ ስቲጋል ከሚኒስትሯ አንደበት ወጡ የተባሉት ቃላቶች ትክክል ከሆነ የብሪታኒ ሂገንስን ብርታት የሚያኮስስ ሊሆን እንደሚችልና የወ/ሮ ሬይኖልድስ በኃላፊነታቸው መቀጠልም አስተማማኝ ሊሆን እንደማይችል አመላክተዋል።
የታዝማኒያ የግል ተመራጭ ሴናተር ጃኪ ላምቢ በፊናቸው ሚኒስትሯ "በአስቸኳይ ከስልጣናቸው ሊነሱ ይገባል" ሲሉ ቁርጥ ያለ አተያያቸውን ሰንዝረዋል።
የሌበር ሴናተር ፔኒ ዎንግ በበኩላቸው "ይህ ተቀባይነት የሌለው አባባል መሆኑ ግልጽ ነው" በማለት ሚኒስትር ሬይኖልድስ አደባባይ ወጥተው ማስረዳት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የመከላከያ ሚኒስትር ሊንዳ ሬይኖልድስ ብሪታኒ ሂገንስን "lying cow" በማለታቸው "በጣሙን ተጸጽተዋል" አባባላቸውም ከድጋፍ አሰጣጡ ጋር ባላቸው የተለየ አተያይ እንጂ በቀጥታ ከወሲባዊ ጥቃቱ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ በማመላከት አለዝበው ገልጠዋል።
የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክርስቲያን ፖርተር ጉዳይንም አስመልክተው እንደ በጅሮንድ ጆሽ ፍራይደንበርግ አቶ ፖርተር በተጠረጠሩበት ጉዳይ በሕግ ተጠያቂነታቸው እስካልሆኑ ድረስ ከወንጀል ድርጊት ነፃ የመሆናቸው ሕጋዊ መብት ሊጠበቅላቸው እንደሚገባ በመግለጽ ከጎናቸው እንደሚቆሙ ተናግረዋል።
አቶ ፖርተር ከሁለት ሳምንት የአዕምሮ ጤና ዕረፍት ሲመለሱም በሥራ ገበታቸው ላይ እንደሚሠማሩ ጠቁመዋል።

