የዩክሬይን ትልቁ የኑክሊየር ጣቢያ በሩስያ ከባድ መሣሪያዎች ጥቃት ደርሶበት የእሳት ቃጠሎ ተቀስቅሷል

*** የአውስትራሊያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሕንድና ጃፓን መሪዎች የዩክሬይንን ግጭት በጋራ አወገዙ፤ ለኢንዶ ፓስፊክ አካባቢ የሰብዓዊና የድንገተኛ አደጋ ዕርዳታ ፕሮግራም ዘረጉ

News

This image made from a video released by the Zaporizhzhia nuclear power plant shows a bright flaring object landing in the grounds of the plant. Source: AP

የዩክሬይን ዛፖሪዚሕዝያ ትልቁ የኑክሊየር ጣቢያ በሩስያ ጦር ጥቃት ደርሶበት የእሳት ቃጠሎ መቀስቀሱን የዩክሬይን ባለስልጣናት ገለጡ።

የኢነርሆዳር ከተማ ከንቲባ ዲሚትሮ ኦርሎቭ "በአውሮፓ ትልቁ የኑክሊየር ጣቢያ የሆነው ዛፖሪዝሕዝያ ኑክሊየር ጣቢያ በእሳት ተያይዟል" ብለዋል።

ሮይተርስ እንዳመለከተው ለጊዜው የቃጠሎው መጠን ለማረጋገጥ አልተቻለም።  

የዩክሬይን ፕሬዚደንት ቫሎድሚር ዜሌንስኪ ጥቃቱ ፍንዳታን ካስከተለ የአውሮፓ ፍፃሜ እንደሚሆን ለምዕራባውያን መሪዎች በስልክ አሳስበዋል። 

የንድሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጥቃቱን አስመልክቶ አስቸኳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት እንዲመክርበት ጥሪ የሚያደርጉ መሆኑን አስታውቀዋል።  

የአራትዮሽ ስብሰባ

የአውስትራሊያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሕንድና ጃፓን መሪዎች የዩክሬይንን ግጭት በጋራ አወገዙ፤ ለኢንዶ ፓስፊክ አካባቢ የሰብዓዊና የድንገተኛ አደጋ ዕርዳታ ፕሮግራም ዘረጉ።

የአራትዮሹ የፀጥታ ንግግር ላይ የአገራቱ መሪዎች ስለ ዩክሬይን ወረራና ሰብዓዊ ቀውስ አንስተው የተነጋገሩ ሲሆን፤ የኢንዶ ፓስፊክ አካባቢ ከወታደራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ ጫና ነፃ እንዲሆን ተግተው እንደሚንቀሳቀሱ ዳግም ቃላቸውን አድሰዋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የአራትዮሹን ስብሰባ አስመልክተው ባወጡት መግለጫ አውስትራሊያ ለዩክሬይን ጦር ማጠናከሪያ የሚውል 50 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እንዲሁም ለአስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ የሚውል 25 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መቸሯን ገልጠዋል። 

የአራቱ አገራት መሪዎች በመጪዎቹ ወራት ቶኪዮ ላይ ተገኛኝተው ለመነጋገር ተስማምተዋል። 

የሩስያ ዩክሬይን ንግግር                                     

ሩስያና ዩክሬይን ቤላሩስ ውስጥ ባካሔዱት የሁለተኛ ዙር ንግግር ለሰብዓዊ ግልጋሎት የሚውል መተላለፊያ ለማበጀት ተስማሙ። 

የዩክሬይን ፕሬዚደንት አማካሪ ሚኻይሎ ፖዶልያክ ንግግሩ ታስበው ከነበሩ ውጤቶች ላይ ባይደርስም በምግብ፣ ሕክምናና ቀዬን ለቅቆ መውጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እንደተነጋገሩ ገልጠዋል። 

አቶ ፖዶልያክ ጊዜያዊ የተኩስ ማቆምን አስመልክተ ሲናገሩም፤ 

"ሁለቱ ተደራዳሪ ወገኖች ብርቱ ውጊያ በሚካሔድባቸው ሥፍራዎች የሕክምናና ምግብ አቅርቦትን ማድረስ የሚቻልበትን ሁኔታ አካትቶ፤ ሰላማዊ ሰዎች ቀዬአቸውን ለቅቀው በሚወጡበት ሰብዓዊ መተላለፊያ ማበጀት ላይ ከጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል። ሰላማዊ ሰዎች ቀዬአቸውን ለቅቀው በሚወጡበትም ወቅት ጊዜያዊ  ተኩስ ማቆም ማድረግ ስለሚቻልበትም ሁኔታ አበክሬ አሳስቤያለሁ። ይህ ማለት ግና በሁሉም አካባቢ ይሆናል ማለት አይደለም። ተኩስ ማቆም ላይ ሊደረስባቸው የሚችሉ ሥፍራዎች ሰላማዊ ሰዎች ቀዬአቸውን ለቅቀው እንዲያልፉ ሰብዓዊ መተላለፊያዎች የሚበጁባቸው ሥፍራዎች ይሆናሉ" ብለዋል።      

አያይዘውም፤ ሁለቱም ተደራዳሪ ወገኖች እንደገና ተገናኝተው የሶስተኛ ዙር ንግግር ለማድረግ መስማማታቸውን አስታውቀዋል።  

 

ፑቲን

የሩስያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ልዩ ወታደራዊ ኃይላቸው ዩክሬይን ውስጥ ውጤት እያስመዘገበ እንደሆነና በግጭቱ ሳቢያ ሕይወታቸው ላለፈ ወታደሮችም የተሰማቸውን ኃዘን በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር ገልጠዋል። 

በንግግራቸው ወቅትም የምዕራቡ ዓለም መሪዎች ጦራቸው የአቅርቦት ችግሮች እንደገጠመውና ብርቱ ፍልሚያም በዩክሬይን በኩል እንደደረሰበት ከገለጡበት ሁኔታ የተገላቢጦሹን ተናግረዋል። 

አቶ ፑቲን የሩስያና ዩክሬይን ሕዝብ አንድ ሊሆኑ እንደሚገባ በማንሳት የጦርነቱም አንዱ ምክንያት ይኼው መሆኑን አመላክተዋል። 

በሌላ በኩል የፈርንሳይ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን ከሩስያው ፕሬዚደንት ጋር በስልክ እንደተነጋገሩ ጠቅሰው፤ አቶ ፑቲን ራሳቸውን እያታለሉና በዩክሬይን ወረራም ስህተት እየሠሩ ነው ሲሉ ተናግረዋል። 

አክለውም፤ ፑቲን በዩክሬይን ላይ የሰነዘሩት ጥቃት ሩስያን ለረጅም ጊዜያት ሊያገልላትና በማዕቀብ ስርም ሊያቆያት እንደሚችል አሳስበዋል።                                                   

ዩክሬይን አውስትራሊያ

የአውስትራሊያ መንግሥት  ወረራ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ዩክሬናውያን መገልገያነት የሚውሉ ከ 1,000 በላይ ቪዛዎችን መደበ።

የቪዛዎቹ ተጠቃሚ ዩክሬናውያን አውስትራሊያ ውስጥ ለ12 ወራት በቱሪስትነት መቆየት የሚችሉ ሲሆን የሥራ መብቶችንና ሜዲኬይር የመጠቀም ዕድልን አያስገኝላቸውም።

የማኅበረሰብ ድርጅቶች ግና ወደ አውስትራሊያ የሚመጡ ዩክሬናውያን የሥራ መብቶችም እንዲኖራቸው ድምፃቸውን እያሰሙ ነው። 

ቪዛዎቹን ካገኙት ውስጥ አብዛኛዎቹ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ነገ ቅዳሜ ማርች 5 እና እሑድ ማርች 6 አውስትራሊያ ይገባሉ።

የብሔራዊ ስደተኞች አማካሪ ቡድን ሊቀመንበር ዛብናም ሳፋ አውስትራሊያ ለዩክሬይን ስደተኞች ያደረገችውን ፈጣን ምላሽ አድንቀው ይሁንና ይህ ዓይነቱ የስደተኞች ቅበላ የተወሰኑትን መርጦ ሌሎችን በማግለል መሆን እንደሌልበት አሳስበዋል።

የአፍጋኒስታን ስደተኞች ተሟጋች ቡድንም በፊናው የአውስራሊያ መንግሥት ለዩክሬይን ብቻ ሳይሆን የታሊባን አገዛዝና ግጭት ሰለባ ለሆኑ ስደተኞችም ተጨማሪ ሰብዓዊ ቪዛዎች እንዲሰጥ ጠይቋል። 

 


3 min read

Published

Updated

By NACA

Presented by Kassahun Seboqa Negewo


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now