የፌዴራል ሌበር ፓርቲ መሪ አንቶኒ አልባኒዚ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን አውስትራሊያ ውስጥ ያሉ የሩስያ ዲፕሎማቶችን ከአገር እንዲያስወጡ ጥሪ አቀረቡ።
አቶ አልባኒዚ ባወጡት መግለጫ አውስትራሊያ እንደ አውሮፓውያኑ አገራት ፈረንሳይና ጀርመን ሁሉ አውስትራሊያም የሩሲያን ዲፕሎማቶችና ሠራተኞች አገር ለቅቀው እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባት አሳስበዋል።
አቶ አልባኒዚ የሩስያ ጦር አባላት በዩክሬይን ላይ ፈጽመዋል የተባሉትን የግድያ ሪፖርቶች አስመልክቶ እርምጃዎች እንዲወሰዱም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
ሆኖም ዲፕሎማሲያዊ የግንኙነት መስመር እንዳይቋረጥ የሩስያ አምባሳደር አውስትራሊያን ለቅቀው እንዲወጡ ጥሪ አላቀረቡም።
ይህንኑ አስመልክቶ የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜሪዝ ፓይን የሩስያ ዲፕሎማቶችን ከአገር የማስወጣቱ ጉዳይ ላይ ክለሳዎች እየተደረጉ መሆኑን ገልጠዋል።
አያይዘውም፤ በአውስትራሊያ የሩስያ አምባሳደር ሩስያ ዩክሬይን ውስጥ እየፈጸመች ያለችውን ድርጊቶች አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ዲፓርትመንት ፀሐፊ ዘንድ በዚህ ሳምንት በድጋሚ ቀርበው እንደነበር ተናግረዋል።
ባርሴሎና አውስትራሊያ
ግዙፉ የዓለም እግር ኳስ ቡድን ባርሴሎና የእግር ኳስ ክለብ በሚቀጥለው ወር አውስትራሊያ ውስጥ ከሲድኒ ደረጃ ሀ የተውጣጡ ምርጥ ኮከብ ተጫዋቾች ቡድን ጋር ግጥሚያ ያደርጋል።
ባርሴሎና አውስትራሊያ ውስጥ መጥቶ ግጥሚያ ሲያደርግ በታሪክ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነው።
ባርሴሎና ግጥሚያውን የሚያካሂደው 80,000 ያህል ታዳሚዎች ተገኝተው ጨዋታውን ይመለከታሉ ተብሎ በሚጠበቀው ኤኮር ስታዲየም ሜይ 25 ነው።

የባርሴሎና እግር ኳስ ክለብ ምክትል የማስታወቂያ ፕሬዚደንት ሁሊ ጊው እንደገለጡት ግጥሚያው ክለቡንና ዕሴቶቹን ለአድናቂዎቹና አዲስ ተመልካቾቹ ይበልጡኑ አቅርቦ የሚያሳይበት አጋጣሚ ይሆናል።
ባርሴሎና በመላው ዓለም 270 ሚሊየን ደጋፊዎች ያሉት ሲሆን፤ 26 ላ ሊጋ የአሸናፊት መጠሪያዎችን፣ አምስት የአውሮፓ ዋንጫዎችን፣ 31 ኮፓ ዴል ሬይ ሽልማቶችንና ሶስት የፊፋ ክለብ የዓለም ዋንጫዎችን ያሸነፈ ቡድን ነው።

