በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ቪክቶሪያ ላይ ተጥሎ የነበረው የፊት ጭምብል የማጥለቅ ግዴታ ደንብ ከነገ እሑድ ዲሴምበር 6 በኋላ ሊነሳ ነው።
የቪክቶሪያ ዋና የጤና ኃላፊ ብሬት ሳተን ቪክቶሪያ ወደ "COVID normal" ገደቦች ደረጃ ለመሸጋገር የሚያስችል ሁኔታ ላይ መሆኗን ለአንድ የፓርላማ መርማሪ ኮሚቴ ገልጠዋል።
በሌላም በኩል የቪክቶሪያ ጤና ሚኒስትር ማርቲን ፎሊ ነገ እሑድ የሚያከትመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሰኞ የሚጀምረውን የሆቴል ወሸባ ፕሮግራም ግብር ላይ ለማዋል እንዲያስችል የሚራዘም መሆኑን አስታውቀዋል።
የፊታችን ሰኞ ዲሴምበር 7 ከአምስት ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አምስት ዓለም አቀፍ በረራዎች ሜልበር አውሮፕላን ማረፊያ ያርፋሉ።
የቪክቶሪያ በጅሮንድ ቲም ፓላስ የተዘረጋው ፕሮግራም በመልካም ሁኔታ እንደሚሠራ ያላቸውን አመኔታ ገልጠዋል።
ቪክቶሪያ ለ35 ተከታታይ ቀናት አንዳችም በኮሮናቫይረስ የተጠቃ ግለሰብ ሳታስመዘግብ ከርማለች።
ተመራጭ - ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ፕሬዚደንታዊ ቢሮአቸውን እንደ ተረከቡ ባሉት የመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት አሜሪካውያን የኮሮናቫይረስ ተዛማችነትን ለመግታት የፊት ጭምብል እንዲያጠልቁ ጥሪ የሚያደርጉ መሆኑን ገለጡ።
ጆ ባይደን ይህን የተናገሩት 14.2 ሚሊየን አሜሪካውያን በኮሮናቫይረስ ተጠቅተውና 276,000 ሕይወታቸውን አጥተው ባሉበት ወቅት ነው።
አቶ ባይደን ከCNN ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የፊት ጭምብል ማጥለቅን ግዴታ ማድረጉ በቫይረሱ መስፋፋት ላይ ብርቱ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ሲያስቡ፤
[["ቃለ መሃላ በምፈጽምበት የመጀመሪያዋ ቀን ሕዝቡን ለ100 ቀናት ጭምብል እንዲያጠልቅ እጠይቃለሁ። ለሁሌም ሳይሆን፤ ለ100 ቀናት ብቻ። 100 ቀናት። እንዲያ ከሆነ ክትባትና ጭምብል ተዳምረው የቫይረሱ ቁጥሮች በአያሌው እንዲያሽቆለቁል ሲያደርጉ ለማየት እንችላለን ብዬ አስባለሁ"]] ብለዋል።

