በሊባኖስ መዲና ቤይሩት ወደብ ላይ በደረሰው መጠነ ሰፊ ፍንዳታ ሳቢያ እስካሁን 157 ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፤ ከ5000 በላይ ቆስለዋል፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ የደረሱብት አልታወቀም።
ከ 300,000 በላይ ነዋሪዎች ለጊዜያዊ መጠለያ አልባነት ተዳርገዋል።
እስካሁን ዘጠኝ ኢትዮጵያዊያን እንደቆሰሉና አንድ ለሕልፈተ ሕይወት መዳረጉን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይሁንና ጉዳት ያገኛቸው ግለሰቦች ማንነትና ጾታ፤ እንዲሁም የደረሱበት ያልታወቀ ግለሰቦች ብዛት ገና ይፋ አልሆነም።
የቤይሩት አስተዳዳሪ ማርዋን አቡድ የደረሰው ጉዳት ከ$10 እስከ $15 ቢሊየን ዶላርስ እንደሚገመት ገልጠዋል።
በምጣኔ ሃብት ድቅቀት፣ አብዮታዊ እንቅስቃሴና በሙስና እየታመሰች ላለችው ሊባኖስ የፍንዳታው ጉዳት እጅግ መጠነ ሰፊ መሆን በሊባኖሳውያን ዘንድ ብርቱ የከፋ ኃዘንና ቁጣን አሳድሯል።
ለፍንዳታው ምክንያት የሆነው በወደቡ በሚገኝ አንድ የዕቃ መጋዘን ውስጥ ተከማችቶ የነበረ 2,750 ቶንስ አሞኒየም ናይትሬት በመጋየቱ ነው።
ፍንዳታው ከቤሩት 240 ኪሎ ሜትሮች ርቆ ሳይፕረስ ድረስ ተሰምቷል።

ፍንዳታው በሕይወትና ንብረት ላይ ካደረሰው ጉዳት ጋር ተያይዞ የእንግሊዟ ንግሥት ኤልሳቤጥ፣ የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰንና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ በርካታ የዓለም መሪዎች የተሰማቸውን ጥልቅ ኃዘን ገልጠዋል።
ቤይሩት የሚገኙ ዜጎቻቸውም የቆንሱላ እርዳታዎችን ለማግኘት ኤምባሲዎቻቸውን እንዲያገኙ አሳስበዋል።

ቤይሩት የሚገኙ ሊባኖሳውያውያን - አውስትራሊያውያን 20 ሺህ የሚደርሱ ሲሆን በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም እዚያ እንደሚገኙ ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን አውስትራሊያ ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የሚውል $2 ሚሊየን ዶላርስ እንደምትሰጥ ቃል ገብተዋል።
በኢትዮጵያም በኩልም እርዳታ መላኩ ተነግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ኒውካስትል - ኒው ሳውዝ ዌይልስ ውስጥ ከቤይሩቱ በአራት እጥፍ በላቀ ተከማችቶ ያለው አሞኒየም ናይትሬት ቀደም ሲል ቅሬታቸውን ሲያሰሙ በነበሩ ነዋሪዎች ላይ አዲስ ሥጋትን አሳድሯል።
ማክሰኞ ዕለት የቤይሩት ወደብን ለውድመት የዳረገው አሞንየም ናይትሬት ክምችት ብዛት የነበረው 2,750 ቶንስ ነበር።
በኒው ካስትል ወደብ ኩራጋንግ ደሴት በኦሪካ የማዕድን ኩባንያ ተከማችቶ ያለው አሞኒየም ናይትሬት መጠን ግና ከ 6,000 እስከ 12,000 ቶንስ እንደሚደርስ ይታመናል።

ይሁንና አንድ የኬሚካል መሐንዲስ፤ ኒውካስትል ያለው የአሞኒየም ናይትሬት ክምችት ከነዋሪዎች ራቅ ያለና በአግባቡ የተያዘ በመሆኑ እምብዛም ሊያሳስብ እንደማይገባ ተናግረዋል።
ቪክቶሪያ ቫይረስ
ቪክቶሪያ ውስጥ ባለፉት 24 ሰዓታት 471 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሲያዙ፤ ስምንት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በትናንትናው ዕለት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 725 ደርሶ ቀደም ካሉት ቀናት ሁሉ ሬኮርድ የሰበረ ነበር።
በኮቪድ - 19 በዛሬው ዕለት ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ከተገለጸው ውስጥ ሁለት ወንዶች በ60ዎቹ፣ ሶስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች በ80ዎቹ፣ እንዲሁም አንዲት ሴት በ90ዎቹ ዕድሜ የነበሩ ናቸው።
ቪክቶሪያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት በቫይረሱ ተጠቅተው ያሉ 7,449 ሲሆኑ 1,533ቱ በአረጋውያን መጦሪያ ቤቶች የሚገኙ ናቸው።
ከዛሬ ሐሙስ ጀምሮም በሜልበርን የንግድ ተቋማት ላይ የተጣሉ ገደቦች ግብር ላይ ውለዋል።
በግልጋሎቶቻቸው አስፈላጊነት በራቸው በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ክፍት የሚሆኑ ተቋማት ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታዎቻቸው ለመሰማራት ሲጓዙ የሠራተኛ ፈቃድ ወረቀት ከአሠሪዎቻቸው ማግኘት ይገባቸዋል።
የሠራተኛ ፈቃድ ለማይገባቸው አሠሪዎች አላግባብ የፈቃድ ወረቀት ሰጥተው የሚገኙ አሠሪዎች በአዲሱ ድንጋጌ መሠረት እስከ $99,123 አላግባብ የሠራተኛ ፈቃድ ይዘው የተገኘ ግለሰብም እስከ $19,826 የሚደርስ መቀጮዎች ይጣልባቸዋል።

